በደጃዝማች ታከለ ወልደ ሐዋርያት መሪነት የተደራጀ የመኮንኖች ቡድን አፄ ኃይለሥላሴን ለመግደል ማሴሩ ተደርሶበት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ከሽፎ ደጃዝማች ታከለ እጄን አልሰጥም ብለው ተኩስ ከከፈቱ በኋላ እራሳቸውን ያጠፉት ከ 50 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 7 ቀን 1962 ዓ.ም ነበር።
ደጃዝማች ታከለ በአልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን አማካኝነት በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በተላላኪነት ተቀጥረው ትንሽ ካገለገሉ በኋላ በአልጋ ወራሹ ትዕዛዝ የማዘጋጃው ፅህፈት ቤት ኃላፊ ተደርገው ተሾሙ። ከ1922 እስከ 1927 ዓ.ም ድረስ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣታቸው በመረጋገጡ የብላታ መዓረግ ተሰጥቷቸው 11ኛው የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ተሾሙ።
ደጃዝማች ታከለ የፋሽስት ጦር ኢትዮጵያን ሲወር በሸዋ በጅሩ፣ በጎጃምና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከጣሊያን ጦር ጋር ተፋልመዋል። በመጨረሻም ወደ ጎንደር ሄደው ከጎንደር አርበኞች ጋር ተቀላቅለው የአርበኝነት ስራ ሰርተዋል። ከድል በኋላም የከተማ ከንቲባ ቦታቸውን መልሰው የተረከቡ ሲሆን፤ ቆይተው ደግሞ በአገር አስተዳደር ሚኒስተር ምክትል ሚኒስተር ሆነው አገልግለዋል። ደጃዝማች ታከለ በስልጣን ላይ ሆነው ከ1935 አንስቶ እስከ ህዳር 7 ቀን 1962 ዓ.ም ድረስ ሶስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎችን አድርገው ሶስቱም ከሽፈውባቸዋል።
በመጨረሻ ያደረጉት መፈንቅለ መንግስት የሻምበል፣ የአስር አለቃ፣ የሃምሳ አለቃ፣ የመቶ አለቃ፣ የሻለቃና የፈንጅ መሀንዲስን ያቀፈ እንደሆነ ይነገራል። መፈንቅለ መንግስቱ ከከሸፈ በኋላ ደጃዝማች ታከለ በሰላም እጅ ሰጥተው ለህግ እንዲቀርቡ ቢጠየቁም አሻፈረኝ በማለት ተኩስ ከፍተው የፖሊስ አባላትን ካቆሰሉ በኋላ የሚስጥር ሰነዶችን አቃጥለው የያዙትን ሽጉጥ ጠጥተው ሲሞቱ የመፈንቅለ መንግስት ቀበኝነታቸው አብቅቷል።
ፍስሐ ያዜ ካሳ በ2004 ዓ.ም ባሳተሙት “የኢትዮጵያ አምስት ሺ ዓመት ታሪክ ካልተዘመረለት ኢያሱ እስከተዘመረለት ኢህአዴግ መጽሐፍ ሁለት” በጃንሆይ ላይ የተነሱ አመጾች በሚል ርእስ ስር እንደጠቀሱት ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋርያት አደገኛ አመጸኛ ነበሩ። ንጉሱ ስደትን ከመረጡ ጊዜ ጀምሮ ለ30 ዓመታት ያህል መንግስታቸውን ለመፈንቀል ሲጣጣሩ ነው የኖሩት። ሲታሰሩ ፤ ሲፈቱ ፤ ሲሾሞና ሲሻሩ ነው ያሳለፉት።
በመጀመሪያ አርበኞችን አስተባብረው አሳድመዋል ተብለው ታሰሩ። እንደገና ተፈትተው በ1938 ዓ.ም ምክትል አፈንጉሥ ሆነው ተሾሙ። ዓመት ሳይቆዩ ሌላ ተመሳሳይ ሴራ ሲጠነስሱ ተደረሰባቸውና ታስረው ሰባት ዓመታትን አሳለፉ። ተፈቱና የአገር ግዛት ምክትል ሚንስቴርና የአፈ-ንጉስነቱ ስልጣን ተመለሰላቸው። ይሄ ሁሉ ሲሆን ጃንሆይ ከአሁን አሁን ይበርድላቸዋል ብለው በመገመትና ጀግንነታቸውንም በደንብ ስለሚያውቁት ነበር የሚታገሷቸው።
በመጨረሻም በ1962 ዓ.ም ጃንሆይ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ለመጎብኘት ሲሄዱ ሰበታ አካባቢ ፈንጅ አጥምደው ንጉሱን ከነመኪናቸው ድምጥማጣቸውን ለማጥፋት ተዘጋጁ። ሁኔታው ቀድሞ በጥቆማ ተደረሰበትና ከሸፈ። ደጃዝማች ታከለ ቤታቸው መሽገው ነበርና በወታደር ተከበው ተኩስ ተከፈተባቸው። እጅ አልሰጥም ብለው ሲዋጉ ቆይተው መያዛቸው እርግጥ መሆኑን ሲረዱ ራሳቸው ላይ ጨክነው የሞት ጽዋን ተጎነጩ።
አዲስ ዘመን ጥቅም3/2012
የትናየት ፈሩ