አዲስ አበባ፦ በንግድና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ተግባራት በጎ ጅምር ቢያሳዩም በአፈፃፀም የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያለፉትን አምስት ወራት እቅድ አፈፃፀም እና የመቶ ቀን እቅድና ተግባራዊነቱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሐዋሳ ውይይት አካሂዷል። በወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶ በመተግበር ላይ ያለው የመቶ ቀናት እቅድ ዋነኛ ዓላማ ዘመናዊ፣ ፍትሐዊና በውድድር ላይ የተመሠረተ የንግድ አሠራርና የግብይት ሥርዓትን ማስፈን ነው። በንግድና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ተግባራት በጎ ጅምር ቢኖሩም በአፈፃፀም ላይ የሚነሱ ግድፈቶችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
እንደ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገለጻ፤ በመቶ ቀናት እቅዱ ውስጥ ከተካተቱ ሥራዎች ውስጥ የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ትኩረት ተሰጥቷል። በተለይም መንግሥት ከውጭ የሚገቡ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ተደራሽና ፍትሐዊ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል። የዘርፉን ማነቆዎች ለመግታት ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ማቅረብ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም የወጪ ንግድን የዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ትስስር አካል በማድረግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦው እንዲጎላ እየተደረገ ነው። ዘርፉን ለማዘመንና ውጤታማ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በልዩ ትኩረት መደገፍ የእቅዱ አንድአካል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ባለሀብቶቹን የዘርፉ መሪ ተዋናይ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል። አያይዘውም በአሁን ሰዓት ለሀገሪቱ ፈታኝ የሆነው የውጭ ንግድ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ ነው። የወጪ ንግድ ምርቶችን ለማሳደግ በስፋት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በንግድና ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ እና የዘርፉን አፈጻጸም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በከፍተኛ አመራሩ ድጋፍና አቅጣጫ ሰጪነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። በተጨማሪም በየደረጃው ባለው መዋቅር አማካኝነት ወደ ተግባር የሚለወጥ ዕቅድ ወጥቶ በመተግበር ላይ እንደሆነና በዚህም ተስፋ ሰጪ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ባደረገባቸው አምስት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ውይይት፤ የዘርፉን ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል። በእቅዶቹ ትግበራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች እየተለዩ በጋራ መሥራት የሚቻልበት መንገድ እንዲመቻች አቅጣጫም ተቀምጧል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2011
በተገኝ ብሩ