የአዳራሹ ድባብ ልዩ ነው፡፡ የአረጋውያንን ባለውለታነት የሚገልፁ፤ የአዛውንቶችን ስራ የሚዘክሩ ጣዕመ ዜማዎች ከመድረኩ ተከታትለው ይደመጣሉ፡፡ የእነርሱ በዓል ነውና በአዳራሹ የታደሙ እድሜ ጠገብ አባትና እናቶች በራሳቸው መዘከሪያ ቀን ባህላዊ አልባሳትን ለብሰው የክብር መጎናፀፊያቸውን ተጎናጽፈው ቦታቸውን ይዘዋል::
በመድረኩ ላይ ወጥተው ለሀገራቸው ሰላም፣ ለህዝባቸው ጤና፣ ለራሳቸው እድሜ በማይጠገቡ የርህራሄ ቃላት አምላካቸውን ይማፀናሉ፡፡ ወጣቱ ትወልድ ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ ነገሮችን ሰከን ብሎ በታላቅ ትዕግስት እንዲያይና የሀገሩን አንድነት እንዲያስቀጥል አባታዊ ጥሪ ያቀርባሉ:: ታዳሚው ልመናቸውን በአሜን፣ ጥሪያቸውን ትህትና በተላበሰ መንፈስ ያዳምጣል፡፡
በእድሜ ዘመናቸው ተምረው፣ በህይወት ተሞክሯቸው ልቀው፣ ከታዳሚው ተመርጠው መድረኩ ላይ ሆነው የድምፅ ማጉያውን እየተቀባበሉ ለዛ ባለው አንደበት መልዕክት የሚያስተላልፉት አዛውንቶች ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ሀገራዊ ሰላም በማረጋገጥ አባቶቹ ያስረከቡትን ሀገር አንድነት እንዲያፀና አባታዊ ተማፅኖአቸውን ይደጋግማሉ::
አቶ ፀጋ መሰለ የ98 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ እድሜ ፀጋ ነውና በህይወት ዘመናቸው ያካበቱትን ልምድ ለወጣቱ ትውልድ ማውረስ ስለሰላም መስበክ በብርቱ ይመኛሉ፡፡ “ወጣቱ ትውልድ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መዘንጋት አይገባውም” የሚሉት አዛውንቱ፤ የሀገር አንድነት ማስጠበቅ እና የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠንከር ለሀገራዊ ለውጥ ወሳኝ መሆኑን ይመክራሉ፡፡
ትናንት የአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባዘጋጀውና “የለውጥ ልማተ ጉዞ አረጋውያንን በእኩልነት ይዞ” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለ28 ጊዜ በተከበረው የአረጋውያን ክብረ በዓል ላይ የተገኙት አቶ ፀጋ የሰላም እጦት የሚያስከትለው ውጤት አስከፊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
አቶ ፀጋ፤ ወጣቱ ትውልድ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲያጤንና ለሀገሩ ህልውና ዘብ እንዲቆም ያሳስባሉ፡፡ “አረጋውያን ሰላምን በማረጋገጡ ሂደት የላቀ ሚና መጫወት ይገባቸዋል” ያሉት የእድሜ ባለፀጋው አቶ ፀጋ መለሰ ወላጆች ወጣት ልጆቻቸውን በማነፅ በጎ ትውልድ በመፍጠሩ በኩል የራሳቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
አባ ሙዳ አበበ ሀይሉ የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ አረጋውያን ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ገልፀው፤ ወጣቶች የአረጋውያንን ጥሪ ተቀብለው የሀገራቸውን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ሰላም በሁሉም ረገድ ውጤት ያስገኛል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ የድርሻውን ሊወጣ የሚገባ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ ተስፋዬ ተርፋሳ፤ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን ልምድና እውቀታቸው ለወጣቱ ትውልድ በማውረስ የልማቱን ስራ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ “አረጋውያን የሰላም መፍትሄ አመላካች ናቸው” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ሰላማዊ ማህበረሰብ በመፍጠር በኩል ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው፤ አረጋውያን በእድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን ልምድ መጠቀም እንደሚገባ ገልፀዋል:: ኃላፊዋ ሀገራዊ አንድነትን በመገንባትና ሰላምን በማስጠበቅ ሂደት የአረጋውያን አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሀገራችንን ከገባችበት ችግር ለማላቀቅ አረጋውያን የማይተካ ሚና እንዳላቸውም ወይዘሮ ዓለምፀሀይ ያስረዳሉ::
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2012
ተገኝ ብሩ