• ወንጀለኞችን ለመያዝ ሥርዓት መዘርጋቱን ኮሚሽኑ ገለጸ
አዲስ አበባ:- ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና ሕዝባዊ አንድነትን የሚፈታተን፣ አገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚሰራ የተደራጀ ኃይል ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ መኖሩን በመገንዘቡ፤ የሰላም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አደጋውን ለመከላከል ኃይላቸውን አስተባብረው እንዲሰሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ክልሎች ወንጀለኞችን አሳልፈው እንዲሰጡ፣ በየከተሞች የመሸጉ ወንጀለኞች ካሉ አሳድዶ ለመያዝና ውጭ አገር ያሉ ወንጀለኞች ካሉም በኢንተርፖል አማካኝነት ወደ አገራቸው እንዲገቡ እየሰራ እንደሚገኝ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ትናንት የተቋማቸውን የ2012 ዓ.ም ዕቅድና የአንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ ለአገራዊ ደህንነትና ለሰላም ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ተቋማትን የያዘ እንደመሆኑ ኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችንና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ሊያዳምጥ ይገባዋል፡፡ ለሃገራዊ አንድነትና ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ የሆኑ ሃይሎችን መከላከል የሚያስችል ስራ እንዲሰራም አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትሩና ተጠሪ ተቋማቱ ከለውጡ አኳያ መቃኘት ያለባቸው ሕጎች ካሉ እንዲመለከቷቸው አሳስበዋል፡፡ ያልተፈቱ የፖለቲካ ችግሮች ምክር ቤቱ ሊያግዝ የሚችልበትን አቅጣጫ እንዲያመለክትም ጠቁመዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፣አሁን የሚታዩ ችግሮች ምንጭና አባባሽ ምክንያቶች መለየታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ተጠሪ ተቋማቱ በሚኒስትሩ ስር መደራጀታቸው ችግሩን ለመፍታት ተስፋ እንደሚሰጥና ጥሩ ዕድል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የችግሩ ምንጭ ብሔር አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፤ በእዚህ እንጠቀማለን ያሉ ግንባር ፈጥረው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የችግሩ ምንጭ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ፖለቲከኞች ሰከን ብለው ከራስና ከቡድን ፍላጎት በላይ አገርን ሊያስቀድሙ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የፖለቲካ መድረኩ ችግርን የሚፈታ መሆን እንደሚገባውም አመልክተዋል፡፡ እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚንቀሳቀሱ አካላትን ኅብረተሰቡ ራሱ እንዲለይ የማንቃትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡ ሕገወጥነትን ለመከላከል ምንጩን መሠረት በማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ቅንጅታዊ ሥራ ይተገበራልም ብለዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው በየአካባቢው ያልተፈቱ የፖለቲካ ችግሮች ቁልፍ ችግሮች እንደሆኑበትና መፈታት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ሄዶ ሄዶ ወደ ጸጥታ ኃይሉ እንዳታስገቡብን ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ችግሩን ለማስተካከል በየአካባቢው የሚሰራ ሥራ መኖሩንና ከአመራሩ አልፎ ወደ ጸጥታ መዋቅሩ ሰርጎ እንዳይገባ እየተከታተለ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
«ነፃ ሆነን እንድንሰራ አድርጉን፣ ልቀቁን፣ ተውን» ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የእኛ ተልዕኮ የሕዝቡን ደህንነትና ሕገ መንግሥት መጠበቅ ነው እስካልተለወጠ ድረስ በሕገ መንግሥቱ የተመለከቱትን መሠረት አድርገን እንሰራለን ብለዋል፡፡ ኮሚሽነር እንዳሻው የትኛውም ኅብረተሰብ ምንም ዓይነት አመለካከት ቢኖረውም አያገባንም እንጠብቃለን ብለዋል ለቋሚ ኮሚቴው፡፡
ቁልፍ ችግሩ ከምክር ቤቱ ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ያለው የአስተዳደር ወይም የፖለቲካው ክንፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሂደቱ ሰላምን፣ ልማትንና የዴሞክራሲ ግንባታውንም እያወከ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሰላም የማረጋገጥ ሥራው ሄድ መለስ የሚሉ ነገሮች ይታዩበታል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ «ጠብ ሲል ስንደፍን፣ ጠብ ሲል ስንደፍ» እየሆነብን ነው ብለዋል፡፡ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያሳስበው ሁሉ ማገዝ አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ኮሚሽኑ ወንጀለኞችን የመለየት ችግር እንደሌለበት የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ ወንጀለኞች መያዝ ላይ ግን ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ወንጀለኞች በአዲስ አበባ ከተማና በክልሎች የተደበቁ እንዲሁም ከአገር ውጪ የሸሹ መኖራቸውንም አብራርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማና በክልሎች የሚገኙትን ወንጀለኞች የሚደብቀው አመራሩና ኅብረተሰቡ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
ከክልሎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ ክልሎች አሳልፈው መስጠት ያለባቸው ወንጀለኞች ካሉ አሳልፈው እንዲሰጡ፣ በየከተሞች የመሸጉ ወንጀለኞች ካሉ አሳድዶ ለመያዝ ይሰራል ብለዋል፡፡ ውጭ አገር ያሉ ወንጀለኞች ካሉም ከብዙ አገራት ጋር እየተጻጻፍን ነው በኢንተርፖል አማካኝነት ወደ አገራቸው እንዲገቡ እየሰራን ነው፣ ሥራው እገዛ ይፈልጋል፡፡ ሥርዓቱ ተዘርግቷል ብለዋል፡፡
ወንጀል እንዳይፈጸም አስቀድሞ የመከታተል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፤ አንዳንዶች ወንጀል ከሰሩ በኋላ ብሔር ጋር እየተመሸጉ ይገኛሉ፣ ችግር ከተፈጠረ በኋላም መደበቂያው ሃይማኖት አካባቢ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡ ብዙሃን መገናኛና ማህበራዊ ሚዲያው ለኅብረተሰቡ ሳይመዝን መረጃዎችን እየለቀቀ እንደሚገኝ ይህም መታረም እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2012
ዘላለም ግዛው