አዲስ አበባ፡- በታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኘው አንድነት ፓርክ የልማት ድርጅት እንዲሆን የመተዳደሪያ ደንብ ለማጸደቅ በሂደት ላይ እንደሆነ የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡ ፓርኩ በቀን አምስት ሺ ጎብኚዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡
የአንድነት ፓርክ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ታምራት ኃይሌ ከፓርኩ ባለቤትነትና ከሥራ እንቅስቃሴው ጋር በተያያዘ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ከመስከረም 29 ቀን 2012 ጀምሮ ፓርኩን ለሕዝብ ክፍት በማድረግ ሥራ የጀመረው የአንድነት ፓርክ ባለቤት ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ ከፓርኩ የሚገኘው ገቢም ለጽሕፈት ቤቱ ይውላል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ቤተመንግሥቱን ጨምሮ በሥሩ ያሉትን ሀብቶችንም ያስተዳድራል፡፡ የልማት ድርጅት ሆኖ ተግባሩን እንዲወጣም የመተዳደሪያ ደንቡን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማስጸደቅ በሂደት ላይ መሆኑን ዶክተር ታምራት አስታውቀዋል፡፡
ፓርኩ በቀን እስከ አምስት ሺ ጎብኚዎችን የማስተናገድ አቅም አለው ያሉት ዶክተሩ የክፍያ አገልግሎት ከጀመረበት ከጥቅምት 3 ቀን 2012 ጀምሮ በቀን በአማካይ አንድ ሺ ጎብኚዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የአንድ ወር የጎብኚዎች ቁጥር እና የገቢ መጠን በቅርቡ እንደሚሰላ ያመለከቱት ዶክተር ታምራት ቁጥሩ በየዕለቱ የሚያሻቅብ ቢሆንም መረጃው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የጎብኚዎች ቁጥር ከ15ሺ በላይ መድረሱንና ከውጭና ከሀገር ውስጥም ጎብኚዎች ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚገኝ ዶክተር ታምራት ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ፓርኩ ማስተናገዱን የጠቆሙት ዶክተር ታምራት፣ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው የሀገር ውስጥ ጎብኚ መሆኑንና በተለይ ቅዳሜና እሁድ ላይ የጎብኚው ቁጥር እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡
በኤሌክትሮኒክስ የተመቻቸውን ክፍያ አለመጠቀም፣ በጉብኝት ወቅት ቅርሶችን በእጅ የመነካካት፣ መፀዳጃ ቤት በአግባቡ አለመጠቀም፣ በጉብኝት ወቅት ሕፃናትን በአግባቡ አለመያዝ በጥቂት ጎብኚዎች ላይ የሚስተዋል መሆኑንና በሂደት እያስተካከሉ መሄድ እንደሚያስፈልግ ትምህርት መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱን ለማቀላጠፍም ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ፓርኩ ካሉት ስድስት የቱሪስት መዳረሻዎች አምስቱ በአገልግሎት ላይ መሆናቸውንና ለተለያዩ እንስሳት መኖሪያ በተዘጋጀው ስድስተኛው መዳረሻ በቅርቡ ሦስት መቶ እንስሳት ይገባሉ፤ በሀገር ውስጥ የሌሉ እንስሳትም እንደሚካተቱ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2012
ለምለም መንግሥቱ