አዲስ አበባ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር በ100 ቀናት እቅዱ በብቃትና በውጤታማነት ባለሙያዎችን በመመደብ እንደገና የማደራጀት እና የጉምሩክ ኮሚሽንን የማቋቋም ሥራውን አጠናቋል፡፡
ይህ ከመቶ ቀናት ዕቅዱ መካከል በተጨባጭ ያከናወናቸው ሲሆኑ፤ ሌሎች ሥራዎች ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የ100 ቀናት እቅድ ይዘት በአብዛኛው ሚኒስቴሩን እና ኮሚሽኑን የማደራጀት ሲሆን፤ ሥራውም በአጭር ጊዜ የተከናወነ ነው፡፡ ሚኒስቴሩን እንደ አዲስ የማደራጀት ሥራው የሥራ ብቃት፣ ተነሳሽነትና ሥነምግባርን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህም የአገሪቱን ገቢ በትክክል ለመሰብሰብ፣ ህገወጥ አሰራርን ለመከላከልና የገቢ አሰባሰቡን በአግባቡና በትክክለኛው መንገድ ለማካሄድ የሚያግዝ ነው፡፡
አቶ አዲሱ እንዳሉት፤ የጉምሩክ ሥርዓትን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ህግን በማስከበር ህጋዊነትን ለማጠናከር የሚያግዝ የጸጥታ አካል ስለሚያስፈልግ የጉምሩክ ፖሊስ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም የህግ ማስከበር ሥራው በፌዴራል ፖሊስ ይሠራ የነበረ ሲሆን፤ አባላቶቹ አልፎ አልፎ ለግዳጅ ወደ ሌላ ቦታ ሲላኩ ኬላዎች እና የፍተሻ ጣቢያዎች ክፍት የሚሆኑበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት አዲስ የጉምሩክ ፖሊስ ተቋቁሟል። ተጠሪነቱም ለፌዴራል ፖሊስ ሆኖ የጉምሩክ ህግ ማስከበሩን ሥራ በኬላዎች ላይ በቋሚነት ይሠራል፡፡
በፍተሻ ጣቢያዎችና በኬላዎች የሚገኙ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ሥነምግባርን መሰረት ባደረገ መልኩ አዲስ ምደባ ተካሂዷል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ የሚያዙ የኮንትሮባንድ ንብረትና ገንዘብ እየጨመረ የመጣው የቁጥጥር ሥርዓቱ በመጠናከሩና ባለሙያዎች በሥነ ምግባር እንዲሠሩ በመደረጉ መሆኑን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከኃላፊዎች ጋር በሚፈጠር ግንኙነት እና ባለሙያዎችን በገንዘብ በመደለል ይደረጉ የነበሩ የኮንትሮባንድ ንግድ ሰንሰለቶችን ለመበጣጠስ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የሚኒስቴሩን አገልግሎት አሰጣጥ ደካማ መሆን፣ የታክስ ስወራ፣ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ መበራከት፣ በውስጥም በውጭም የታክስ አስተዳደሩ ለምዝበራ ተጋላጭነቱ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ፣ ዝቅተኛ የታክስ አሰባሰብ እና የሪፎርም ሥራዎች ቀጣይነት ማጣትን የመሳሰሉ በሚኒስቴሩ የተንሰራፉ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የመቶ ቀናት እቅድ መዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡
እቅዶቹም በአብዛኛው የተቋሙን ባለሙያዎች ብቃትና ሥነምግባር ማሻሻል ላይ ያተኮረ የሥራ ምደባ ማካሄድና ለባለሙያዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ መፍጠር ሲሆን፤ ደንብ፣ መመሪያና አሰራሮችን ማስተካከል፣ የታክስ ህጉን በትክክል ሥራ ላይ ማዋል እና ተጠያቂነትን ማስፈንም በመቶ ቀናት እቅዱ ተካቷል፡፡ ገቢን በብቃት መሰብሰብ የሚያስችሉ የፊስካል ሥራዎችን በመሥራት በግማሽ ዓመቱ የተያዘውን 121 ቢሊዮን ብር አሟጦ መሰብሰብ፣ ከሁሉም ጋር በመተባበር ኮንትሮባንድን መከላከል የሚያስችል ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋትም ይገኙበታል፡፡
እንዲሁም የኦዲት ጥራት ችግርን የሚፈታ አሰራርን በማጠናከር ጥራቱን 80 በመቶ ለማሳደግ፣ የሽያጭ መመዝገበያ ማሽኖች ችግርን መፍታትና እንዲሁም አዲስ የተጨማሪ እሴት ታክስና የኤክሳይዝ ግብር አሰራር መተግበር መጀመርም ከ100 ቀናት እቅዶች ውጤት የሚጠበቁ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
በሰላማዊት ንጉሴ