አዲስ አበባ፡- የ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የማኑፋክቸሪንግ የወጪ ንግድ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሽመልስ ሲሳይ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የ2011 ዓ.ም የሩብ ዓመት የማኑፋክቸሪንግ ወጪ ንግድ ገቢ ታቅዶ የነበረው 180 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም አፈጻጸሙ ግን 129 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም አፈፃፀሙ 71 ነጥብ ስድስት በመቶ ያህል ነው፡፡ ይህ በ2010 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ተገኝቶ ከነበረው 119 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው የ9 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ቢኖረውም የሚጠበቀውን ያህል ገቢ አለመገኘቱ ግን ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
እንደባለሙያው ገለጻ፣ የወጪ ንግዱ አፈፃፀም አነስተኛ እንዲሆን ምክንያት የሆኑት የአስተዳደር፣ ቴክኖሎጂ፣ የቴክኒክና አቅም ውስንነቶች መሻሻል አለማሳየት፣ የግብዓት አቅርቦት ጥራት በተሟላ መልኩ ማረጋገጥ አለመቻል እና የግብይት አቅም ውስንነቶች ናቸው፡፡ የገበያና ተያያዥ የዋጋ አፈፃፀም ችግሮች፣ የወጪ ንግድ ሥርዓትን አለማክበር እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት አሁንም መፈታት ያልቻሉ ችግሮች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም መዘግየት ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዋነኛ ማነቆዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሽመልስ አሁንም ልዩ ትኩረት በመስጠት በዘላቂነት የሚፈቱበትን አቅጣጫ አስቀምጦ መረባረብን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ሥጋና ወተት፣ ምግብና መጠጥ፣ ፋርማሲቲካል፣ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ ብረታብረት፣ ኢንጂነሪንግ፣ ኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
በሰላማዊት ንጉሴ