አዲስ አበባ፡- የህብር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሆኑት ወዛም ግርማ እና መሰለ ግርማ ከአንድ መምህር ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ኢፍትሀዊ በሆነ የትምህርት ቤቱ ውሳኔ ከጥቅምት 27 ጀምሮ መባረራቸውን ታኅሣሥ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ዘግበን ነበር። ሆኖም ውሳኔው ተስተካክሎ ተማሪዎቹ ከታኅሣሥ 15 ቀን ጀምሮ ወደ መደበኛ ትምህርታቸው መመለሳቸውን ትምህርት ቤቱ አስታውቋል።
ተማሪዎቹ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ህግና ደንብን ያላከበረ እንዲሁም የወላጅ ኮሚቴዎችን ያላሳተፈና ለመምህሩ ብቻ የወገነ ነው በሚል አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሁሉ አነጋግሮ መዘገቡ ይታወሳል። ሆኖም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ትምህርት ጽህፈት ቤት የሥነ ምግባር ኮሚቴ የተማሪዎቹን ጉዳይ በጥልቀት ፈትሾ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ መሰረት ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
ህብር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጁንዲ ሁሴን ተማሪዎቹ ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ ትምህርት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ተማሪዎቹ ወደ ትምህርታቸው በመመለሳቸው የትምህርት ቤቱ መምህራን «አናስተምርም» በማለት ለሁለት ቀን ሥራ አቁመው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ መምህራኖቹ አናስተምርም ያሉበትን ምክንያትም «አስተማሪዎች እየተደፈሩ ለተማሪዎቹ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሊሰጥ አይገባም፤ ጉዳዩ በጋዜጣ የወጣበት ሁኔታ አግባብ አይደለም» በማለት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት የወረዳ ኃላፊዎች፣ ወላጅ እና መምህራን በጋራ በትምህርት ቤቱ፣ በመምህሩ እና በተማሪዎቹ በኩል የታዩ ችግሮች ላይ ምክክር ተደርጎ በሽምግልና መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡ በተማሪዎቹ እና በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ከዚህ በኋላ ችግር እንዳያጋጥም ክትትል እንደሚያደርጉም አቶ ጁንዲ ገልጸዋል፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሽ በእውቀት እንደተናገሩት፤ አጥፍታችኋል ተብለው ከትምህርት ገበታቸው የተባረሩት እህትና ወንድም የነበሩ ሲሆን፤ በኮሚቴው የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተማሪዎቹ ለመባረር የሚያደርስ ጥፋት እንዳላጠፉና ጉዳዩ በደንብ ሊታይ ይገባል ያላቸውን ከግምት በማስገባት ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የወረዳው ኮሚቴ በተማሪዎቹ እና በመምህሩ ተፈፀመ የተባለውን ጥፋት በዝርዝር ስላስቀመጠ የትምህርት ቤቱ አመራሮች በመምህሩ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚችሉም አቶ ማሙሽ አመልክተዋል፡፡ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ሲመለሱ የመማር ማስተማር ሁኔታው ላይ ችግር እንዳይገጥማቸው በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ቤቱ አካላት በቅርበት እንዲከታተሏቸው እና ተማሪዎቹም ችግር የሚገጥማቸው ከሆነ በቀጥታ እንዲያሳውቁ ከተማሪዎቹ ጋርም መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተማሪዎቹ ወደ ትምህ ርታቸው መመለሳቸውን ለማረጋገጥ ባደረገው ማጣራት ተማሪዎቹ ቀደም ሲል መምህሩ ከሚያስተምርበት ወደ ሌላ ክፍል ተቀይረው መማር መጀመራቸውን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
በሰላማዊት ንጉሴ