አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቶ ቀናት ዕቅዱ 300 ሺ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎችን ደንበኛው ለማድረግ አቅዶ በ30 ቀናቱ ውስጥ ተግባራዊ ያደረገው ለ12ሺ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።
የአገልግሎቱ የስትራቴጂና መረጃ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ስዩም ተጫኔ እንደተናገሩት ፣ በ100 ቀናት ውስጥ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ 300 ሺ ደንበኞችን ለማድረስ ከዚህም ውስጥ በ30 ቀናት ለ28 ሺዎቹ ለማዳረስ ቢታሰብም ማከናወን የተቻለው ግን የእቅዱን 46 በመቶ ብቻ ነው።
ዕቅዱ በታሰበው ልክ መሄድ ያልቻለበት ዋናው ምክንያት የግብዓት አቅርቦት እጥረት በማጋጠሙ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ስዩም፣ አሁን ያሉት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በኃይል ብዛት የተጨናነቁ በመሆናቸው የመስመሮቹን አቅም ማሳደግ ይጠበቃል። ይሄ በወቅቱ ባለመፈጸሙ የወሩ ዕቅድ አፈጻፀም ዝቅ ብሏል።
ለመስመሩ ዝርጋታ ዋናው ችግር የትራንስፎርመር፣ የገመድና የመሳሰሉት አቅርቦት አለመኖር መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ግን ችግሩ እየተፈታ በመሆኑ በቀሪው ጊዜ በተሻለ ፍጥነት በመሥራት እቅዱን ለማሳካት እና በዓመቱ በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቋል። ።
እንዲሁም ለማስፋፊያ አራት ቢሊዮን ብር ተጠይቆ ሁለት ቢሊዮን ይለቀቃል ቢባልም እስካሁን ባለመለቀቁ 405 ከተሞችን ለማዳረስ የተያዘው እቅድ መቆሙን ተናግረዋል።
የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ፕሮጀክቶችን ሳይጨምር በተቋሙ አቅም በመሥራት መቶ በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን ለማስወገድም ክረምቱን መነሻ በማድረግ በሁሉም ከተሞች 98 በመቶ ማስወገድ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት በዚህ በኩል እየተሠራ ያለው ሥራ በመጪው ክረምት ያልታሰቡ ችግሮች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2030 ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ ብርሀን ለሁሉም የሚል እቅድ መኖሩን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ለዚህም በመቶ ቀናት ውስጥ በሶላር የሚሠሩ ኃይል ማመንጫዎችን በ12 ከተሞች ለመትከል የተያዘው እቅድ ጥናት ተጠናቆ ጨረታ ወጥቷል። በታሪፍ ማስተካከያ ላይ ለተገልጋዩም ለሠራተኞችም የተሠራው የግንዛቤ ማዳበር ሥራም በመቶ ቀናት እቅድ መካከል ውጤታማ ነበር ብለዋል።
የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በበኩላቸው የፋይናንስ እጥረት ለግብዓት አቅርቦት ዋናው ችግር እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም ግን ሙሉ ለሙሉ ወጪውን መሸፈን ባይቻልም ተቋሙ ያለበትን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ከ12 ዓመት በኋላ የታሪፍ ማስተካከያ ማድረጉ አንድ እርምጃ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ በወቅቱ በመክፈል፣ የኃይል ብክነትን በመቀነስና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቅረቢያ መሰረተ ልማቶችን መንከባከብ ይጠበቅበታል ብለዋል።
እንዲሁም በግብዓት አቅርቦት በኩል ከዚህ በፊት ሙሉ ለሙሉ ያቀርብ ከነበረው ከሜቴክ ጋር የነበረው ግንኙነት መቋረጡንና አዲስ መደራደር በማስፈለጉ በዕቅዱ አፈፃፀም ላይ መዘግየት መኖሩን ጠቅሰው፣ አሁን ግን ጨረታ የማውጣት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል ።
የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን 58 በመቶ ሲሆን፣ 6ሺ905 ከተሞች ደግሞ ኤሌክትሪክ አግኝተዋል፤ አጠቃላይ የደንበኞች ብዛትም 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን መሆኑን ከአግልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ