አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና ባለሀብቱ በቅንጅት ሲፈፀሙ የነበሩት የተደራጀ ሌብነት ከፌደራል ሥነ ምግባርና ከፀረሙስና ኮሚሽኑ አቅም በላይ እንደነበር ተገለፀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም ለጋዜጣው ሪፖርተር ትናንት እንደተናገሩት፤ ሙስናና የተበላሹ አሠራሮች በሀገራችን በመጨመር ላይ ነው። የሙስና ብልሹ አሠራር በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተዋናይነት የተከወነ፣ የተደራጀ ሌብነት በመሆኑ ከሥነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽኑ አቅም በላይ ነበር።
ኮሚሽኑ ብቻውን የሚሠራው ነገር አለመኖሩን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ሕብረተሰቡ፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትና መንግሥት በጋራ ሆነው በመሥራት አስተዋጽዖ ካላበረከቱ ኮሚሽኑ ብቻውን የሚወጣው አለመሆኑን አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በአዋጅ ሲቋቋም ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ከተገኝ የማጣራት የመመርመርና የመክሰስ መብት የበረው መሆኑን አውስተው፣ አሁን ግን ኮሚሽኑ የመጣለትን ጥቆማ በማጣራት ባገኝው መረጃ ተገቢውን ቅጣትና እርምጃ እንዲወሰድ ለሕግ አካል መረጃዎቹን የማቅረብ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስረድተዋ። የኮሚሽኑ አቅም ማስተማር ፣ ግንዛቤ ከመፍጠር ቀድሞ ከመከላከል እና የተረጋገጡ የሙስና ወንጀሎች ሲኖሩ ለሚመለከተው የሕግ አካል ከማቅረብ ያለፈ አለመሆኑን ገፀዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ያከናወናቸውን ኮሚሽነሩ እንደገለፁት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ በሕገ ወጥ መንገድ የተዘረፉ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትር ካሬ መሬት ከዘራፊወች እጅ በመንጠቅ ወደ መሬት በንክ እንዲገባ ማድረግ ችሏል። ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ የተዘረፉ የመንግሥት ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ እንዲሆን አድርጓል። በሌብነትና በብልሹ አሠራር ተዘፍቀው የነበሩ ባለሀብቶችና ባለሥልጣናቶችን ለሕግ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረጉንና ሙስናን የሚታገል ማህበረሰብ ለመፍጠርም የግንዛቤ ሥራ በመሥራት ሚናውን ሲወጣ እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡ አሁን በሀገሪቷ ይፋ እየወጡ ያሉት የሙስና ወንጀሎች ሕብረተሰቡ ሲታገላቸው የነበሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በኢትዮጵያ ለ14ኛ በዓለም ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ በወቀታዊ የሙስናና ብልሹ አሠራሮች ዙሪያ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
በሰለሞን በየነ