– የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የነበረችው ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ትተካለች
– ከ44 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ስደተኞች እንዲመለሱ ተደርጓል
አዲስ አበባ፡- በኢትዮ-ኤርትራ ዳግም ግንኙነት ክፍት የተደረጉ መንገዶች ከትላንት በስቲያ መዘጋታቸውን የዛላንበሳ አካባቢ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡ ለጥያቄያቸው የተሰጣቸው ምላሽም የፌዴራል መንግሥት ፍቃድ ያላገኘ ማንኛውም አካል ማለፍ እንደማይችል ነው፡፡ ቤተሰብ ጥየቃ እንዲሁም ለሥራ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ በተመሳሳይ ከኤርትራም ወደ አገሪቱ የገቡ ዜጎች መመለሻም አሳሳቢ እንደሆነ ጭምር አንስተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያነሳንላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም አስተያየት የማይሰጡባቸው ቀይ መስመሮች እንዳሉ በመግለፅ፤ በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ሲኖር ምላሽ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በትላንትናው ዕለት መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የነበረው የሻከረ ግንኙነት ታድሶ በአሁኑ ወቅት ጠንካራ ወዳጅነት እየተመሰረተ ነው፡፡ ይህንንም የበለጠ ማጠናከር እንዲቻል የመጀመሪያው አምባሳደር አቶ ሰመረ ርዕሶም የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል አዲስ የመተባበርና በጋራ የመሥራት ምዕራፍ ዕውን እንደሆነም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
አቶ መለስ፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት በመሻሻሉ የነበረው የጥርጣሬ ድባብ መወገድ መቻሉ ለአፍሪካ ቀንድ ያስገኘው ውጤት ትልቅ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ ለዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሙሉ ድጋፉን በመስጠት በኤርትራ ላይ የተጣለ ማዕቀብ እንዲነሳና ከጅቡቲ ጋር የነበራቸው ችግር ሊፈታም ችሏል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና እንድትጫወት የረዳት የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆኗና የሠራቻቸው ሥራዎች ያበረከተላት ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ከአገሪቱ አንፃርም ለጀመረችው የለውጥ እንቅስቃሴ ትርጉም ያለው ድጋፍ አስገኝቶላታል፡፡
ኢትዮጵያ ተቀባይነትን ያስገኘላትና ስኬታማ ሥራዎችን ያከናወነችበት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ቆይታ ታኅሣስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በስኬት እንደሚጠናቀቅም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ለሦስት ጊዜ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የነበረችው ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ትተካለች፡፡ በሥራዎቿ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ከማረጋገጥ አልፎ ለቀጣናው ሠላም የሚሆን ትሩፋቶችንም አስገኝታለች፡፡
በዚህም 12 ሺህ 800 የሚደርስ በዓለም አቀፍ መስፈርት ትልቅ ቁጥር ያለው የሠላም አስከባሪ ኃይል ታሰማራለች፡፡ ላለፉት 70 ዓመት በዘለቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም ማስከበር ሂደት ውስጥ ከፍ ብሎ የሚታይ ሚና እንደነበራትም አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሠላም አስከባሪ ኃይል ስምሪት ቀዳሚውን ስፍራ ከመያዟ ባሻገርም ባለው የማስፈፀም አቅምም ትልቅ አስተዋጽዖን ስታበረክት ቆይታለች፡፡ በቀጣይም ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የሠላም ማስከበር የውሣኔ ሃሳብ አቅርባ ተቀባይነት ያገኘች ሲሆን፤ የሠላም አስከባሪ ኃይሎችን አቅም ከመገንባት አኳያም አዲስ አስተሳሰብና አሠራር ለማስተዋወቅ ችላለች፡፡
በመግለጫው የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ ስደተኞችን የተመለከተ ሲሆን፤ ባለፉት ስድስት ወራት ህይወታቸውን በሞት አደጋ ውስጥ ጥለው ባህር አቋርጠው የተጓዙ 44 ሺህ 500 ሕገ ወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ በቀጣይም መንግሥት ለእያንዳንዱ ዜጋው በተቆርቋሪነት እንደሚሠራና ዜጎች ሲቸገሩ የሚረዱበት ብቻ ሳይሆን በአገራቸው ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ለዚህም እያንዳንዱ አካል በያገባኛል ስሜት ሊሠራ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
በፍዮሪ ተወልደ