አዲስ አበባ፦የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ግልጽ ጨረታ በማውጣት ለሁለት የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን አሳወቀ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ በውድድር ላይ የተመሰረተ የአገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ጨረታ በማውጣት ለሁለት የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እነዚህ በጨረታ የሚያሸንፉ ድርጅቶችም ቀደም ሲል በኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማቅረብ በተጠቃሚው ፍላጎትና ተደራሽነት ልክ ለህብረተሰቡ የተለያዩ አማራጮችን ለማቅረብ የሚያግዙ፤ እንዲሁም በሀገሪቱ ተወዳዳሪ የገበያ ሥርዓትን ለማስፈን የሚረዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ውሳኔም የሀገሪቱን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቀጣይ ምዕራፍ ቴክኖሎጂን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የመምራት ዓላማ ያለው የአዲሱ የመንግሥት ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አካል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ በውድድር ላይ የተመሰረተ የአገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር ከአንድ ዓመት በፊት በመንግሥት የተሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገበያ የመክፈት ሂደትን ግልጽ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በዚሁ መሰረት እስካሁን ሃያ ሁለት የሚሆኑ ድርጅቶች በጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳሳዩ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ድርጅቶቹ ያላቸው ልምድ፣ ብቃትና የገንዘብ አቅም መመዘኛ ሊሆን እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፣ የፈቃድ አሰጣጡ የሚመራበት ማዕቀፍ የተዘጋጀ ነው፤ ማዕቀፉ ለህዝብ ቀርቦ አስተያየት ይሰጥበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ የህዝብና የባለ ድርሻ አካላትን አስተያየት ለመሰብሰብና ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም በሚበጁ አሠራሮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ይዘጋጃል፡፡
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በኮሚኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 ነሐሴ 6 ቀን 2011 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ ዋነኛ ተግባሩም ተወዳዳሪ የገበያ ሥርዓትን በማበረታታት የተጠቃሚዎችን ፍላጎትና ተደራሽነት ያሟላ፣ ጥራቱ የተጠበቀ ቀልጣፋ አስተማማኝ እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ያገናዘበ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ እንዲስፋፋ ማድረግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
ኢያሱ መሰለ