በቀድሞ ዘመናት የአሁኖቹ የመናገሻ፣ የወጨጫና የአዲስ ዓለም አካባቢዎች እንደዝነኛው ጨንገሬ ሶኪ እና እንደ ሁኪ ጉላ ባሉት የሜታ ኦሮሞ መሪዎች ስር በባላባትነት የግዛት ወሰን ውስጥ የነበሩ ናቸው። ንጉሰ ነገስት አጼ ምኒልክ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ ዓለምን (የዛሬዋን ኤጀሬ) የጎበኟት በ1874 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ወደ እንባቦ ጦርነት ሲያቀኑ እንደነበር የገዳሙ እና የደብሩ ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ደሳለኝ ብርሃኑ ይናገራሉ። (በነገራችን ላይ የቀድሞውን የአካባቢው ባላባት ፣ ታሪኩንና ቅርሱን ለማስታወስ ሲባል የአዲስ ዓለም ከተማ በማለት አነሳን እንጂ በአሁኑ ወቅት መጠሪያው ኤጀሬ ከተማ ነው። ) አዲስ ዘመን ጋዜጣም በአሁኗ ኤጀሬ በታሪካዊቷ አዲስ ዓለም በመገኘት የከተማዋን ታሪክ እና ቅርስ ለማስቃኘት ወደናል።
አጼ ምኒልክ መጀመሪያ እንጦጦ ላይ በኋላም አዲስ አበባ መቀመጥ ከጀመሩ በኋላ እሳቸውን ተከትሎ በዙሪያቸው የሚኖረው ህዝብ እጅግ በጣም ስለበዛ በአካባቢው የነበረው ጫካ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እየመነመነ ሄደ። ሠራዊቱናህዝቡ ቤቱን የሚሰራውም ሆነ ለየቀኑ የሚያስፈልገውን ማገዶ የሚያገኘው ከዚያው ከጫካው ስለሆነ አዲስ አበባ ከተማ ገናአሥራ ስድስት ዓመት ሳይሞላት በተለይ የማገዶ ችግር እየተባባሰ ሄደ። በዚህም ምክንያት አመራጭ ከተሞች ይፈለጉ ነበር። ከእነዚህ አማራጭ ከተሞች መካከል ደግሞ አዲስ ዓለም አንዷ ነበረች።
ስለከተማዋ ታሪክ እና ስለቅርሶቿም እንዲያስረዱኝ የገዳሙንና የደብሩን ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ደሳለኝ ብርሃኑን አነጋግረናል። ርዕሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ከአዲስ አበባ 50 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። እንደ ቀሲስ ደሳለኝ ገለጻ ታቦተ ማርያም ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ጀምሮ በቤተ መንግሥት አካባቢ እንደቆየችና በዐፄ በዕደ ማርያም ዘመነ መንግሥት መንዝ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ታንፆላት ምስሐለ ማርያም ተብላ በታላቅ ክብር ነበረች፤ በግራኝ መሐመድ ጊዜ ንጉሡ ሲሰደዱ ታቦቷን ከመቅደስ አውጥተው በአካባቢው በሚገኝ ዋሻ ባህታውያን ሲጠብቋት መኖራቸውን ያወሳሉ።
ርዕሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም በ1892 ዓ.ም የተቆረቆረ ገዳም መሆኑን የሚናገሩት ቀሲስ ደሳለኝ ገዳሙ በውስጡ 775 የሀገር እና የሕዝብ ቅርሶችን ያጨቀ ሙዚየም በውስጡ ይዟል። ሙዚየሙ በውስጡ አ ጼ ምኒልክ፣ የባልቻ አባ ነፍሶ ደብዳቤዎች፣ ጠመንጃዎች፣ ከምኒልክ አልጋ እስከ ውሃ መጠጫቸው እንዲሁም ሌላም ሌላም ድንቅ ቅርሶች ይገኙበታል። በነገራችን ላይ የመጀመሪያው የመኪና መንገድ የተዘረጋው ከአዲስ አበባ ወደ አዲስ ዓለም እንደነበር ሰምተናል።
በ1933 ዓ.ም ጣሊያን አዲስ አበባን ለቆ ሲወጣ በነጻነት ባንዲራ ከፍ ብሎ የተውለበለበው በአዲስ ዓለም መሆኑን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። አዲስ ዓለም የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለቤተመንግስትነት ነበር የተገነባችው። የመጀመሪያዋ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ናት ማለት ይቻላል። በኋላ ነው አጼ ምኒልክ ቤተክርስቲያን እንድትሆን የወሰኑት። የቤተክርስቲያኗ ግድግዳዎች ሳይቀር ቅርሶች ናቸው ፤አራቱም ግድግዳዎቹ ስዕሎች ናቸው። ግድግዳው በግምት ወደ ላይ ሶስት ሜትር ወደ ጎን አራት ሜትር ገደማ ይሆናል።
ቤተ መቅደሱ በአራቱም መዓዘን የተለያዩ መንፈሳዊ ስዕለ አድኅኖ፣ እንዲሁም የነጉሠ ነገስት ምኒልክ፣ ንጉሠ ነገሥት ዘውዲቱ እና የልጅ ኢያሱ ምሥሎች ተስለውበታል። የሚደንቀው ሥዕሎቹ በሙሉ የተሰሩት በአንድ ሰው ብቻ መሆኑ ነው። ሰዓሊው አለቃ ሉቃስ ይባላሉ። እኚህ ኢትዮጵያዊ እነዚያን ድንቅ ስዕሎች የሳሉት ቅጠል ጨፍጭፈው ቀለም በመጭመቅ ነው። በሌላ አነጋገር ስዕሎቹ ዘመናዊ ቀለም የሚባል ነገር አልነካቸውም።
ይህንን አይተን፤ ኢትዮጵያ ከመቶ ዓመታት በፊት ዘመናዊውን ቀለም የሚያስንቅ ፈጠራ እና ጥበብ እንደነበራት፣ አሁን ግን ጥበበኛ እንደናፈቃት ሲነገር ያስገርማል። ስለ ጥበብ እና ጥበበኛ ከአነሳሁ አይቀር፤ በአዲስ ዓለም ሙዚየም ውስጥ ከሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች (ደብዳቤዎች) መሃል የሚከተለውን መጥቀስ ግድ ነው። ይህ የምኒልክ አዋጅ በ1901 ዓ.ም የወጣ ነው። የምኒልክን ጥበብ ናፋቂነት ይታይበታል። እነሆ፦”አንተ ጸጉረ ልውጥ … የአውሮጳ ሰው … ባህልህን ሳይሆን ስልጣኔህን በአስቸኳይ ላክልኝ:: ያገር ሰው … አንተ ትውልድ … የአንገትህን ማተብ ሳትፈታ ባህልህን ሳትጥል እንደ ባህር ማዶ ሰው ሰልጥን::” ይህም ምኒልክ ምን ያህል ለስልጣኔ ያላቸውን ቀናኢነት የሚያሳይ ደብዳቤ ነው። እንደ ቀሲስ ደሳለኝ ብርሃኑ ይህ ዋነኛ የሀገርና የቤተክርስቲያን የጀርባ አጥንት የሆነው ቅርስ እንዲጠናከርና ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ለማድረግ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል። በተለይ ለአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርት እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች እድሳትና ማጠናከሪያ የሚውል የገንዘብ፣ የቁስና የሀሳብ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሌላኛው አሁን ቅርሶቹ በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙበት ሁኔታ ለጉብኝትም ሆነ ለአቀማመጥ ምቹ ባለመሆኑ ሳይበላሹና ጥንታዊ ይዘታቸውን ሳይቀይሩ እንዲቀጥሉ ለማድረግና በዘመናዊ መልክ ለማደራጀት የሙያ ፣የቁስ የተጨማሪ ማስፋፊያ ገንዘብም እንደሚያስፈልግ ዋና ጸሐፊው ይናገራሉ።
ሙዚየሙ የቱሪስት መዳረሻነቱን አስፍቶ ከቱሪዝም ዘርፍ በሚገኘው ገቢ ለአገር እና ለዜጎች ጥቅም እንዲያገለግል እንዲሁም ለጥናታዊ ምርምሮች እንዲጠቅም ለማድረግ ለውጭና ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የማስተዋወቅ ሥራ ላይ እገዛ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል። የቤተክርስቲያኒቱ ህንጻ እንዲሁም በቅርስነት የተመዘገቡ ጥንታውያን ቤቶች በጥናት የተደገፈ ጥበቃና እድሳትም እንዲደረግላቸውም ቀሲስ ደሳለኝ አሳስበዋል።
ቀሲስ ደሳለኝ እንዳሉት አፄ ምኒልክ ለአዲስ ዓለም ያላቸውን ጽኑ ፍቅር ለመግለጽ ለቤተ መንግሥትነት ያሰቡትን ሕንጻ ወደ ቤተ ታቦትነት በመለወጥ የቦታውን መንፈሳዊነት ለማስጠበቅ ጥረት አድርገዋል።ከዚህም በላይ በዘመኑ የነበሩ የስልጣኔ ነጸብራቆችን ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በአዲስ ዓለም እንዲገኙ ይሰሩ እንደነበር ይተርካሉ።
በተለይ ከዐፄ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ የቤተ መንግሥትና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሚያሳዩ ቅርሶች የሚገኙባት ደብር መሆኗን የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱ የሚናገሩት ቀሲስ ደሳለኝ የኤጀሬ ከተማ ሕዝብ የአገር እና የሕዝብ ቅርሶችን በመጠበቅ ያደረገው ተግባር አድናቆት እና ምስጋና የሚገባው እንደሆነም ጠቁመዋል።
ማልዶ የነቃ፤ ቀድሞ ያንቀላፋል እንደሚባለው ቀድሞ ነቅቶ የነበረ ከተማ አሁን ስልጣኔ ርቆታል። የሚመለከተው አካልም ከተማዋ ወደ ቀድሞ ዝናዋ እና ስልጣኔ እንድትመለስ እንዲሁም በአዲስ ዓለም ደብረ ጺዮን ማርያም ለሚገኙ ቅርሶች ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርግለት መልዕክታችን ነው። መልካም ዕለተ ሰንበት !
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
አብርሃም ተወልደ