አዲስ አበባ፡- ባለፉት 20 ዓመታት የቆዳ ምርቶችን በማምረት ወደ ውጭ በመላክ የሚታወቀው እና በደብረብርሃን ከተማ ከቀዳሚዎቹ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚጠቀሰው የጥቁር አባይ ቆዳ ፋብሪካ የአካባቢ ብክለት በማስከተሉ መዘጋቱ ተገለፀ፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደገለፁት፣ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ያቋረጠው ፋብሪካ በአካባቢ ብክለት ምክንያት ከነዋሪዎች በተነሳ ተደጋጋሚ ቅሬታ እንዲዘጋ መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡
ፋብሪካው ቀደም ሲል ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረና በአመሰራረቱም ከቀዳሚዎቹ ውስጥ የሚጠቀስ ነበር፡፡ ይሁንና ከከተማው መስፋት ጋር ፋብሪካው ያለበት ስፍራ ዋና የመኖሪያ ማዕከል ሆኗል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ማህበራዊ ግልጋሎት የሚሰጡ ተቋማትና ቤተ እምነቶች በአካባቢው ተስፋፍተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዙሪያው ያሉ አርሶ አደሮች ከአካባቢው የሚመነጨውን ውሃ ለተለያዩ ግልጋሎት የሚጠቀሙ በመሆኑ ፋብሪካው ባስከተለው ብክለት ምክንያት ለተለያዩ የጤና እክሎች ተዳርገዋል፡፡
በዚሁ ምክንያትም የአካባቢው ነዋሪዎችም ለከተማ አስተዳደሩና ሌሎች የመንግሥት አካላት ተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ይህንን መነሻ በማድረግና ተደጋጋሚ ምልከታዎችን በማካሄድ የከተማ አስተዳደሩም ችግሩ እንዲቃለል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ገልፀዋል፡፡ይሁን እንጂ የተደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራዎች ለውጥ ባለማምጣታቸው ፋብሪካውን ለማገድ መገደዳቸውን ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለፃ፤ የፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎችን መስፋፋት የምናበረታታ ቢሆንም ከማህበረሰቡ አኗኗር ጋር ያልተዛመደ ብሎም ለጤና ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎችን የሚለቅ ፋብሪካ ሥራ እንዲሠራ መፍቀድ ህጋዊ ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑ ፋብሪካው ሊታገድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው አሁን ካለበት ቦታ በክላስተር ታቅፎ በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ታቅፎ እንዲሰራ ሐሳብ ቢቀርብለትም፤ ፋብሪካውን ወደ ሌላ ሥፍራ ለማዛወር ሃብት ያስፈልገኛል በሚል ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ፈቃደኛ መሆን አልቻሉም፡፡
መሰል ፋብሪካዎች ከህብረተሰቡ መኖሪያ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገንባት እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ደስታ፣ የቆሻሻ አወጋገዳቸው ሥርዓታቸውም ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ህጉ እንደሚያስገድድ ምክትል ከንቲባው አስታውሰው ይሁንና የጥቁር አባይ ፋብሪካ ይህንን ደረጃ ማሟላት እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ፋብሪካው የሚገኝበት ደብረብርሃን ፋብሪካ ድረስ በመሄድ ተደጋጋሚ ዘገባዎች ማውጣቱ ይታወሳል፡ ፡ በወቅቱ አዲስ ዘመን ሲዘግብ እንደቆየውም ነዋሪዎቹ ባለቤትነቱን ጭምር የማን እንደሆነ ለማወቅ እንደተቸገሩና መፍትሄ የሚሰጥም የመንግሥት አካል ለማግኘት እንደተቸገሩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ጉዳዩ ከዓመታት በፊት የደብረብርሃን ከተማ ከሚገኝበት ሰሜን ሸዋ ዞን አቅም በላይ በመሆኑ ወደ ክልሉ መንግሥት ቢሄድም ውሳኔ ሳያገኝ ቀርቶ ለፌዴራል መንግሥት መላኩም ይታወሳል፡፡
የፌዴራል መንግሥትም ውሳኔ ሳይሰጥ በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱና ነዋሪዎችም ለከፍተኛ የጤና እክልና መልካም አስተዳደር እጦት መንስኤ ሆኖ ስለመቆየቱ አዲስ ዘመን ተደጋጋሚ ዘገባዎች ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
የጥቁር አባይ ቆዳ ፋብሪካ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጉዳዩን ለማጣራት በተደጋጋሚ የእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 8/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር