ከቤቴ ለጉዳዬ ፈጥኜ ለመድረስ ተቻኩዬ ወጥቻለሁ፡፡ ምርጫዬ ከስቴዲየም አራት ኪሎ፣ ሥድስት ኪሎ ከዚያም ማሳረጊያው ሽሮ ሜዳ የሆነ የሕዝብ መገልገያ ታክሲ መያዝ ነበር፡፡ እስከ 1፡20 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ ለመድረስ አቅጄ ብወጣም ረጃጅም ሰልፎቹ ተስፋ የሚሠጡ አልነበሩም፡፡ ተደርድረው የቆሙት ሰዎች ከአሁን አሁን ታክሲ ይመጣል በሚል ሥሜት አይናቸው ላፍታ አይቦዝንም፤ያማትራል፤ይቃኛል፤አሻግሮ በመምጫው በኩል ይወረወራል፡፡ ግን አልመ ጣም፡፡ ደቂቃዎች ተቆጠሩ፡፡ በሰልፉ ከተኮለኮሉት ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ የለበሱ ተማሪዎች ናቸው፡፡ የሌሎችም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
ከቆይታ በኋላ ተራ አስከባሪ የነበረው ወጣት የኮንትራት አገልግሎት ከሚሠጡት ትናንሽ ታክሲዎች አንዱን ጠራ፡፡ ሹፌሩም እርሱም በላዳ ካልሄዳችሁ በሚል ተሳፋሪውን ይወተውቱት ጀመር፡፡ በሕዝብ ታክሲ ሦስት ብር የሚከፈልበትን በሀምሳ እና በመቶ ብር ካልሄዳችሁ በሚል፡፡ ከኋላ ከተሰለፉት አንዱ ‹‹ለዚህ ሲሉ እኮ ነው የህዝብ ታክሲዎችን እንዲዘገዩ የሚያደርጉት›› አለ በንዴት፡፡ በአብዛኛው ሰው ምንም ምላሽ ሣይሰጥ መጠበቁን ቀጠለ፡፡
እየዘገዩ የሚመጡ ታክሲዎችን ተሣፋሪው ተንሰፍስፎ ይቀበላል፡፡ ጢም እስኪሉ ድረስ ይሞላል፡፡ ልክ እንደ እቃ ሰው በሰው ላይ ይደረባል፡፡አሥራ ሁለት አካባቢ ሰው የጭነት ልካቸው የሆኑ ታክሲዎች እስከ አስራ ሰባት ሰው ድረስ ይጭናሉ፡፡ በጫኝም በተሣፋሪም ዘንድ ሕጋዊ እውቅናና ፈቃድ ያለው ሊሆን ተቃርቧል፡፡ ሽርፍራፊ የሣንቲም መልስ ለተሣፋሪ መመለስም እንዲሁ፡፡ ጉዞውን ጨርሶ ሲወርድ ‹‹ሃምሣ ሣንቲም መልስ ሥጠኝ?›› በሚል የጠየቀ ሰው በታክሲ ረዳቱ ብቻ ሣይሆን በተሣፋሪም ጭምር ሊመናጨቅ ይችላል፡፡
ወጣት አለማየሁ ቢተው ወደ ሽሮ ሜዳ ለመሄድ ተሰልፈው የታክሲ መምጣትን ከሚጠባበቁ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በታክሲ አገልግሎቶች አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮች በዋናነት ምን ይሆኑ? ሥንል ትዝብቱን እንዲያካፍለን ጠየቅነው፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ የታክሲዎች የረጅም ጊዜ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጾ፤ በሕዝብ ትራንስፖርት አካባቢ የሚስተዋለው ችግር በአንድ አካል የሚፈጠርም የሚፈታም አይደለም፡፡ በቅርቡ የተፈጠረም አይደለም፡፡ የቆየ ነው፡፡ አሁንም አለ፡፡ ለመቅረፍም ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡
ወጣት ዓለማየሁ እንደተናገረው፤ በትራንስፖርት ዘርፉ በዋናነት የሚታየውና ኅብረተሰቡን የሚያማርረው ችግር አሰልቺው ወረፋ ነው፡፡ የታክሲ ሥራ በተሰማሩት አካላት ላይም ያለ ታሪፍ መቀበል፣ከልክ በላይ መጫን፣ አቆራርጦ መጫን፣ለተሳፋሪ መብት አለማሰብ ጥቂቶቹ ችግሮች ናቸው፡፡ በተሳፋሪዎች በኩል እንዲከፍሉ የተጠየቁት ታሪፍ ተገቢ እንዳልሆነ እያወቁ መክፈልና መብትን አውቆ አለማስከበር መሰረታዊ ችግሮች ናቸው፡፡ በመንግሥት በኩል ተራ ለማስጠበቅ ያደራጃቸው፣ መንገድ ሥምሪት ተቆጣጣሪዎችና የትራፊክ ፖሊሶች አካባቢ ሰፊ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ በጥቅም መጋራት ተሳስረዋል፡፡ ብዙዎቹ የሕዝብ አገልጋይ አይመስሉም፡፡
በትራንስፖርት ዘርፉ የተሰማሩ አንዳንድ አካላት ያልተገባ ጥቅም የሚያገኙበትን መንገድ ብቻ የሚያሰሉ ይመስለኛል ሲል ይገልጻል፡፡ መፍትሔውን ከአንድ አካል መጠበቅ አይቻልም፡፡ እንደውም ዋናው ሥርዓት ማስያዝ የሚገባው ተሳፋሪው ራሱ ነው፡፡ ወቅታዊ መረጃ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን በተገቢው መብቱን ያስጠብቃል ግዴታውንም ይወጣል ብሏል፡፡
ከቦሌ እስከ ሜክሲኮ በሚጭን ሚኒባስ የሕዝብ መጠቀሚያ ታክሲ በሾፌርነት በመስራት ላይ ያገኘነው አቶ ታደሰ ወንድሙ እንዳሉት፤ ችግሩ በመጠን ይለያይ ይሆናል እንጂ በሁሉም የሕዝብ መገልገያ የከተማ ትራንስፖርት አካባቢዎች ያለ ነው፡፡ በአንድ ሥራ ውስጥ በርካታው ሕግ የማያከብር ከሆነ ሕግን የሚያከብር በልቶ መኖር፣ ሰርቶ ልጅ ማሳደግና ቤተሰቡን ማስተዳደር ይሳነዋል ሥለዚህ ለሕገ ወጥ ሥራ ይዳረጋል፡፡ ሕግን አክብሮና ፈርቶ ከሚኖርና ከሚሰራው ይልቅ በድብብቆሽ የሚሆነው ይበልጣል፡፡
ተገልጋዩም ወዶና ፈቅዶ አይደለም በትርፍ የሚጫነው፡፡ መንገድ ይጨናነቃል፡፡ ካሰበው ላይደርስ ይችላል፡፡ ያለው አማራጭ ሕገ ወጥም ቢሆን የተሻለውን ለመምረጥ ይገደዳል፡፡ እውነተኛ ለውጥ የሕዝቡ ወይም የተገልጋዩ አስተሳሰብ ሲለወጥና ትራፊክ ፖሊስ፣ ሾፌሩ፣የመንግሥት አካላትና ሌላውም የሕዝብ አገልጋይነት ሥሜቱ ከዕለታዊ ጥቅሙ በልጦ ራሱን ለሕዝብ እስከመስጠት ካላሰበ ችግሩ የሚቀረፍ አይመስለኝም ሲል ተናግሯል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ የዚህ አይነት ችግሮች መኖራቸውን አውቆ በተደጋጋሚና በየጊዜው የማሻሻያ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በቅርቡ የተቋሙ የመቶ ቀን ዕቅድ አስመልክተው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት፤ በየደረጃው በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር፣መመሪያና የአሰራር ደንቦቹን በማሻሻል፣ በአዲስ አበባ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር በተለይም በመንገድ ግንባታና ጥገና፣ በመንገድ ትራንስፖርት ዙሪያ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ጭምር ለመቅረፍ መቶ ቀን ተቆርጦ እየተሰራ ነው፡፡
ችግሮቹ ከኅብረተሰቡ የእለት ከእለት ተግባር ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነዋል፡፡የሕዝቡን እሮሮ ጆሮ ሰጥቶ በማድመጥና በመቅረፍ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማታችን እንዲፋጠን ያለመ ተግባር በመቶ ቀናቱ ይከወናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በትራንስፖርቱ ዘርፍ በተለይም የሕዝብ ምሬትና እሮሮ በሚበረክትባቸው አካባቢዎች ያሉትን ችግሮች የመቶ ቀናቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እቅድ መፍትሄ ያስገኝ ይሆን ? ስንል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ አሸናፊ ጋዕሚ ጠይቀናቸዋል፡፡ እርሳቸውም በበኩላቸው፤ቋሚ ኮሚቴው የተግባር እቅዱን አንድ በአንድ የገመገመው መሆኑን ገልጸው ክፍተቱንና መካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች በተገቢው አመላክቷል ብለዋል፡፡
በመሰረተ ልማት ማስፋፋት፣ በመንገድ መዘጋት በተለይም በመግቢያና በመውጫ ሰዓት፣ ከቀላል ባቡሩ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ቋሚ ኮሚቴው በእቅዱ ላይ የተመለከታቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ነገር ግን የተቀመጠው እቅድ እንደ ትራንስፖርት አቅርቦትና ሥምሪት ያሉ ችግሮችን በተገቢው የሚፈታ አለመሆኑ ተገምግሟል፡፡ በመሆኑም ከቀላል ባቡሩ የመለዋወጫ አቅርቦት ጋር ያጋጠመውን ችግር ጨምሮ ሌሎቹም በዚህ በጀት ዓመት መፍትሔ እንዲያገኙ ቋሚ ኮሚቴው አቋም ይዟል ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘውም በምክር ቤቱ የታመነባቸውን መመዘኛዎች ተከትለው በዘርፉ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ መመዘኛዎቹ ምንድን ናቸው? በምንስ ላይ ያተኩራሉ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ውጤትን መሰረት ያደረገ ምዘና ይካሄዳል፡፡ በዋናነትም በባለብዙ ዘርፍ ተግባራት፣በመንግሥት የፋይናንስ በጀት አጠቃቀምና በኦዲት በተሰጡ አስተያየቶች ተፈጻሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰሩና ያልተሰሩ ተግባራትን ለይቶ ይፈትሻል፡፡ በመመዘኛዎቹም መሰረት እንደየጥረታቸው ከፍተኛ ፣መካከለኛና ዝቅተኛ በሚል ይለያል፡፡ ለእያንዳንዱ እንደየጥረቱ እውቅናም ይሰጣል፡፡ ይህ ሲሆን የህዝብን ብሶት አዳምጦ የሚሰራውና የማይሰራው ይበልጥ ይለያል፤አድሏዊ አሰራሩም ይቀረፋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2011
በሙሐመድ ሁሴን