አዲስ አበባ፡- በቻይና ሀገር የተመረቱና 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሁለት መቶ የባቡር ፉርጎዎች እስካሁን ድረስ ወደ አገር ውስጥ እንዳልገቡ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።
የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሰርካ ሰሞኑን ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ የባቡር ፉርጎዎቹን ከቻይናውያኑ ለመግዛት ሲታሰብ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማምጣት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደነበር ገልፀዋል። ከዚሁ የባቡር ግዢ ውስጥ ከ30 አስከ 35 በመቶ የሚሆነውን በአገር ውስጥ በማምረት ለመሸፈን በመንግሥት በኩል አቅጣጫ መያዙንም ጠቅሰዋል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ 35 በመቶ የሚሆነውን የባቡር ፉርጎ ሥራ ለማከናወን የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን / ሜቴክ/ በንኡስ ተቋራጭነት ለመስራት በወቅቱ ከዋናው የቻይና የባቡር ፉርጎ አቅራቢ ድርጅት ውል ማሰሩን ዋና ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል። ኮርፖሬሽኑ ለባቡር አቅራቢው ድርጅት የሚጠበቅበትን ክፍያ በወቅቱ መፈፀም እንዳልቻለና በዚህም ምክንያት ሁለት መቶ የሚሆኑት ኮንቴነር ጎታች የባቡር ፉርጎዎች ወደአገር ውስጥ ሳይገቡ እንደቀሩም ጠቁመዋል።
የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ መዋቅር እንደ አዲስ እየተዋቀረ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በባቡር መስክ የገቡበት ሁኔታ ብዙም ውጤት ያላመጣ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ ውስጥ ባቡርን በሚመለከት በባለቤትነት የሚመራ አካል ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱንም አስታውቀዋል።
የቻይናው ባቡር አቅራቢ ድርጅት ከሁለት መቶዎቹ ፉርጎዎች ያገኘው ክፍያ አለመኖሩንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀው፤ የባቡር ፉርጎዎቹን ወደአገር ውስጥ ለማስገባት መንግሥት 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላሩን እንዲሸፍንለት መጠየቁን ተናግረዋል።
ማህበሩ የባቡሩ አንቀሳቃሽ ከመሆኑ አኳያና የፉርጎዎቹ ወደ አገር ውስጥ በቶሎ መግባት በወደብ አካባቢ የሚታየውን የኮንቴነር ክምችት የሚያቃልል በመሆኑ መንግሥት ለጉዳዩ መላ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር በጥር ወር 2010 ዓ.ም በቻይናዎቹ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን /CCECC/ እና ባቡር ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /CREC/ ጥምረት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን የአገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ በማቀላጠፍ ረገድ የድርሻውን እየተወጣ ቢገኝም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አደጋና ስርቆት እየፈተኑት ይገኛል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 8/2012
አስናቀ ፀጋዬ