-ከሩብ ዓመቱ ገቢ የመሰብሰብ ዕቅዱ ከመቶ ፐርሰንት በላይ አሳክቷል
አዲስ አበባ፡- የገቢዎች ሚኒስቴር ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በሩብ ዓመቱ ባደረገው ክትትልና ፍተሻ በሀሰተኛ ማንነት ላይ ተመስርተው ከፍተኛ የታክስ ማጭበርበር ሲፈጽሙ የነበሩ 166 ህገወጥ ድርጅቶችን ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አሳውቋል። በሩብ ዓመቱም 56 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 57 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጿል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት ባለፈው ዓመትም በሀሰተኛ ማንነት ላይ የተመሰረተ የታክስ ማጭበርበር የፈጸሙ 124 ድርጅቶች ይፋ መደረጋቸውን አስታውሰው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተደረገው ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ አምና ከተገለጹት ውጭ 166 ህገወጥ ድርጅቶች መለየታቸውን አሳውቀዋል።
ድርጅቶቹ ዕቃ የማይሸጡና አገልግሎት የማይሰጡ፣ በሀሰተኛ ማንነት ላይ የተመሰረቱና በተጨባጭ የሌሉ ነገር ግን ልክ እንደዕቃ አቅራቢና አገልግሎት ሰጪ በመሆን ደረሰኝ እያተሙ የሚሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ድርጅቶቹ የያዙት ሀሰተኛ መጠሪያና አድራጎታቸውም ጭምር ተለይቶ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን እነዚህ ሀሰተኛ ማንነት ያላቸው ድርጅቶች ደረሰኝ መሸጣቸው ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ ደረሰኝ ከሚገዙ አካላት ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር የተለያየ መልክ ያላቸው ማጭበርበሮችን በመፈጸም በህዝብና በሀገርን ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት ማድረሳቸውን ሚኒስትሯ አስረድተዋል።
በእነዚህ ህገ ወጦች ላይ ክትትልና ምርመራ በማድረግ የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ጋር በመተባበር አመርቂ ሥራ መስራታቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ በቀጣይም በከፍ ተኛ ሁኔታ ክትትላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። ህገወጦችን ሥርዓት የማስያዝና ህጋዊ የሆኑትን የማጠናከርና የማበረታታት ሥራ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በሩብ ዓመቱ 56 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 57 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሰብሰብ እንደቻለና በዚህም የዕቅዱን 102 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ገልጸዋል። ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ12 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ወይም የ29 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ለገቢ አሰባሰቡ መሻሻል ከምንም በላይ ግብር ከፋዩ እራሱ ባገኘው ግንዛቤ ሃላፊነቱን የመወጣት ፍላጎት ማሳየቱ እንዲሁም የዘርፉ አመራሮችና ሠራተኞች ከመደበኛ የሥራ ጊዜያቸው ውጭ የእረፍት ጊዜያቸውን በመጠቀምና አምሽተው በመስራት ጭምር የተመዘገበ ውጤት መሆኑን ወይዘሮ አዳነች አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 8/2012
ኢያሡ መሰለ