የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ተማሪዎች የሚማሩበት፣ የሚመራመሩበትና እውቀት የሚያፈልቁበት ተቋም ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ይህ ተቀይሮ በዘር በመከፋፈል ጸብ የሚስተናገድበት ሜዳ ሆኖ ታይቷል፡፡ በውስን ተማሪዎች የሚፈጠረው አለመግባባት ተማሪዎችን ከሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት እያስተጓጎለ ነው፡፡
ተማሪዎች የመቻቻልና የመከባበር እሴቶችን በመጠበቅ የጋራ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር እንዳለባቸው የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይናገራሉ፡፡ በህግ የአራተኛ ዓመት ተማሪው ዓሊ ኢብራሂም፤ ‹‹በአፋር ክልል ዘረኝነት የለም፡፡ ከየትኛውም ክልል የተገኘ ህዝብ አፋር ላይ የሚስተናገደው እኩል ነው፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችም ይከባበራሉ፣ የዘር ክፍፍል በአፋር ክልልም በሰመራ ዩኒቨርሲቲም የለም›› ሲል ይናገራል፡፡ ይህም በዩኒቨርሲቲው ሰላም እንዲሰፍንና የሰላም አምባሳደር ሆኖ እንዲመረጥ እንዳስቻለው ይመሰክራል፡፡
በግቢው አልፎ አልፎ ችግሮች እንደሚገጥሙና አለመግባባቶችም እንደሚከሰቱ የሚናገረው ተማሪ አሊ፤ እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ በውይይት እንደሚፈቱም ይጠቁማል፡፡ ‹‹ተማሪዎች በእኩል አይን ይተያያሉ፣ በመቻቻል፣ በመተማመንና በመከባበር በአንድነት ይኖራሉ፡፡ ትንሿ ኢትዮጵያም ተምሳሌት በግቢያችን ይታያል›› ሲልም ይገልጻል፡፡ መቻቻልና መከባበር የአፋር ክልል ህዝብ ባህል መሆኑንም ይጠቁማል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ሰላምን ማስቀጠል የተቻለው እኩልነት፣ መቻቻልና መከባበር በመኖሩ መሆኑን የሚገልጸው ተማሪ ጀማል፤ ይህንን መልካም ተሞክሮ ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሊጋሩ እንደሚገባ ይናገራል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላም መሆን በሁሉም አካባቢዎች ሰላም እንደሰፈነ ይቆጠራል የሚለው ተማሪ አሊ፤ የአንድ አካባቢ ተወላጅ በተመደበበት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተንቀሳቅሶ ትምህርት መገብየቱ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች በሰላም ከተማሩ ቤተሰቦቻቸው፣ ዘመዶቻቸውና የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላም ይሰማቸዋል፡፡ የአፋር ክልል ህዝብም በሄደበት በሰላም በፍቅርና በመቻቻል ለመኖር ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መስፈንም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ይላል፡፡
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ሲቪል ኢንጂነሪንግ አራተኛ ዓመት ተማሪና የሰላም ፎረም ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ጀማል ሐሰን፤ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ ሆኖ መቀጠሉን ይናገራል፡፡ ተማሪዎች ከመምህራንና ከአመራሩ ጋር ቅርብና ግልጽ ናቸው፡፡ አመራሮች ከተማሪዎች ጋር በመነጋገርና ያለውን እጥረት በመመልከትም ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጡ ይገልጻል፡፡
በጊቢው በእጥረት የሚነሱ የውሃ አቅርቦት፣ የመብራት አገልግሎትና ሌሎች ችግሮች ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ በመጠቆም፤ ‹‹ከአመራሩ ጋር እጅና ጓንት ሆነን ስለምንሠራ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ ነው›› ሲልም ይገልጻል፡፡ የግቢው ሰላም ከደፈረሰ ተረጋግቶ ለመማርም ሆነ እውቀት ለመገብየት አዳጋች ነው፤ ሰላም በመስፈኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ አድርጓቸዋል፡፡
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የተወከሉ ተማሪዎች በትምህርት፣ በመኝታ ክፍልና በገበታ አብረው እንደሚቋደሱ የጠቆመው ተማሪ ጀማል፤ ‹‹የአፋር ክልል ተወላጅ ብሆንም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ጋር ላለፉት ዓመታት በግቢው ያሳለፍኩት ቆይታ የሌሎች አካባቢ ልጆችን ባህል፣ አኗኗርና ስነ ልቦና እንዳውቅ ረድቶኛል›› ሲል ይገልጻል፡፡
አለመግባባት በማንኛውም ጊዜ ሊፈጠር እንደሚችል የሚናገረው ተማሪ ጀማል፤ ቅድመ ጥንቃቄ እንደሚወሰድም ይጠቁማል፡፡ አለመግባባቶች ሲከሰቱ ለሰላም ፎረም ህብረት አባላቱ መረጃ ስለሚደርስ አደጋ ሳይደርስ በህብረቱ የሚፈታው በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ ሲደረግ፤ የማይቻለውን ደግሞ ለበላይ አመራሮች ሪፖርት እንደሚደረግም ይገልጻል፡፡ ሌሎችም ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ መቻቻልና መከባበርን፣ ተግባብቶ መኖርን፣ መምህራንና አመራሩ ያላቸውን ቅርበት እና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ልምድ ሊጋሩ እንደሚገባ ይመክራል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አሊ ሁሴን እድሪስ እንደሚሉት፤ ተማሪዎቹ የመጡበት ዓላማ ላይ አተኩረው ስኬታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይታወክ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ውስጣዊ ጉዳዮችን በመለየት ይፈታሉ፡፡ ተማሪዎች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና እንዲግባቡ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ይካሄዳሉ፡፡ ሀገራዊ አንድነትን በማስጠበቅና በመቻቻል መዝለቅ እንዲቻል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት በታዋቂና ታላላቅ ሰዎች ምክክር ይደረጋል፡፡
ሰላማዊ የማስተማር ሂደቱን ሊያደናቅፉ የሚችሉ የተለያዩ ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ቢሆንም ተማሪዎች በተደራጀ መንገድ ዓላማቸውን የሚያሰናክል ሁኔታ እንዳይከሰት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ተማሪዎቹ የሚታወቁት በሰላማዊነታቸው ነው፡፡ በሰለጠነ መንገድ ፍላጎታቸውን የመጠየቅ ባህል አላቸው፡፡ ብዙ ችግሮች ቢኖሯቸውም በቅርበት በመወያየት ሊፈቱ የሚችሉት ፈጣን ምላሽ ይሰጣቸዋል፣ በጊዜ ሂደት መፈታት የሚችሉትንም በመግባባት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ በተሻለ ሁኔታ እንዲካሄድ አስችሏል፡፡
ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉ ነገሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ስሜትን የሚጎዱ ነገሮች እንዳይከሰቱም ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ እንደ አንድ ቤተሰብ ልጆች እየተያዩ እንዲኖሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
በዘላለም ግዛው