አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የገቢ አሰባሰብ ላይ የታክስ መሰረት መጥበብ ዋነኛ ችግር እየሆነ መምጣቱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በአገሪቱ ስር የሰደደ የተደራጀ ሌብነት፣ ታክስ ስወራ፣ የኮንትሮባንድ መስፋፋት እና ሌሎችም ጥፋቶች ለአገሪቱ ገቢ መቀዛቀዝ ምክንያት ሆነዋል።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ የታክስ መሰረት መጥበብ ግብር የሚከፍል ህብረተሰብ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የሚመጣ ነው፤ የታክስ መሰረት ሲጠብ ደግሞ ህቡዕ ኢኮኖሚ እንደሚስፋፋ አመልክተዋል፡፡
በህገወጥ ድርጊት የተሰማራና ግብር የማይከፍል ህብረተሰብ በርካታ በመሆኑ የሚሰበሰበው የግብር መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ የሚሰበሰበው ገቢ እየቀነሰ መጥቶም ከአገራዊ አጠቃላይ ምርት ያለው ድርሻ 10 ነጥብ ሰባት በመቶ ብቻ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ከሰሀራ በታች ካሉ አገራት ግርጌ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በግብር ሰብሳቢውና የታክስ ፖሊሲ አውጪ ድክመት ቀዳሚውን ድርሻ ቢወስድም፤ በአገሪቱ ስር የሰደዱ ትልልቅ የተደራጁ ሌብነቶች፣ ታክስ ስወራ፣ የተደራጀ ኮንትሮባንድ ወንጀሎች መስፋፋታቸው እና ሌሎች የሚታዩ ጥፋቶች ለአገሪቱ ገቢ መቀዛቀዝ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የግብር መሰረቱ ካልሰፋና ህብረተሰቡ ግብርን በትክክል ካልከፈለ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደማይቻልም አመልክተዋል፡፡
የገቢ አሰባሰቡ እስከአሁን በብዙ ችግሮች ያለፈና አሁንም ተግዳሮቶቹ ባሉበት መቀጠላቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ የታክስ ገቢ አሰባሰብ ላይ ያለው የታክስ ሥርዓቱ እና የገቢ አሰባሰብ ሥራው ደካማ መሆን ዘርፉ ለህገወጥ ሥራ ተጋላጭ እንዲሆን ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ የገቢ ማሰባሰብ ዘርፉ ችግሮች ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው በየጊዜው አዳዲስ ሥራዎችን የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
‹‹ግብር የመክፈል ግዴታውን ተወጥቶ መብቱን የሚጠይቅ ማህበረሰብ መፍጠር ይገባል›› ያሉት ሚኒስትሯ፤ ግብርን በአግባቡ የማይከፍል አካል በራሱ ፈቃድ የአገር ሀብት እንዲሰረቅ ከመፍቀድ የማይተናነስ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የተደራጀ ሌብነት፣ ኮንትሮባንድ፣ ግብር ስወራ፣ ማጭበርበር እየተስፋፋ መምጣቱ የህግ ተገዥነትን እያዳከሙ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ለረዥም ጊዜ የተለመዱ ህገወጥ ተግባራትን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ ባይቻልም በህግ የሚመራ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት መፍጠር እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡
ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2011 ዓ.ም ሚኒስትሩ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለመሰብሰብ ካቀደው ከአገር ውስጥ ገቢ እና ከጉምሩክ ተያያዥ አገልግሎቶች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ አልሰበሰበም፡፡ ከጉምሩክና ተያያዥ አገልግሎቶች ከስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ አልቻለም፡፡ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደው 28 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ መሰብሰብ የተቻለው 25 ነጥብ 62 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ መሰብሰብ የነበረበት ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ታክስ አልተሰበሰበም፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
በሰላማዊት ንጉሴ