በኢትዮ-ኤርትራ መካከል ሰላም በመስፈኑና ስጋት በመወገዱ ፣ በመከላከያ በተካሄደው ሪፎርም ስድስት የነበሩት ዕዞች ወደ አራት ዝቅ በማለታቸው በሰሜን ድንበር አካባቢ የነበረውን የተወሰነው የመከላከያ ሰራዊት ወደ ሌሎች የኢትየጵያ ክፍሎች የማንቀሳቀስ ስራ እየተሰራ መሆኑን በቅርቡ የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡
የልዩ ዘመቻዎች ሀይል አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሞላ ሀይለማርያም፣ በኤርትራ በኩል ያለው ስጋት በመወገዱ ምክንያት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከነበረው ሰራዊት የተወሰነው ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሰው ህዝቡ ያለ ስጋት መኖር እንዲችልና የሜጋ ፕሮጀክቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በብዛት ተሰባስቦ የሚገኘውን የመከላከያ ሀይል ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የማንቀሳቀስ ስራዎች የሚሰሩባቸው ምክንያቶችም የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ሁኔታ በአብዛኛው የተሻለ ሁኔታ በመድረሱ፣የሁለቱ ህዝቦችና መንግስታት የሰላም ፍላጎታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ፤ የክልሎችን የጸጥታ ሀይሎች አቅም ለማጠናከር፣ የሁሉንም የአገሪቱ ክፍሎች ደህንነት ለማስጠበቅ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ይህ ማለት ግን ከባድሜና ሌሎች አካባቢ ሰራዊቱ ሙሉ ለሙሉ ይወጣል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፣በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ሊገጥም የሚችለውን የጸጥታ አደጋ መከላከል በሚያስችል መልኩ አሰፋፈሩ ተወስኖ ወደ ስራ መገባቱን ሌተናል ጀነራል ሞላ ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት ሰራዊቱን ሲያንቀሳቅስ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ገምግሞና ሌላ ዓላማ የለውም የሚል እምነት ስላለኝ እንደ ትልቅ ስጋት አላየውም የሚሉት የቀድሞው አየር ሀይል አዛዥ ሜጀር ጄነራል አበበ ተክለሀይማኖት፣ ነገር ግን ስጋት አላቸው፡፡
‹‹ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ነገ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ባህሪውን አውቀዋለሁ ፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መናገር የሌለበት ቢሆንም አሁንም በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ እንደፈለገ ነው እየተናገረ ያለው›› የሚሉት ሜጀር ጄነራል አበበ፤ ከኤርትራ ጋር ሙሉ ለሙሉ ሰላም መጥቷልና ሰራዊት ላንቀሳቅስ ማለቱ ተገቢ አይደለም ሲሉ ሞግተዋል፡፡
‹‹ሌሎቹ እንደሚሉት የእኛን ጠቅላይ ሚኒስትር የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እየመራው ነው የሚል እምነት ባይኖረኝም፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ግን እንደፈለገ እንዲናገር መፈቀድ የለበትም የሚል እምነት አለኝ፡፡ እርግጥ ነው ሙሉ ለሙሉ ሰላም ከተፈጠረ ድንበሩ በሚሊሻም ሊጠበቅ ይችላል፡፡ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ተማምኖ ሰራዊትን ማንቀሳቀስ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ ከህወሓት ጋር ባላቸው ቁርሾ ምክንያት ስጋት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
‹‹ሌሎቹ ወገኖች ሰራዊቱ መንቀሳቀስ የለበትም የሚሉትና ስጋት የፈጠረባቸው ከጥርጣሬና ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ካላቸው የሻከረ ግንኙነት ጋር አስተሳስረው ነው ፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ባድመ ሲወረር ሚሊሻ ብቻ ነው በአካባቢው የነበረው፡፡ እዚህ ላይ ጥንቃቄ አድርጎ የተከማቸ ሰራዊት ካለ ወደ ሌላው ማንቀሳቀስ ችግር የለውም›› ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት መንግስት ዋና ስጋቴ ነው የሚለው ከውጭው ይልቅ አገር ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የውጭው ስጋት የአገሪቱ ውስጣዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የሚመጣ ነው›› የሚሉት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፣በተለያዩ ግለሰቦች አቀናባሪነትና ፈጣሪነት የጎሳ ግጭት የሚመስል ግን ደግሞ መደበኛ የሰራዊት ውጊያ አይነት ክስተት እየታየ ነው፡፡ ለምሳሌ ሞያሌ የተደረገውን ውጊያ ማየት ይቻላል፡፡ይህ የጎሳ ግጭት ወይንም የቦረና ኦሮሞና የገሪ ሱማሌዎች ውጊያ አይደለም፡ ፡ምክንያቱም የሚጠቀሙበት መሳሪያና የውጊያው አይነት ፈጸሞ የጎሳ ግጭት አለመሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ
ሰላም የማስፈንና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ውስጣዊ ስጋታችን ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ይህን ስጋት ለማስወገድ ደግሞ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ሀይል አንስቶ ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍል ማሰማራት እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ሰፍሮ የነበረው ሰራዊት የማንቀሳቀስ ርምጃ ስጋት ሊፈጥር የቻለበት ምክንያት አንደኛው የኢትዮ-ኤርትራን ግንኙነት የተፈጠረውን ሰላም በመጠርጠር ሊሆን ይችላል፡፡ መነሻውም ‹‹በቀን እባብ ያየ ለሌት በቅርፊት ይሸሻል›› እንደሚባለው ተደጋጋሚ የሆነ አለመተማመኖች ስላሉ፣አሁንም ከኤርትራ በኩል ጦርነት ስለሚነሳብን ሰራዊቱ እዚህ አካባቢ መነሳት የለበትም ከሚል ቅን አስተሳሰብ የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ኤርትራ ኢትዮጵያን በጦርነት አትፈልጋትም ነው ያሉት፡፡
ምክንያቱም ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላማቸውን ዋጋ ገና እያጣጣሙት ነው፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም ተጧጡፏል፡፡ሌላው ኤርትራ ሰላም እየፈጠረች ያለችው ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከጂቡቲና ከሶማሊያም ጭምር ነው፡፡ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳም ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና ተጫውታለች ሲሉ ነው ኤርትራ የኢትዮጵያ ስጋት አለመሆኗን ያስረዱት፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ግን ሰራዊቱ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል መንቀሳቀስ የለበትም የሚሉት ወገኖች የራሳቸውን ድብቅ ፍላጎት ሊያስፈጸሙ በማሰብ ነው ይላሉ ሌተናል ጄነራል ባጫ፤ እዚህም እዚያ ብሄር ብሄረሰቦችን ለማጋጨት የሚፈልጉ ሰዎች ሰራዊቱ ወደ ሌሎች አገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀስ ከሆነ የማጋጨት ዕድሉ አይኖራቸውም፡፡ ከዚህ ተነስተው ሰራዊቱ መነሳት የለበትም ሊሉ ይችላሉ፡፡ስጋቱ ከማንኛውም ሆነ ከየትኛውም ወገን ይነሳ ሰራዊቱን የማንቀሳቀሱ ውሳኔው ግን በጣም ትክክለኛና አገራችን ውስጥ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ የተወሰደ ዕርምጃ በመሆኑ ማንንም ስጋት ውስጥ የሚጥል አይደለም በሚል ሃሳብ አላቸው፡፡
‹‹የመከላከያ ሰራዊት ትግራይ ላይ የሰፈረው ድንበሩን እንጂ ማንኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ለመጠበቅ አይደለም›› ያሉት ሌተናል ጄነራሉ፣ሰራዊቱን ስጋት ወደ አለባቸው አካባቢ አስገብቶ ሰላም እንዲያመጣ ማሰማራት ተገቢና ኃላፊነት የተሞላበት ርምጃ ነው፡፡እንዲያውም ዘግይቷል ብለዋል፡፡
ሚያዝያ 28 ቀን 1990 ዓ.ም የተቀሰቀሰው የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ተከትሎ ሰራዊቱ ላለፉት 20 ዓመታት ያህል በድንበር አካባቢ ሰፍሮ ቆይቷል። አሁን የሁለቱ አገሮች መሪዎች የፈጠሩት ግንኙነት በስጋት ተወጥሮ የነበረው አካባቢ እፎይታ አግኝቷል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
በጌትነት ምህረቴ