አዲስ አበባ፡- በተፈቀደላቸው ቦታ ላይ ብቻ በህጋዊ መንገድ ለመንገድ ከተመዘገቡ 38 ሺ 675 የጎዳና ላይ ነጋዴዎች መካከል 10 ሺ 137ቱ ህጋዊ የንግድ ስርዓት ውስጥ ገብተው መነገድ መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው መደበኛ ያልሆኑ ንግድ ስርዓት ማስያዝ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሉሌ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ቢሮው ባመቻቸው የንግድ ስርዓት ውስጥ ለመግባት ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር አንስቶ አስከ ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ድረስ በደንቡና መመሪያው መሰረት መታቀፍ የሚጠበቅባቸው 27 ሺ 735 የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ተመዝግበዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 10 ሺ 137ቱ ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት መግባታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣በዚህም ቢሮው ከያዘው የሁለት ዓመት የመካከለኛ እቅድ አኳያ ሲታይ በሩብ ዓመት ብቻ ከ 10 ሺ በላይ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት ማስገባቱ አፈፃፀሙን አመርቂ እንዳደረገው አስታውቀዋል፡፡
የመነገጃ ቦታዎቹ ህግና መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት ተሸንሽነው ዕጣ ከወጣባቸው በኋላ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ላወጡት 10 ሺ 137 የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ተሰጥተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በቦሌ ፣የካ፣ አዲስ ከተማና አራዳ ክፍለ ከተሞች ተሸንሽነው ዕጣ በወጣባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የጎዳና ላይ ነጋዴዎቹ እንዲነግዱ እንደተፈቀደላቸው አስታውቀዋል፡፡ በሁለተኛው የንግድ ስርዓት ማስያዝ ዙር ደግሞ ቀሪዎቹ ተመዝጋቢዎች በቀሩት ክፍለ ከተማዎች በሚገኙ የተፈቀዱ ቦታዎች ላይ እንዲነግዱ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲገቡ በማድረጉ ሂደት የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ተባባሪነት ዝቅተኛ እንደነበር አቶ ዳኛቸው ጠቅሰው፣ በተለይ ቦታዎቹን ቶሎ ሸንሽኖ በማፀደቅ ነጋዴዎቹ እንዲጠቀሙባቸው የማድረጉ ሂደት መጓተት መፍጠሩን ገልጿል። ይህም በሚፈለገው ልክ ነጋዴዎቹን ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት ማስገባት እንዳላስቻለ አመልክተዋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በደንቡና መመሪያው መሰረት መታቀፍ የሚጠበቅባቸውን ከ27 ሺ በላይ የሚሆኑ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን እንዲሁም ከዚህ መመሪያና ደንብ ውጪ የሆኑና የነዋሪነት መታወቂያ የሌላቸውን ከ 10 ሺ በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎችን በተጨማሪነት መመዝገቡም ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
በአስናቀ ፀጋዬ