መስከረም 21 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹የቆጡን አወርድ ብላ…›› በሚል ርዕስ ዘገባ መስራታችን ይታወሳል። ዘገባው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ጌሴም ኮንስትራክን ግንባታና ግብዓቶች ምርት ኃላፊነቱ የተወሰነ ሕብረት ሥራ ማህበር በሚል መጠሪያ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጀ ማህበር ላይ ያጠነጠነ ሲሆን፤ በሥራው ለዓመታት ከቆዩ በኋላ አባላቱ በውስጣቸው በተፈጠረ አለመግባባት ፍርድ ቤት ድረስ ያመራ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር። እስከ ፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሰው ቅሬታ ታዲያ መቋጫው ከማህበሩ ሥራ አይሠሩም በሚል የተባረሩ ሁለት አባላት አለአግባብ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲያገኙ ያደረገ መሆኑን በመግለጽ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅና ገንዘብ ያዥ ወደ ተቋማችን ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
በቅሬታቸው፤ ምንም እንኳ ሁለቱ ግለሰቦች ሥራ ካለመስራታቸው አልፈው በማህበሩ ውስጥ ከሌሎች አባላት ጋር ድብድብ የሚገጥሙና ድርጅቱን ወደ ሁከት ማዕከልነት የቀየሩ መሆኑ ታምኖ ያደራጃቸው የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት አውቆት ቢሰናበቱም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው የተዛባ ፍርድ እንዲሰጥ አድርገዋል ሲሉም ማቅረባቸው ይታወሳል። ውሳኔውም ከማህበሩ አልፎ የሥራ አስኪያጇ በክፍለ አገር የሚገኝ የግል መኖሪያ ቤት እንዲሁም ገንዘብ ያዡ በዕጣ ያገኙት የጋራ መኖሪያ ቤት ተሸጦ እንዲከፈል መወሰኑ ቅሬታን ፈጥሮባቸዋል። እኛም በጉዳዩ ላይ የሠራነውን ዘገባ አስመልክቶ በይደር ያቆየነውን ቀጣይ ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ሕጉ ምን ይላል?
የማንኛውም ማህበር ሲቋቋም መተዳደሪያ ደንብ የሚኖረው ሲሆን፤ አባላቱ ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ መስፈርቶችም ያስቀምጣል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዋጅ 147/91 እና በማሻሻያው 402/96 በማህበሩ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ማህበሩ በተሰጠው የምስክር ወረቀት ውል የማዋዋል፣ የመከሰስ፣ በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና መሰል መብቶች ይኖረዋል።
የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ የማህበሩ መሠረታዊ ሰነድ መሆኑን በመግለጽም፤ የማንኛውም ማህበር የበላይ አካል ጠቅላላ ጉባዔ በመሆኑ የአመራሩ አካላት ማለትም የሥራ አመራር ኮሚቴ፣ የቁጥጥር ኮሚቴና አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ንዑሳን ኮሚቴዎች በጠቅላላ ጉባዔው እንደሚመረጡ ያብራራል። ሥልጣን፣ ኃላፊነትና ተግባሩም ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የአመራሩ አካላት ሥልጣን፣ ኃላፊነትና ተግባር በግልጽ መስፈር እንደሚኖርበትም ሰነዱ ያትታል። በዚህም አባላት ከማህበሩ ስለሚወጡበትና ስለሚወገዱበት ሁኔታ በመተዳደሪያ ደንቡ መገለጽ አለበት።
አንድ ማህበር የሕግ ሰውነት ያለው ራሱን የቻለ ድርጅት በመሆኑ የሠራተኛ ቅጥር በአገሪቱ የሠራተኛ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦች መሠረት የሠራተኛ ቅጥር መፈፀም እንደሚኖርበትም ያስረዳል። ማንኛውም አባል በአዋጅ 147/91 መሠረት ጥቅሞቹ ተከብረውለት በጥያቄው መሠረት ከማህበሩ የመሰናበት እንዲሁም ደግሞ የህብረት ሥራ ማህበሩን ሕግና መመሪያዎች ብሎም በጠቅላላ ጉባዔ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የማክበር ግዴታም ይኖርበታል ይላል።
የማህበሩን የጋራ ንብረት የመንከባከብና የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበትም አዋጁ ይደነግጋል። በዚህም ማንኛውም አባል በተደጋጋሚ ግዴታዎችን ባለማክበሩ ወይም በማህበሩ ላይ ጥፋት በመፈፀሙ ምክንያት ከማህበሩ እንዲወጣ በጠቅላላ ጉባዔ ሊወሰንበት ይችላል። ስንብት ሲፈፀምም ሊከበሩለት የሚገቡ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችና መብቶች በመሆናቸው ተፈፃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ይደነግጋል።
ሽምግልና ዳኝነት
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ የጌሴም ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሥራ ማህበር ጉዳይ በሽምግልና ዳኝነት ታይቶ ኅዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም የተሰጠ ውሳኔ ማህበሩን አስመልክቶ ስናገላብጥ ካገኘናቸው ሰነዶች መካከል ይገኛል። በዚህም ከሳሾች አቶ ፍቃዱ ገብረሚካኤል እና አቶ ሺበሺ ተሾመ ሲሆኑ፤ ተከሳሾች ደግሞ ማህበሩ በመጀመሪያ ደረጃ፣ የማህበሩ ሊቀመንበር ወይዘሮ አሰፋሽ ፍቃዱ፣ የማህበሩ ገንዘብ ያዥ አቶ በለጠ ሙላት እንዲሁም የማህበሩ አባል ወይዘሪት በለጠች ደሳለኝ መሆናቸውንና ጉዳዩ ለግልግል ዳኝነት ቀርቦ ውሳኔ እንደተሰጠበት ሰነዱ ያመለክታል።
የግልግል ዳኝነቱ የሰጠው ውሳኔ ያረፈበት ሰነድ፤ ከሳሾች ከማህበሩ አለአግባብ ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጋቸውን ላቀረቡት ክስ የሽምግልና ዳኞቹ በሕጉ መሠረት ሁኔታውን መርምረው አቶ ፍቃዱና አቶ ሺበሺ ከማህበሩ ሊወገዱ አይገባቸውም በማለት በድምጽ ብልጫ መወሰኑ ሰፍሯል። የሽምግልና ዳኞች ውሳኔውን ሊያሳርፉ የቻሉትም ከሳሾችና ተከሳሾች በጋራ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ጉዳያቸው በሽምግልና ዳኞች እንዲታይላቸውና ውሳኔ እንዲሰጥላቸው በጠየቁትና በጻፉት ቃለጉባዔ መሠረት እንደሆነም ያትታል።
ከሳሾች ሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ለሽምግልና ዳኞች ጽፈው ባቀረቡት ክስ ከሳሾችና ተከሳሾች በአጠቃላይ አምስት የማህበሩ አባላት መሆናቸውንና በጠቅላላ በ10 አባላት የተመሰረተውን ተከሳሽ ማህበር መመስረታቸውን መግለፃቸውን የውሳኔ ሰነዱ ያወሳል። በማህበሩ ሥም ኦዲት ባለመደረጉም በጠቅላላ ምን ያህል ካፒታል እንዳለ እንደማያውቁና አንደኛ ተከሳሽ በሆነው በማህበሩ ሥም ግን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ 2 መቶ 15 ሺ ብር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራከሽን ጽሕፈት ቤት የሚገኝ መሆኑን በቃል ክርክር ወቅት ተከሳሾች እንዳስረዱ ማቅረባቸውን ያብራራል።
ተከሳሾች በራሳቸው ሥልጣን ከማህበሩ አባላት ዕውቅና ውጪ ከስምንት ድርጅቶች ጋር በእያንዳንዳቸው ሥም እንደተዋዋሉና ከሳሾችን ከማህበሩ አለአግባብ እንዳባረሩ ያስረዳል። በተመሳሳይ የማህበሩ አባላት ሳያውቁ ባልና ሚስት ሥልጣናቸውን አለአግባብ ተጠቅመው ከድርጅቶቹ ጋር ውል በመዋዋልና ‹‹ሰርተናል›› በማለት የማህበሩን ፍቃድ ለራሳቸው የግል ጥቅም እንዳዋሉት ተከሳሾች ማቅረባቸውን ሰነዱ ያስነብባል። ከሰባት ተቋማትም አጠቃላይ መጠኑ 2 ሚሊዮን 2 መቶ ሺ ብር ከማህበሩ አባላት ውጪ በማህበሩ ሥም በመውሰድ ባልና ሚስት በግላቸው ገንዘቡን ወደ ኪሳቸው ማስገባታቸውን ከሳሾች ባቀረቡት ዝርዝር ማስረጃ መረጋገጡን ያብራራል። የሽምግልና ዳኞቹም ገንዘቡ በማህበሩ ሥም ወደ ባንክ ሒሳባቸው አለመግባቱን ተከራካሪ ወገኖች ባሉበት ማረጋገጡንም ሰነዱ ያስቀምጣል።
የሽምግልና ዳኞቹ የማህበሩ ሒሳብ በኦዲት ተመርምሮ እንዲቀርብ ለማህበሩና ማህበሩን ወክለው ለሚከራከሩ ተከሳሾች ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም ፍቃደኛ ሊሆኑ አለመቻላቸውን የግልግል ዳኝነት የሰጠው ውሳኔ ሰነድ ያስነብባል። ከሳሾች ያቀረቡት ክስ በማህበራት ማደራጃ በኩል ለተከሳሾች ደርሷቸው የማህበሩ ተወካይ ወይዘሮ አሰፋሽ በሰጡት ምላሽ፤ ከሳሽ አቶ ፍቃዱ ከማህበሩ አለአግባብ እንደተባረሩ ቢያቀርቡም ዕውነታው ግን በሥራ ላይ የማይገኙ መሆናቸውና ‹‹አልሰራም›› በማለት እንደሆነ በማቅረብ ክሱ የሐሰት መሆኑን ማስረዳታቸውን ሰነዱ ያሳያል።
ሰነዱ እንደሚያመላክተው፤ ከሳሽ ያልደከሙበትን ገንዘብ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸው አግባብነት የጎደለው ጥያቄ በመሆኑም የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚዎች ቃለጉባዔ ይዘው እርምጃ በመወሰድ ከማህበሩ እንዲታገዱ መደረጉንም በምላሻቸው አብራርተዋል። አያይዘውም ተከሳሾች በ2002 ዓ.ም በጥቃቅንና አነስተኛ በህብረት ሥራ ማህበራት አዋጅ ቁጥር 147/91 ተደራጅተው በንግድ ሥያሜ ጌሴም ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዞች ማህበር በመባል በኋላም ይህ የንግድ ሥም ጌሴም ኮንስትራክሽን ግንባታና ግብዓቶች ምርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሥራ ማህበር በማለት በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባ ውስጥ እንዲመዘገብ ተደርጎ ግንባታና ግብዓቶች ምርት ንግድ ሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ያወሳል።
ተከሳሾችም የማህበሩ የመጀመሪያ ተመራጭ በመሆን ከተመሰረተበት 2002 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በሥራ አስፈፃሚነት ሲያገለግሉ እንደነበርና ከሳሽ አቶ ሺበሺ በአባልነት በማህበሩ ሲሰሩ እንደነበር መግለፃቸውን ሰነዱ አስፍሯል። ነገር ግን ተከሳሾች ባልና ሚስት በመሆናቸው ነባር አባላትን በልዩ ልዩ ምክንያት ከማህበሩ በማስወጣት፣ በማዋረድና በማጉላላት ከፍተኛ በደል እንደተፈጠረባቸው በከሳሾች የቀረበውን ክስ ብሎም የማህበሩን ማምረቻ መሣሪያዎች ሞልዶችን ተከሳሾች በራሳቸው ሥልጣን በማከራየት የኪራዩን ገቢ ወደ ማህበሩ ከማስገባት ይልቅ ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉ ለቀረበባቸው አቤቱታ ከሳሾች በቃል ከማስረዳት የዘለለ አያይዘው ያቀረቡት ማስረጃ የለም ሲሉም ተከሳሾች በምላሻቸው መሞገታቸውን ያብራራል።
ወይዘሮ አሰፋሽ በ25/5/2007 በከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ ሙሉ በሙሉ ክደው መከራከራቸውን የውሳኔ ሰነዱ ያመለክታል። ከሳሾች አለአግባብ ከማህበሩ እንደተባረሩና የማህበሩ መገልገያ መሣሪያዎችን ማለትም ቼክ ደረሰኝ፣ ማህተምና መሰል የማህበሩ መገልገያ መሣሪያዎች በተከሳሾች እጅ መቀመጣቸውንና ሥራውን እየሰሩበት መሆኑን አምነዋል። ምክንያቱ ደግሞ በግለሰብ ፍቃድ ሳይሆን በድርጅቱ መመሪያና ደንብ መሠረት ማህተም እንዲሁም ቼክ ደረሰኝ በአመራሩ እጅ መቀመጥ እንዳለበት መተዳደሪያ ደንቡ ያዛል ሲሉ አቅርበዋል።
ማህበሩ ሥራ ከጀመረበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ኦዲት ተደርጎ እንደማያውቅ የቀረበው ሌላኛው ክስ ሲሆን፤ ተከሳሾች ኦዲት ማስደረጋቸውን በማሳወቅ ለሽምግልና ዳኞች በቃል ክርክር ወቅት ማስረዳታቸውን ሰነዱ ያትታል። ሆኖም ግን ኦዲት ስለመደረጉ ማሳያ የሚሆን የኦዲት ሪፖርት አያይዘው ያቀረቡት ማስረጃ እንደሌለ ያሳያል። ከሳሾች ባቀረቡት አቤቱታ ተከሳሾች ባልና ሚስት ሆነው የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚዎች በመሆናቸውን ማህበሩ የቤተሰብ ቤት አድርገውት በአግባቡ ሊመሩ አለመቻላቸውን አሳውቀዋል።
ይህም በማህበሩ አምነው ሥራቸውን በአግባቡ ሰርተው መጠቀም እንዳይችሉ ተፅዕኖ ስላሳደረባቸው መሆኑንም መግለፃቸው በሰነዱ ይነበባል። ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል የቀረበው ክስ ሐሰት መሆኑን የሥራ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው ማህበሩ ከጊዜ ወደጊዜ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሱ ዓይነተኛ ማሳያ እንደሚሆን በመግለጽ ምላሽ መስጠታቸው በሰነዱ ይታያል።
በክርክሩ የመጀመሪያው ጭብጥ ማህበሩ የሚመራው በሕብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ? ወይንስ? በሽርክና ማህበር ነው የሚለው ሲሆን፤ በተከሳሾች በኩል በህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ወደ ሽርክና ማህበር እንዲቀየር መደረጉ ምላሽ ተሰጥቷል። ጉዳዩንም የክፍለ ከተማው ማህበራት ማደራጃ ሕግ ክፍል ባለሞያ ተጠይቆ ወደ ሽርክና ማህበር መቀየሩን እንደማያውቁ እንዳስረዱ ነው ሰነዱ የሚያመላክተው። ከሳሽ በበኩላቸው፤ በሰጡት ሐሳብ ማህበሩ ሲደራጅ በመጀመሪያ ኢንተርፕራይዝ እንደነበርና በኋላ ግን በማህበራት ማደራጃ እንድንደራጅ ሆነው እየሰሩ ወደ ሽርክና ማህበር ለመደራጀት ተስማምተው እንደነበር አብራርተዋል። በቆይታም ከሳሾችን ከማህበሩ እንዳስወጧቸው በክርክራቸው ማቅረባቸውን ሰነዱ ያስነብባል።
በሌላ በኩል ተከሳሽ ያቀረቡት ሐሳብ፤ ከሳሽ በስብሰባ ላይ አይገኙም በዚህ ምከንያት ከማህበሩ እንዲወገዱ መደረጋቸውን ነው። በተያያዘ ከሳሽ ከማህበሩ እንዲወጡ ከመደረጉ አስቀድሞ በተለያዩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታረሙ ማስመስከራቸውን በመግለጽ በከሳሽ የቀረበውን ክስ ትክክል እንዳልሆነ ማስረዳታቸውን ሰነዱ ያትታል። የሽምግልና ዳኞቹም በአዋጅ 147/9/ መሠረት አንድ የማህበር አባል እንዲወጣ ሲደረግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጠቅላላ የማህበሩን አባላት ስብሰባ ጠርቶ ጉዳዩ ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ ከተመከረበት በኋላ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት መሆን እንደሚገባው በማብራራት፤ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በራሱ ሥልጣን አንድ የማህበር አባልን ከማህበሩ ሊያስወጣ አይችልም በማለት በአንድ ድምጽ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንና ውሳኔያቸውን ማሳረፋቸውን የግልግል ዳኝነት ሰነዱ ያመላክታል።
ከሳሽና ተከሳሽ ባቀረቡት አቤቱታና ምላሽ መሠረት የሽምግልና ዳኞች አምስት ጭብጦችን በመያዝ ውሳኔ መስጠታቸውን ሰነዱ ያብራራል። በዚህም ማህበሩ ፈርሷል አልፈረሰም? ፣ ተከሳሾች ከሳሾች ላቀረቡት የገንዘብ ጥያቄና ወደ ሥራ የመመለስ እንዲሁም አለአግባብ ከማህበሩ ለታገዱበት ተጠያቂ ናቸው ወይስ አይደሉም? ፣ ተከሳሾች አለአግባብ የወጣውን የማህበሩን ገንዘብ እንዲከፍሉ ሊጠየቁ ይገባል ወይስ አይገባም? ፣ የማህበሩ ሒሳብ ኦዲት መደረግ አለበት ወይስ የለበትም? ፣ አንድ አባል በተደጋጋሚ ግዴታዎችን ባለማክበሩ በማህበሩ ላይ ጥፋት በመፈፀሙ ምክንያት ማህበሩ ሥራ አስፈፃሚዎችና በወረዳ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ቃለጉባዔ በመያዝ ከማህበሩ ማገድ ወይም ማስወጣት ይችላል ወይስ አይችልም? እንዲሁም በማህበሩ አባል ውስጥ ባልና ሚስት ሊቀመንበርና ገንዘብ ያዥ ሆኖ መመረጥ ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚሉ ጭብጦችን ይዘው እንደነበር ያሳያል።
የግልግል ዳኞቹ ከያዙት ጭብጥ በመነሳት ውሳኔ ማሳረፋቸውን ሰነዱ ያመላክታል። በዚህም ማህበሩ በአዋጅ ቁጥር 147/91 ንዑስ አንቀጽ ሦስት መሠረት ማህበሩ በመሰረታዊ ማህበር የተዋቀረ ሲሆን፤ ማህበሩ ግን በዚህ አዋጅ መሠረት የተሟላ አይደለም። ምክንያቱም ማህበሩ የተሟላ አባላት የሉትም። ምንም እንኳ በአንድ ማህበር ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው አባላቶች ቁጥር ከ10 በታች መሆን እንደሌለበት ማህበራት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 147/91 በአንቀዕ ሦስት መሠረት ቢደነገግም ቅሬታ በተነሳበት ማህበር ውስጥ ግን ያሉት አባላት ብዛት ከአምስት በታች ነው።
ይሁን እንጂ ማህበሩ አዋጁን ሳይከተል እንደሚሰራ ክፍለ ከተማው ሕብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ የቀረበ መረጃ የለም። ነገር ግን ማህበሩ በሥራ አስፈፃሚዎች ብቻ የማህበሩን ሥራ እያንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የሽምግልና ዳኞች እንደተረዱ ከሰነዱ ይነበባል። ዳኞቹም አሠራሩን አስመልክቶ የማህበራት ማደራጃ ኃላፊዎች ችግሩን በቅርበት በመከታተል በአዋጁ መሠረት እንዲያስተካክሉ ካልሆነም በሕግ አግባብ ማህበሩ እንዲፈርስ ውሳኔ መስጠታቸውን ሰነዱ ያሳያል።
ተከሳሾች ከሳሾች ላቀረቡት የገንዘብ ጥያቄና ወደ ማህበሩ አባልነት መመለስና ከማህበሩ ታግድው ለቆዩበት ተጠያቂ ናቸው ወይስ አይደሉም? እንዲሁም ሕጋዊ ያልሆነ የሠራተኛ ቅጥር በመፈፀም አልአግባብ የወጣውን የማህበሩን ገንዘብ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ? በሚል የቀረበው ቅሬታ ሌላኛው ዳኞቹ ውሳኔ ያሳረፉበት ጭብጥ ነው። በዚህም የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚዎች የድርጅቱን ንብረት ለማስጠበቅ በቀጠሩት የጥበቃ ሠራተኛ በቂ የሆነ ተያዥ እንዲያቀርብ በማድረግ ቅጥር መፈፀም ሲገባቸው በአካባቢ ነዋሪ ከሆኑት ታማኝና ጠንቃቃ ሠራተኛ መቅጠር ሲገባቸው በቸልተኝነት የማህበሩ ገንዘብ በዘራፊ ሠራተኞች እንዲወሰድ ማድረጋቸው ተጠያቂ ያደርጋቸዋል በሚል የቀረበ ክስ ታይቷል።
በተጨማሪም የተዘረፈ ዕቃ ለማስመለስ ተብሎ አላግባብ አድራሻው ባልታወቀና ትከክለኛ መረጃ ሳይኖራቸው ለፍለጋ በሚል ሰበብ የማህበሩን ገንዘብ የሆነ 33 ሺህ ብር ውጤት ላላመጣ ሥራ ወጪ መደረጉ በክስ መቅረቡ በውሳኔው ሰፍሯል። በመሆኑም ሥራ አስፈፃሚዎቹ ተጠያቂ እንዲሆኑና ገንዘቡን እንዲያሰሉ ከሳሾች ጠይቀዋል። በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የሥራ አስፈፃሚዎቹ የስልጣን ጊዜ ገደብ ያልተገለፀ ስለሆነ ማህበሩ በአዋጅ ቁጥር 449 መሠረት ያልተቀረፀ እንዲሁም የሥራ አስፈፃሚዎቹ በዘፈቀደ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው የማህበሩን አመራር አደጋ ወይም ጥፋት ላይ የጣላቸው በመሆኑ በማህበራት ማደራጃ በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ማህበሩ በሕግ አግባብ እንዲዋቀር መደረግ እንዳለበት ዳኞቹ ውሳኔ ሰጥተዋል። ለጠፋው ገንዘብ ሕግን ባለማወቃቸው ይታለፉ ባይባልም እየሠሩ የማህበሩን ገንዘብ እንዲከፍሉ ውሳኔ ማሳረፉን ሰነዱ ያሳያል።
ዳኞቹ፤ የማህበሩ ሒሳብ ኦዲት መደረግ ያለበት መሆኑን በተመለከተ ኦዲት ተደራጊ አካላት ለሒሳብ ምርመራ ለመተባበር ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፤ ለዚህ ድርጊታቸው በወንጀልና በፍትሐብሔር ሕግ እንዲጠየቁ የሽምግልና ዳኞቹ በአንድ ድምጽ ወስነዋል። ይህንንም የህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ በአዋጅ ቁጥር 147/91 አንቀፅ 39 መሠረት ጉዳዩን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ወስነዋል። በተያያዘ ከኃላፊነት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ አዲስ ምርጫ ማድረግ እንደሚቻል እንዲሁም ከሳሾች ከማህበሩ እውቅና ወጪ ተሰርቷል በሚል አጣርተው ባቀረቡት ማስረጃ መሠረት ከተመዘገበው ገንዘብ 2 ሚሊዮን 2 መቶ ሺህ ብር የመንግሥት ግብር ዕዳ ተቀናሽ ተደርጎ ለከሳሾች ለእያንዳንዳቸው አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲከፈላቸው የሽምግልና ዳኞች መወሰናቸው በሰነዱ ተመላክቷል።
የፍርድ ሒደት
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት በቀን 07/11/09 በቁጥር 40569 የወጣው መዝገብ ግልባጭ፤ አቶ ፍቃዱና አቶ ሺበሺ መሆናቸውን ያሳያል። በሌላ በኩል በሽምግልና ዳኝነቱ ላይ ተከሳሽ የነበሩት ማህበሩና ሦስት አባላቱ እንደሆኑ ያብራራል። በዚህም የፍርድ ባለመብቶች የግብር ዕዳው ተጣርቶ የቀረበ በመሆኑ የመንግሥት የግብር ገንዘብ 321 ሺህ 842 ብር ከ70 ሣንቲም ለአራት ባለዕዳዎች ወይንም ባለአክስዮኖች ሲከፈል ለእያንዳንዱ የሚደርሳቸው ድርሻ ከተወሰነላቸው ብር አምስት መቶ ሺህ ብር ላይ ሲቀነስ ሊደርሳቸው የሚገባው 469 ሺህ 539 ብር ከ32 ሣንቲም ስለሚሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ በፍርድ ባለዕዳዎች ሥም ካለውና ከ21/6/2009 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ የተገለፀው 159 ሺህ 135 ብር ለፍርድ ባለመብቶች እንዲከፈላቸው ለባንኩ ትዕዛዝ እንደተላለፈ መዝገብ ግልባጩ ያሳያል።
ቀሪውን ገንዘብ በተመለከተ ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 389 ሺህ 971 ብር ከ82 ሣንቲም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት የፍርድ ባለዕዳ አቶ በለጠ ንብረት የሆነው የቤት ቁጥር B007/20 የመኖሪያ ቤት በሐራጅ በመሸጥ በቅድሚያ የመንግሥት የግብር ገንዘብ ካስከፈለ በኋላ ለፍርድ ባለመብቶች በስሌቱ መሠረት ገንዘቡን እንዲያስከፍላቸው ማዘዙን በመዝገብ ግልባጭ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
በቀን 29/06/09 የመዝገብ ቁጥር 40569 የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ አንደኛ አፈፃፀም ችሎት የመዝገብ ግልባጭ ደግሞ የፍርድ ባለመብት አቶ ፍቃዱና አቶ ሺበሺ እንደሆኑና የፍርድ ባለዕዳዎች ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎትም ተከሳሽ የነበሩት ማህበሩና ሦስት አባላቱ መሆናቸውን ያሳያል። መዝገቡን መርምሮ ባሳለፈው ትዕዛዝም የፍርድ ባለዕዳዎች እንደፍርዱ ያልፈፀሙ በመሆኑ የፍርድ ባለመብቶች ተገደው እንዲፈጸምላቸው የጠየቁ ሲሆን፤ በግልግል ዳኞች ውሣኔ ላይ የመንግሥት ግብር ተቀንሶ ለባለመብቶች አምስት መቶ ሺህ ብር ለእያንዳንዳቸው እንዲከፈል የታዘዘ በመሆኑ የፍርድ ባለዕዳዎች ግብር አልተከፈለም እንዲሁም የጋራ እዳ ነው በማለት ክርክር እንዳቀረቡ ያትታል። ስለሆነም በቅድሚያ በማህበሩ ሥም ምን ያህል ግብር ዕዳ እንደሚፈለግ ማረጋገጫ እንዲላክ ማዘዙም ይነበባል።
ይህንን ለመመልከትም ለመጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም የፍርድ ባለእዳዎች እንዲያደርሱ ትዕዛዝ መሰጠቱ ይታያል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ የፍርድ ባለመብቶች የእግድ ትዕዛዝ ጠይቀው ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም እግድ የተሰጠላቸው ቢሆንም የቤት ቁጥር ስህተት አለበት ይታረም በማለት ያቀረቡትን ቃለመኃላ በመቀበል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገነት መናፈሻ ሦስተኛ ፎቅ ብሎክ ሰባት የቤት ቁጥር 199 የተባለው ቀርቶ የቤት ቁጥር B007/20 መሆኑን በመረዳት ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ ቤቱ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ ለሌላ ሦስተኛ ወገንም እንዳይተላለፍ መጠየቃቸውን በማንሳት በተጨማሪ ትዕዛዝ ላይ አስፍሯል። በመሆኑም ቤቱ ታግዷል በማለት መታገዱን እንዲያውቁ የዚህ ትዕዛዝ ግልባጭ ለቤቶች ልማት አስተዳደር ይተላለፍ በማለት መወሰኑን መዝገብ ግልባጩ ያስረዳል።
የመዝገብ ቁጥር 40569 በቀን 21/10/2009 ዓ.ም ቂርቆስ ምድብ አንደኛ አፈፃፀም ችሎት የፍርድ ባለመብቶች እነ አቶ ፍቃዱና የፍርድ ባለእዳዎች የሆኑት ማህበሩና ሦስት አባላቱ እንደሆኑ በመግለጽ፤ የፍርድ ባለእዳዎች በ30/09/2009 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ በመመሪያው አነሳስ መሠረት እንደሚነሳ ተረጋግጧል ቢባልም የገንዘብ መጠኑ ግን አልተገለፀምና በድጋሚ ምን ያህል እንደተነሳ እንዲገለጽ ይጠየቅ ማለታቸውን ያወሳል። የፍርድ ባለመብቶችም ጥያቄያቸው ገንዘቡ ተሰልቶ እንዲቀርብ መሆኑን መጥቀሳቸው በመዝገብ ግልባጩ ይነበባል። ፍርድ ቤቱም ይህንን ተቀብሎ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በ30/9/2009 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ መሠረት በመመሪያው ቁጥር 55/2003 እንዲስተናገዱ ማዘዙን ያሳያል። የተቀነሰው መቀጫ ምን ያህል እንደሆነ ስላልገለፀው ቁጥር አዘል ምላሽ እንዲልክ መታዘዙንና ትዕዛዙንም የፍርድ ባለእዳዎች እንዲያደርሱ መታዘዙን መዝገብ ግልባጩ ያስረዳል።
መዝገብ ቁጥር 193542 በቀን 15/02/10 ዓ.ም ማህበሩ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱንና እነ አቶ ፍቃዱ ደግሞ መልስ ሰጪ እንደነበሩ ያሳያል። መዝገቡ የተቀጠረውም በቀረበው የይግባኝ ማስፈቀጃ ላይ መርምሮ ተገቢውን ትዕዛዝ ለመስጠት ሲሆን፤ በዚህም ተመርምሮ ትዕዛዝ መሰጠቱን ያስቀምጣል።
በዚህም ይግባኝ ባይ በ21/06/09 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው ያለፈባቸው ውሳኔውን ለማወቅ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲመላለሱም ውሳኔ ሳይሰጣቸው ቀርተው በይግባኝ ባይ በኩል የተወከሉት ገላጋይ ዳኛ ባልተገኙበት ኅዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም ጉዳዩ እልባት ማግኘቱን የካቲት 9 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈ የአፈፃፀም አቤቱታ ከመጥሪያ ጋር ሲደርሳቸው መሆኑን ገልፀው ይግባኙን ለማቅረብ እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን መዝገብ ግልባጩ ያስረዳል። ፍርድ ቤቱም በቀረበው አቤቱታ ላይ መልስ ሰጪ አስተያየት እንዲሰጡበት ትዕዛዝ ተሰጥቶ ለሰጡት መልስ ክርክሩ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር መፍጀቱን ገልፀው፤ ይግባኝ ባይ በራሱ ጊዜ ቀርቶና የወከለውም ዳኛ እንዳይገኝ በማድረግ በክርክሩ ሳይሳተፉ ቀርተው ይግባኝ ያላቀረብኩት ውሳኔውን ባለማወቅ ነው በማለት ያቀረቡት ምክንያት ተቀባይነት የሌለው ነው ይላል። ይግባኙን ለማቅረብ ሊፈቀድላቸው አይገባም በማለትም ተከራክረዋል።
ፍርድ ቤቱም ይግባኝ ማስፈቀጃው ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል አይገባም? በሚል መመርመሩን ሰነዱ ያመለክታል። የቀረበውን አቤቱታ ለመመርመር ያመች ዘንድ ፍርድ ቤቱ የግልግል ዳኞች መዝገቡ አስቀርቦ ተመልክቷል። ከቀረበው መዝገብ ለመረዳት እንደተቻለው ጉዳዩ ረጅም ጊዜ የወሰደ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ በግልግል ዳኞች ያለመሟላት ምክንያት መዝገቡ ሲቀጠር እንደነበር በተለይ በይግባኝ ባይ በኩል የተመለከቱት ዳኛ በቀጠሮ ሳይገኝ እንደቀረ መዝገቡ ያስረዳል።
የጉባዔው መዝገብ የተለያዩ ቀጠሮዎች የሰጠ ሲሆን፤ ለቀጠሮ ባደረበት ሁኔታ በእንጥልጥል ያልተቀጠረበት ወቅት ያለው እንዲህ ከሆነ ደግሞ ክስ የቀረበበት ወገን ቀጠሮውንእያስከበረ ጉዳዩን የመከታተል ኃላፊነት ስላለበት ጉዳዩን ባለመከታተል ለሚፈጠሩ ውጤቶች ኃላፊነቱን የሚወስደው ተከራካሪ ወገን ነው በሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል። በተያዘው ጉዳይ ይግባኝ ባዮች ይግባኙን ለማስፈቀድ በምክንያትነት የሚገልጹት ውሳኔው መቼ እንደተወሰነ ስናውቅ በአፈፃፀም ስንገደድ ነው የሚል ነው።
የግልግል ዳኞች ጉዳዩን ሲመሩ ፍርድ ቤቶች በሚሰሩበት ሥርዓት ጉዳዩን ይመራሉ ተብሎ እንደሚታመንም ያሳያል። ይህ ከሆነ ደግሞ ተከራካሪ ወገኖች በየቀጠሮው እየተገኘ የጉዳዩን ደረጃ ያውቃሉ ተብሎ ይገመታል። በመሆኑም ይግባኝ ባይ ያቀረቡት ምክንያት ፍርድ ቤቱ በቂ ሆኖ ስላላገኘው ማስፈቀጃውን እንዳልተቀበለው መዝገብ ግልባጩ ያትታል።
መዝገብ ቁጥር 193542 በቀን 25/11/09 ይግባኝ ባይ ማህበሩ እንዲሁም መልስ ሰጪ እነ አቶ ፍቃዱ መሆናቸውን ያሳያል። ባሳረፈው ትዕዛዝም የቂርቆስ ክፍለ አስተዳደር ህብረት ሥራ ማህበር እንደ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ያልፈፀመበትን ምክንያት ከመግለጽ ጋር ችሎቱ በ30/10/09 ዓ.ም በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የግልግል ዳኝነት መዝገቡን ከቀጠሮው በፊት በሬጅስትራር በኩል እንዲያያይዝ ታዟል። በሌላ በኩል በ13/11/09 ዓ.ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ እስከ ተለዋጭ ቀጠሮ ፀንቶ እንዲቆይ ማዘዙን ያሳያል።
በመዝገብ ቁጥር 20522 በቀን 27/11/10 ይግባኝ ባይ ማህበሩ እንዲሁም መልስ ሰጪ እነ አቶ ፍቃዱ ሲሆኑ፤ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በህብረት ሥራ ማህበራት በቁጥር 56/2010 በቀን 24/11/2010 ዓ.ም በላከው መልስ የሰጠው ትዕዛዝ የተላኩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የሽምግልና ዳኞችን ማግኘት እንደማይችል መልስ ልኳል። ፍርድ ቤቱ በቀን 5/11/2010 በመዝገብ ቁጥር 205223 ያዘዘው ትዕዛዝ ጉባዔው ኅዳር 2009 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ በአምስተኛ ጭብጥ ላይ ለመልስ ሰጪዎች ለእያንዳንዳቸው ብር አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲከፍል ኃላፊነት የተወሰነበት ተከሳሽ ወይንም በዚህ ችሎት ይግባኝ ባይ ማን እንደሆነ ለይቶ እንዲልክ መታዘዙንም ያሳያል። ስለዚህ ይግባኝ ባይ ማን እንደሆነ ለይቶ እንዲልክ በድጋሜ መታዘዙን ሰነዱ ያሳያል።
በመዝገብ ቁጥር 205223 በቀን 04/07/2011 ዓ.ም ደግሞ በዋለው ችሎት የነበረውን የፍርድ ሒደት አብራርቶ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 40569 በ07/11/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን የአፈጻጸም ትዕዛዝ መሻሩን ያብራራል። የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለመልስ ሰጪዎች ለእያንዳንዳቸው እንዲከፈላቸው በግልግል ዳኝነት ጉባዔው በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ገንዘቡን በቅድሚያ ኃላፊነቱ የተወሰነው የህብረት ሥራ ማህበር ንብረት ላይ አፈጻጸሙን በመቀጠል የመንግሥት ግብር ካስቀነሰ በኋላ ለመልስ ሰጪዎች የተወሰነው ገንዘብ እንዲከፈል እንዲያደርግ ብሎም የአንደኛ ይግባኝ ባይ ንብረት ለእዳው መክፈያ በቂ ሆኖ ካልተገኘ ወይም ከሌለ ግን ወደ ሁለተኛና ሦስተኛ ይግባኝ ባይ ንብረት በመሄድ አፈጻጸሙን ቀጥሎ የተወሰነባቸውን ገንዘብ የመንግሥት ግብር ከተቀነሰ በኋላ እንዲከፈላቸው ይላል።
የመዝገብ ቁጥር 274289 በቀን 26/10/2011 ዓ.ም የፍርድ ባለመብት እነ አቶ ፍቃዱ የፍርድ ባለዕዳዎች መካከል በነበረው ክርክር ትዕዛዝ አስተላልፏል። በዚህም የፍርድ አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት አንደኛ የፍርድ ባለዕዳ በሚሰሩበት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት የቤት ቁጥር 004 በሆነው ቤት ውስጥ ያለውን የአንደኛ የፍርድ ባለዕዳን ንብረት ቆጥሮና መዝግቦ ያሸገው ከሆነ ለምን እንደታሸገ፣ አንደኛ ባለዕዳ ሌላ ዕዳ ስላለበት ከሆነም የሚፈለግበት ዕዳ ምን ያክል እንደሆነ የንብረቶቹ ዋጋ ግምት ታውቆ ከሆነም ተገቢውን ማጥራት አድርጎ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ማዘዙን ሰነዱ ያመለክታል።
በመዝገብ ቁጥር 265223 በቀን 03/11/2011 ዓ.ም ይግባኝ ባይ ማህበሩና ሦስት አባላቱ እንዲሁም መልስ ሰጪ እነ አቶ ፍቃዱ ሲሆኑ፤ አንደኛ ይግባኝ ባይ ትክክለኛ ሥም ጌሴም ኮንስትራክሽን ግንባታ ግብዓት ምርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ማህበር በመሆኑ የይግባኝ ክርክሩ እልባት አግኝቶ ለዋስትና የተያዘው ገንዘብ እንዲመለስ ትዕዛዝ ስለተሰጠ ይግባኝ ባዮች በዚህ መዝገብ ለዋስትና ያስያዙት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ማዘዙን ያመለክታል። ጉዳዩም በዚህ መልኩ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ደርሶ መዝገቡ ለይግባኝ አያስቀርብም በሚል ተዘግቷል።
የሚመለከታቸው አካላት
ማህበሩን ያደራጀው የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት በሰጠን ምላሽ፤ ጉዳዩ የቆየ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በጥልቀት መግለጽ አይቻልም። ነገር ግን ማህበሩ እንደፈረሰ ሰነዶች እንደሚያመላክቱ ነው የተገለፀልን። በመቀጠል በጉዳዩ ላይ ይመለከተዋል በሚል ያመራነው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሕብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፤ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን ሊሳካ አልቻለም።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
ፍዮሪ ተወልደ