አዲስ አበባ፡- ግዴታውን በታማኝነት የሚወጣና መብቱን በአግባቡ የሚጠይቅ የህብረተሰብ ክፍል ለማፍራት እንደሚሠሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ ።
ፓርቲዎቹ በገቢዎች ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተበሰረው የታክስ ንቅናቄ ፕሮግራም ላይ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ፓርቲዎቹ ግብርን መክፈል የዜግነት ግዴታ በመሆኑ ይህንን በታማኝነትና በአግባቡ የሚወጣ ማህበረሰብ በመፍጠር ሂደቱ ላይ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ ዋና ፀሐፊና የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማዬ ሀደራ እንዳሉት፤ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ነው። አንድ ሰው ግብሩን በታማኝነት በመክፈሉ ኩራት ሊሰማው ይገባል።
‹‹ሁሉም በመድረክ አንዳንዴም ጫካ ገብቶ እስከ መታገል የሚደርሰው አገሩን ለማገልገል ካለው ቀናይ ፍላጎት በመነጨ ነው›› ያሉት አቶ ግርማዬ፣ በዚህች በትንሿ ነገር ታማኝ መሆን ካልቻለ ግን ሥራው ሁሉ ኪሳራ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ ግብርን በታማኝነት በመክፈል አገራዊ ግዴታን መወጣት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
«እኛም አሁን ተፎካካሪ ፓርቲ እንባል እንጂ አንድ ቀን መንግሥት እንሆናለን፤ ያን ጊዜም ቢሆን ግብር ክፈሉ ብለን ማስተማራችን አልፎም ማስገደዳችን አይቀረምና አሁን ላይ ሀሳባችንን መቀበልና ለህዝቡ እንዲደረስ ማድረግ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡
‹‹ሙስና አለ ብሎ ግብር አለመክፈል አይቻልም›› ያሉት አቶ ግርማዬ፣ ግዴታን እየተወጡ መብትን በአግባቡ መጠየቅ የሠለጠነ ህብረተሰብ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ሁላችንም ልንተገብረው ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥትም ያጠፉትን መቅጣት ብቻ ሳይሆን በአግባቡና በታማኝነት ግዴታቸውን የሚወጡትንም በማበረታታት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አስታውቀዋል።
የመላው ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ተሰማ ሁንዱማ በበኩላቸው ‹‹ግብር መክፈል የሁሉም ግዴታ ነው፤ እስከ አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን ግብር የመክፈል ባህላችን ብዙ ይቀረዋል›› ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ይህንን መሰል ሰፋ ያለ የንቅናቄ ሥራ መሥራት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ እኛም እንደ ፓርቲ አስፈላጊውን የቅስቀሳ ድጋፍ እናደርጋለን›› ብለዋል።
‹‹ሰዎች በታማኝነት ግብራቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል አበረታች የሆኑ ተግባራት ሊኖሩ ይገባል ያሉት አቶ ተሰማ፣ አገልግሎቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማዋቀርና ቀልጣፋ አሰራርን በመዘርጋት ተጠቃሾቹ ሥራዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ግብር ከፋዩ ግብርን ሊሰውርና ሊያጭበረብር ሲሞክር፤ የግብር ሰብሳቢው ሠራተኛ በአቅምና በብስለት ከአጭበርባሪው ተሽሎ መገኘት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ይህ መሆን ከቻለ ግብር በአግባቡና በሥርዓቱ ይሰበስባል የሚል እምነት እንዳላቸውም ይናገራሉ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተከታታይነት ያላቸውን ትምህርቶች መስጠት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበው፣ በትምህርት የማይመለሱትንም በህግ አግባብ መቅጣቱ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የመድረክ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ሚሊዮን ቱማቶ ግብር ለአገሪቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ለሌሎች አገልግሎቶች ማስፋፊያ በመሰረታዊነት የሚጠቀስ ገቢ ግብር መሆኑን ተናግረው፣ ኑ ሁሉም የግብር ግዴታውን በአግባቡና በሥርዓቱ ሊወጣ ይገባል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ማቲዮስ ገለጻ ‹‹እንደ ዜጋ ያለማንም አስገዳጅነትና ጎትጓችነት ገቢያችንን በታማኝነት በማሳወቅ ግብራችንን በአግባቡ መክፈል አለብን ›› ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከዚህ አንጻር በግብር አሰባሰባቸው ላይ የተሻሉና ጥሩ ግንዛቤንም የፈጠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ተሞክሯቸውን አምጥተን ተግባራዊ ማድረግ ብንችል ኃላፊነቱን የሚወጣ ዜጋ ለመፍጠር ያስችለናል›› ብለዋል።
በአገሪቱ የህግ የበላይነትንና ዴሞክራሲ ለማምጣት ገንዘብ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ማቲዎስ ይህ ገንዘብ ሊገኝ የሚችለው ደግሞ ከግብር ብቻ መሆኑን በመረዳት ዜጎች ግብራቸውን በተገቢው መልኩ መክፈል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
እኛም እንደ አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ ዜጎች በታማኝነት ግብራቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉ ንቅናቄውን በመደገፍ የማስተማር ሥራንችንን እንሠራለን ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
በእፀገነት አክሊሉ