ወጣቶችን ማሳተፍ፣ ወደ አመራር ማምጣት በየመድረኩ የሚጠቀስ ዓለም አቀፍም ሀገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ወጣቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ካላቸው ብዛት አኳያ ነው መሳተፍም፣ ወደ አመራር መምጣትም አለባቸው የሚባለው፡፡
ይህ ወጣቶችን የማሳተፍ እና ወደ አመራር የማምጣት አስፈላጊነት በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩልም ዘወትር ይነሳል፡፡ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ባለፈው ባካሄዱት ድርጅታዊ ጉባኤያቸው ነባር የአመራር አባላትን በክብር ሲያሰናብቱ ወደ ሥልጣን ካመጧቸው ወጣቶች መካከል ይገኙባቸዋል፡፡
ወጣቶችን ወደ አመራር ከማምጣት አኳያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ክፍተት እንዳለባቸው የተለያዩ ወገኖች ይጠቁማሉ፡፡ የፓርቲዎቹ መሥራቾችና ነባር አመራሮች የአመራር ስፍራውን ለዘመናት ይዘውታል፤ ወጣቶችን ወደ አመራር ለማምጣት ሲሠሩ አይታዩም እየተባሉም ይተቻሉ፡፡
የተፎካካሪ ፓርቲዎች በበኩላቸው ለዓመታት የተደረጉብን ጫናዎች ወጣቶችን ለማብቃትና ወደ አመራር ለማምጣት ቀርቶ፣ በአባልነትም ይዞ ለመሥራት የማያስችሉ ነበሩ ሲሉ ምላሻቸውን ይሰጣሉ። የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ወጣቱን በፖለቲካ ውስጥ እንዳይሳተፍ የሚያደርግ፣ ቢሳተፍም ከፍተኛ መስዋዕት የሚያስከፍል እንደነበር ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ይጠቁማሉ።
አንጋፋው ፖለቲከኛና የተፎካካሪ ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ‹‹የቆየንበት የፖለቲካ ድባብ ወጣቶችን ለማብቃትና ወደ ኃላፊነት ለማምጣት የሚጋብዝ አልነበረም››ይላሉ፡፡ በእኛ ሀገር ዐውድ የፖለቲካ ፓርቲ -አመራር መሆን ማለት ራስን ለማይገባ መስዋዕትነት ማጋለጥ ነው ሲሉም ሀገሪቱ ያሳለፈቻቸውን አፋኝ የፖለቲካ ዓመታት ይገልጻሉ፡፡
አውራውን ፓርቲ ለመቀናቀን አመራር መሆን ቀርቶ አባል መሆን በራሱ ለከፋ ተፅዕኖ ሲዳርግ መቆየቱን፣ ይህም ተጨባጭ ሁኔታ ወጣቱ ወደ ፖለቲካው መድረክ እንዳይመጣ ማድረጉን ያስታውሳሉ፡፡
‹‹ወጣቱ ሥራ ይፈልጋል፤ ሥራ ላይም መቆየት ይፈልጋል››ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ ተፅዕኖዎቹ ወጣቱ ለመድረክ እንዲበቃ ደንቃራ እንደነበሩ ያብራራሉ፡፡ ወጣቶች ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው የአመራር ቦታውን ለመቀበል ምን ጊዜም ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የሚጠቁሙት።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ‹‹ያሳለፍናቸው ዘመናት ወጣቱን መስዋዕትነት ውስጥ የሚከቱ እንጂ ለፖለቲካ ፓርቲ አባልነት የሚያበቁ አልነበሩም›› በማለት የፕሮፌሰር በየነን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ በሀገር ውስጥ በአመራርነት ቀርቶ በአባልነት ለመሳተፍ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳልነበር ይጠቁማሉ። በዚህ የተነሳም ወጣቱን ለማብቃት የሚያስችሉ ዐውዶች አልነበሩም ይላሉ።
ፕሮፌሰር መረራ በውጭ ሀገሮች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወጣቱን የሚያሳትፉ እንዳልነበሩ ይጠቅሳሉ፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል በውጭ ሀገሮች ከ40 እስከ 50 ዓመት የቆዩ እንዳሉ ጠቅሰው፣ ተተኪ አመራሮችን ለማፍራት እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በውጭ የሚኖሩ ወጣት ዜጎቻችን ለእንጀራቸው ስለሚሮጡ በፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ሊቸግራቸው ይችላል›› ሲሉ ፕሮፌሰር መረራ ይጠቁማሉ፡፡
ወጣት ምሁራንን ማፍራት እንደሚገባም አስገንዝበው፣ መጪው ዘመን በሀገር ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ የሚችሉበት ስለመሆኑ ፍንጮች እየታዩ መሆናቸውንም ያመለክታሉ፡፡ ወጣቶችን ማፍራት የሚቻልበት ሜዳ ሠፊ እና ምቹ እንደሚሆንም ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ አመራር አቶ ተሻለ ሰብሮ ከሁለቱም ፖለቲከኞች የተለየ ሀሳብ ነው ያላቸው፡፡ ፓርቲው ሲዋቀር አንስቶ በወጣቶች የተሞላ መሆኑን፣ ከ3ሺህ አባላቱ 2/3ኛው ወጣቶች መሆናቸውን ያብራራሉ።
ወጣት አባላቱ ራዕይ ያላቸው ሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ ከአንጋፋዎቹ የአመራር አባላት ተሞክሮዎቹን እንዲቀስሙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተሻለ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣት አባላትንና አመራሮችን ለማፍራት ጥረት አያደርጉም የሚለው ፓርቲያቸውን እንደማይመለከት ይናገራሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ወጣቶችን ወደ አመራር የማምጣት ጉዳይ ፓርቲው ሲመሰረት አንስቶ በሕገ ደንቡ በግልፅ አስፍሮ ሲሠራበት የቆየ መሆኑን ነው ።
የፓርቲያቸው አመራሮች የሥራ ዘመን አራት ዓመት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ተሻለ፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለሁለት ዙር መመረጥ የሚቻልበት ዕድል እንዳለም ይናገራሉ፡፡ ከሁለት ዙር በላይ ማገልገል ግን እንደማይቻል ይጠቁማሉ፡፡
አመራሩ አዲሱን አመራር ተቀብሎ ኃላፊነቱን ያስረክባል። በቀጣይ ፖለቲካውን በሰከነ መንገድ የሚመሩ የተማሩና ልምድ ያላቸው ወጣቶችን ለማብቃት እየሠራን ነው ይላሉ፡፡
የፖለቲካ ሥልጣን ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጥበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በፓርቲያቸው ውስጠ ዴሞክራሲ መሰረት ይህን ኃላፊነት የሚወጡ ብቃት ያላቸውን ወጣቶች በአመራርነት ለማስቀጠል እየተሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ።
‹‹በኃላፊነትና በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ወጣት ኃይል ነው ያሰባሰብነው፤ ወጣት ምሁራንም አሉበት፤ አንድ ሁለት የሚሆኑ መካከለኛና አንጋፋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አመራሮች ያሉበት ነው›› ሲሉ አቶ ተሻለ ይናገራሉ።
አቶ ተሻለ ቀደም ሲል ስጋትና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች እንደነበሩ አስታውሰው፣ በሴቶች እና ወጣቶች ላይ ብዙ ለመሥራት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡ አሁን የተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በወጣቱ ዘንድ የፖለቲካ ተሳትፎ ፍላጎት ማሳደሩንም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ