አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት መፍጠር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) አስታወቀ፡፡
የኦዴግ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ እንዳሉት፤ በአገሪቷ ምቹ የዴሞክራሲ ሁኔታ እንዲኖር የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዋና ዋና አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር በመዋሃድ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል በፓርቲያቸው ውስጥ ማዳበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት እንዲፈፅሙ ያቀረቡትንም ጥያቄ እንደሚደግፉ ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከሌሎች አገር አቀፍ ዋና ዋና ፓርቲዎች ጋር የሚፈፅሙት ውህደት በፓርቲዎቹ ይሁንታ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም፤ ፓርቲዎቹ ውህደት ከፈፀሙ በኋላ ለሚወክሏቸውና መብታቸውን ለማስጠበቅ ለቆሙላቸው የህብረተሰበ ክፍሎች ምርጫ በተቃረበ ወቅት ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሊታገሉላቸው ይገባል፡፡
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ብቻ ሳይሆን ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋር መዋሃድ እንደሚገባቸው ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰፊ የአስተዳደር መዋቅርና የሃያ ዓመታት የአመራር ልምድ እንዳለው ጠቅሰው፣ ‹‹በውጭ አገራት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የራሳቸው መዋቅርና ልምድ የሌላቸው በመሆኑ ውህደት መፈፀማቸው ተገቢ ነው›› ብለዋል፡፡
ውህደት በመፈፀም እንደ አንድ ፓርቲ ለመቆም ከኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ከወጡ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋር ንግግሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን ሊቀመንበሩ ተናግረው፣ የእርሳቸውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለማቸውንና ለየትኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች መታገል እንዳለባቸው ከወዲሁ ማሳወቅ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
በአስናቀ ፀጋዬ