በኢትዮጵያ 2011/12 ዓ.ም የምርት ዘመን ከመኸር እርሻ 382 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል። ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 13 ነጥብ 86 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት ታስቦ 13 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር ከእቅዱ 96 በመቶ ተዘጋጅቷል። እስከተጠናቀቀው ሳምንት ድረስም ከታረሰው ማሳ 12.2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ 89 በመቶውን በዘር ለመሸፈን መቻሉን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የመኸር እርሻ በስፋት ከሚከናወንባቸው ክልሎች በተወሰኑ አካባቢዎች የበረሀ አንበጣና የስንዴ ዋግ የመሳሰሉ ችግሮች ቢከሰቱም ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። የክረምቱም ዝናብ የተስተካከለና አሉታዊ ተጽእኖ የሌለው በመሆኑ ሰብሉም በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ መረጃው አመልክቷል። በመሆኑም እስካሁን ያለው የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ በእቅዱ የተቀመጠውን ያህል ምርት ለማስገኘት የሚያስችል መሆኑን ያነጋገርናቸው የክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ገልጸውልናል።
በአማራ ክልል የመኸር ግብርና እንቅስቃሴው በተቀመጠው እቅድ መሰረት እየተከናወነ ስለሆነ በዘንድሮ አመት ከፍተኛ ምርት ይጠበቃል ያሉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ ናቸው። እንደሃላፊው ማብራሪያ በዘንድሮ አመት በክልሉ የመኸር እርሻ አራት ሚሊየን 435 ሺ 747 ሄክታር በሰብል የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም ከ120 ሚሊየን 739 ሺ607 ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
እቅዱ የተያዘው ባለፈው አመት የተገኘውን 102 ሚሊየን 952 ሺ 971 ምርት መነሻ በማድረግ አስፈላጊውን ግብአት በመጠቀም የምርት መጠኑን ወደ 121 ሚሊየን ለማሳደግ በመዘጋጀት ነው። ይህንንም ለማድረግ በምርጥ ዘር አቅርቦት በኩል ከዚህ ቀደም በቆሎ በስፋት በሚመረትባቸው የምእራብ አካባቢዎች የነበረውን ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ዝርያዎችን የመጠቀም ልምድ በማስተካከል በአጭር ጊዜ የሚደርሱትን በስፋት እየተጠቀምን እንገኛለን ብለዋል።
ኩታ ገጠም አሰራርን መሰረት አድርጎ በመስመር መዝራት እንዲሁም ሞዴል አርሶ አደሮችን በማበረታታት ኤክስቴንሽንና መካናይዜሽንን በማስፋፋት ረገድም በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ሰለሞን ግብአት በመጠቀም በኩልም የአፈሩ ለምነት ለተመናመነባቸው አካባቢዎች የሚሆን አምስት ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ተሰራጭቷል ብለዋል።
በሌላ በኩል ክረምቱ ሲጀምር በተለይ ሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ አካባቢና የተወሰኑ ቦታዎች ላይ የዝናብ መዘግየት የነበር ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በቂ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል። የሰሊጥ ምርት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ዝናቡ ክረምቱ ይወጣል ከተባለበት ጊዜ አልፎ እየጣለ እንደሆነና የሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን እየሰበሰቡ ቢሆንም ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለ ለሰሊጥ ምርት ስጋት እንደሚሆን ግን ጠቁመዋል። በተጨማሪ በምስራቁ ክፍል ከፍተኛ ሙቀት ያለበት አካባቢ በመሆኑ ሰብሉ እየደረሰ እንደሆነና ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለ ሊወድቅ እንደሚችል ስጋት አላቸው።
በተጨማሪ አሜሪካ መጤ ተምች በተወሰኑ ቦታዎች ተከስቶ የነበረ ቢሆንም 18 ሺ ሊትር ኬሚካል ከፌዴራል በማምጣትና በመጠቀም በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ዶክተር ሰለሞን ተናረዋል። ሌላው ለመኸር እርሻው እንደ ስጋት የተጋረጠው ችግር በአፋር አካባቢ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ አሁንም ተባዝቶ በአፋር፤ አማራ፤ ትግራይና ኦሮሚያ ድንበር አካባቢዎች በስፋት ይገኛል። ይህንንም ለመከላከል የፌዴራል መንግስትና የክልሉ ግብርና ቢሮ እስከ ወረዳ የሚደርስ መዋቅር ዘርግቶ በቅርበት እየተከታተለና ለመቆጣጠር እየሰራ ይገኛል።
ይህም ሆኖ ለአንበጣው ምቹ ሁኔታ ስላለለት ብዙ ስራ የሚጠይቅ ሲሆን ምን አልባትም በአሮፕላን በመጠቀም የመከላከያ መድሀኒት ርጭት ማካሄድ የሚደርስ ሰፊ ስራ የሚጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል። የመከላከሉ ወቅት ደግሞ አሁን ሲሆን በዚህ ሰአት ተገቢው እርምጃ ካልተወሰደ እንቁላል ይጥልና በመኸሩም በበልጉም እንዲሁም በመስኖ የሚለሙ ሰብሎች ላይ ጉዳት የሚያደርስበት እድል ስለሚፈጠር ይህንን ለማስወገድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሃላፊው ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ደጀኔ ሂርጳ በበኩላቸው የክልሉ የመኸር እርሻ በታቀደለት መሰረት እየተከናወነ እንደሆነ ይገልጻሉ። አቶ ደጀኔ እንደሚናገሩት በመኸር እርሻ ስድስት ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታስቦ እስካሁን 97 በመቶውን ማሳካት ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም የዘር መዝራት እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የሰብል እንክብካቤ ስራ እየተሰራ ይገኛል። በአንዳንድ አካባቢዎችም ቀደም ብለው የተዘሩት እየደረሱ በመሆኑ ለመሰብሰብ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
በግብአት አቅርቦት ረገድም ባለፈው አመት በክልሉ አራት ነጥብ አንድ ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን በማስታወስ ዘንድሮ ከቀረበው አምስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን ኩንታል ውስጥ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊየኑ አገልግሎት ላይ መዋሉን አቶ ደጀኔ ተናግረዋል። በአንዳንድ ኪስ ቦታዎች ከማዳበሪያ አቅርቦት ዩሪያ መጠነኛ እጥረት ገጥሞ ነበር ያሉት አቶ ደጀኔ ለመኸር ከቀረበው የተረፈውን ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለመስኖ እርሻ ልማት ለመጠቀም እቅድ መያዙን።
በምርጥ ዘር አቅርቦቱም ረገድ በታሰበው መሰረት የተከናወነ ሲሆን ከአገዳ እህሎች ጋር ተያይዞ በቤኒሻንጉል ክልል አካባቢ ምርጥ ዘር ሲመረት ተከስቶ ከነበረው የጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ ችግር ገጥሞ እንደነበርና እሱንም የማስተካከል ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል። የዝናቡም ስርጭት ካለፉት አመታት የተሻለ መሆኑንና ከሜትሮሎጂ የሚወጡት መረጃዎች ከዚህ በኋላ ዝናቡ እየቀነሰ የሚሄድ መሆኑን የሚያመላክቱ በመሆናቸው ለሰብሉ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ የመቀበልና አዳዲስ አሰራሮችን የመተግበር ችግር የለበትም ያሉት አቶ ደጀኔ ነገር ግን በሶስተኛ ደረጃ ላሉ የአቅም እጥረት ላለባቸው አርሶ አደሮች አንዳንድ ቴክኖሎጂዎችን ማዳረስ አልተቻለም ብለዋል። ላለፉት አስር አመታት ይቀርብ የነበረው በክፍያ በመሆኑ ሊጠቀም የሚችለው ገንዘብ ያለው አርሶ አደር ብቻ ነበር። ይህን ለመቅረፍ በዘንድሮ አመት አንዳንድ ስራ የሚያቀላጥፉና የጉልበት ወጪና የምርት ብክነት የሚቀንሱ መሳሪያዎችን በብድር ለማቅረብ እየተሰራ ነው። በእውቀት ሽግግር ረገድም በቂ የሰለጠነ የሰው ሀይል ቢኖርም በአንዳንድ ሙያተኞች በኩል በየኔነት ስሜት መስራት ላይ ክፍተት እንዳለ በመለየቱ ይህንን ለማስወገድ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአዋሽ ተፋሰስ ምእራብ ሸዋ ኤጀሬ የሚባል አካባቢ እንዲሁም በሰበታ በኩል እስከ ምስራቅ ሸዋ ባለው አካባቢ ከአንድ ወር በፊት ከፍተኛ የውሃ ሙላት ተከስቶ በሰብል ላይ ችግር አድርሶ ነበር። አርሶ አደሩም ከአካባቢው የተነሳው በሄሊኮፕተር ነበር አሁን እሱን ለመተካት እየተሰራ ሲሆን የተወሰደውን ዘር ብቻ ለመተካት ስልሳ ሚሊየን ብር የሚደርስ ወጪ የሚጠይቅ የዘር ግዢ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ባጠቃላይም ከክልሉ የመኸር እርሻ 186 ሚሊየን ኩንታል ምርት የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት የቅድመ ምርት ግመታ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ምሩጽ በበኩላቸው በክልሉ ለመኸር እርሻ በተደረገው ዝግጅት አንድ ነጥብ 28 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል። አቶ ሚካኤል ለመኸር እርሻ የተደረገውን ዝግጅት ሲያብራሩ የማዳበሪያ ግዢን በተመለከተ በፌደራል በኩል የተወሰነ መዘግየት ተከስቶ የነበረ ቢሆንም ወደ ክልሉ ከደረሰ በኋላ ግን የቀረበውን 455 ሺ ኩንታል በፍጥነት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ተደርጓል። በተወሰኑ አካባቢዎች የበቆሎ ዘር እጥረት ገጥሞ የነበረ ቢሆንም እሱንም በመቅረፍ ዘጠኝ ሺ 450 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲዳረስ ተደርጓል።ከመኸር እርሻው 25 ነጥብ ሰባት ሚሊየን ኩንታል እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
በክልሉ ደቡብ፤ ደቡብ ምስራቅና ምስራቃዊ ዞን ዝናቡ ሁለት ሳምንት ዘግይቶ የጀመረ ሲሆን በማእከላዊ ሰሜን ምእራብና ምእራብ ዞኖች ጥሩ የዝናብ ስርጭት እንደ ነበር የተናገሩት ዳይሬክተሩ የበርሃና የአሜሪካ አንበጣ ተከስቶ አርሶ አደሩን በማስተባበርና መድሀኒት በመርጨት ለመቆጣጣር መቻሉን ተናረዋል።እስካሁን በስፋት እየተስተዋለ ያለውንም ድህረ ምርት ብክነት ለመከላከል በሚድያ በመጠቀምና የሀይማኖት አባቶችንም በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋ አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ