አዲስ አበባ፡- የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እስከ አሁን ከ 38 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። ለ23 ሺ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጿል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ በፓርኩ ውስጥ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሰማሩ 19 የውጭ እና አንድ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ገብተው እየሠሩ ይገኛሉ።
ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን በዋነኝነት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያ እየላኩ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ በአገዋ የገበያ ዕድል በመጠቀም ወደ አሜሪካ ገበያዎች ለመግባት ሰፊ ዕድል እንደተፈጠረላት ገልጸዋል፡፡ በአውሮፓ ገበያም እንዲሁ እንደ አገዋ ያለ ኢ.ቤ.ኤ የተሰኘ ድርጅት አባልም መሆኗን ጠቅሰው፣በዚህም ምርቶቿን ከቀረጥ ነጻ ወደ አውሮፓ ገበያ እያስገባች እንደምትገኝ አመልክተዋል። እነዚህንና ሌሎች መሰል የገበያ አማራጮችን መጠቀሟ የምታገኘው ገቢ ከፍ እንዲል እንደሚረዳም አቶ መኮንን አስታውቀዋል፡፡
በፓርኩ የባንክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም፣ ኢሚግሬሽን ፣ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎቶች እንዲሁም የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ ሌሎችም የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ለኩባንያዎቹ እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
‹‹ፓርኩ ከሌሎች የሚለይባቸው በርካታ ነገሮች አሉ›› ያሉት አቶ መኮንን፣ አንዱ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ሥራ አስኪያጆች እንዲሁም የዘርፉ ኤክስፐርቶች አቅማቸውን ለመገንባት የሚያስችላቸው የሥልጠና ማዕከል የሚገኝበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ብቸኛው የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት እንዲሁም የፓርኩን ተረፈ ምርቶች እንደገና በመፍጨት በፓርኩ ያሉ ኩባንያዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲጠቀሙበት የሚያደርግ መሆኑን ሌሎች ልዩ የሚያደርጉት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቀደም ብለው ወደ ሥራ ከገቡት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅትም ለ23 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
በቀጣይም የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመረቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀም ይገኛል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
በእፀገነት አክሊሉ