ለካ እንደትዝታ አስታምሞ
እንደዘነጉት የእናት ጡት ፣ ከዘመን ጋር አገግሞ
ምንም ቢቀር ምንም ቢ ሸሽ ፣ ሕልሜ ከሕልምሽ ተዛሞ
በዓይንሽና በዓይኔ መሃል ፣ የሃሰት ሥልጣኔ ቆሞ
ባንተያይ ባንወያይ ፣ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
እንደልጅነት ሰመመን ፣ ለካስ ዕድሜም ያማል ከርሞ ።
ተግ ሲል ያንቺ ሽውታ
ብዥ ሲል እንደአድባር ጥሪ ፣ እንደተረብ ቅርስ ሽታ
እንደእሳት ዳር ተረት ግራሻ ፣ እንደእንቆቅልሽ ትውስታ
የጥቅምት እሸት አወደ ፣ ነቃ ደሞ ያንቺ ትዝታ . . . .
አውድማው ተንደረከከ
ሰንበሌጥ ተንተረከከ
ነይ አክርማ እንነቃቅል፣
ከወንዛችን ሾላ ጠለል
ነይ ጢሎሽ እንጣጣል ፣
መስኮቻችን ሰብሎቻችን ፣ ግጦሾቻችን አባቱ
የአቴቴሸ ላሞች አጋቱ
በሮቻችንም አጓሩ ፣ ኮርማዎቻችንም ነቁ
ጊደሮቻችን ለጥቃት ፣ ለይዘታ ለክብደት በቁ
የሁዳድ ድርቆሽ ሠፈረ ፣ ጥገቶቻችን ቦረቁ ፡
አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ ፣ እጄን በትዝታሽ ያዢኝ
በሕልም ጣቶችሽ ሳቢኝ
መቸም … በውን አልሆንሽም ፣ እንዲያው በሰመመን
ዳሺኝ ።
የኔ እጅ እኮ እርፍ አይጨብጥም
የኔ ክንድ ተልሞ አይተልምም
የኔ ጣት አረም አይነቅልም
በፊደል መፈደል በቀር ፣ ጉልጓሎ እኮ አይጐለጉልም
ለስልሻለሁ ፣ ሠልጥኛለሁ ፣ ሰይጥኛለሁ አልሆንሽም፣ አቴቴ ዱበራ ቦረና
መቸም ሁሉን ቻይ ነሽና
አጥንቴ ከአጥንትሽ ማዕድን ፣ ቢመነጭም ተቀምሞ
ከ”ሀና” ከ”አሐዱ” በፊት ፣ ከቃል በፊት አስቀድሞ
ዛሬ በዓይንሽ በዓይኔ መሀል ፣ አጉል ሥልጣኔ ቆሞ
ሰየጠንኩና አልሆንሽ አልኩ ፣ አቴቴ ዱበራ ኦሮሞ፣ …
አዎን መቻል ባንቺ ያም ራል ፣ ያን የትዝታ ሰ ቀቀን
ያን የልጅነት ሰመመን
ምንም በውል ባንደርስበት ፣ ጭላንጭሉ እየታወሰን
ውል ሲል እንዳልጠፋ ቀን
ከዓመት ዓመት ተሸጋግረን ፣ አዳዲስ ዘመን ሲሰለፍ
ሰንበሌጡ ሲንተረከክ ፣ የአዝመራ እሸት ሲትረፈረፍ
የማር እሸት እንቁረጥ ተይ ፣ የጥቅምት አበባ እንቅጠፍ
ነይ ሸጎዬ አብረን እንግዘፍ
ጣት ለጣት እንቆላለፍ
በዓይን ጥቅሻ እንገራረፍ
ከአውድማችን አፋፍ ለአፋፍ ፣ በዳሰሳ እንጠላለፍ
ተይ ፍቅር እንዘራረፍ
በሕልም እንኳ እንተቃቀፍ ፣ . . . .
አቴቴ ዱብራ ቦረና ፣ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
የቀን የጊዜ እንቆቅልሽ ፣ በሕልም መርፌ ተጠቅሞ
በየመከሩ ተተልሞ
ከትዝታ ጋር አስታምሞ
እንደዘነጉት የእናት ጡት ፣ ከዘመን ጋር አገግሞ
ምንም ቢቀር ምንም ቢሸሽ ፣ ሕልሜ ከሕልምሽ ተዛሞ
በዓይንሽና በዓይኔ መሃል ፡ አጉል ሥልጣኔ ቆሞ
ባንተያይ ባንወያይ ፣ እንደጥንቱ እንደቀድሞ
እንደልጅነት ሰመመን ፣ ዕድሜም እኮ ያማል ደሞ . . . .
አዎን ዕድሜም ያማል ከርሞ . . . .
“አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ።”
(ለአቴቴ ዱብራ ኦሮሞ – 1962 ዓ.ም – ባሌ ጎባ)
ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012