እንጉርጉሮ ለስለስ ባለ ድምጽ የሚዘፈን ወይም የሚዜም ኀዘንና ብሶት፤ የደስታ ስሜት የሚገለጽበት፤ ሥላቃዊ ወይንም ለዘኛ ጨዋታ የሚሰማበት የዜማ ወይም የቁዘማ ስልት ነው ። በመላ ሀገራችን በግብርና ሥራ የሚኖሩ አርሶ አደሮች እንደ ጃርት፣ ጦጣ፣ አሳማ፣ ዝንጀሮ፣ ነጎዴና ግሪሳ ወፎች የመሳሰሉትና በአስቸጋሪነታቸውና በእህል ፈጂነታቸው የሚታወቁት ፀረ ሰብል አራዊት አዝመራቸውን እንዳያጠፉባቸው የጥበቃ ሥራ ሲሠሩ፤ ይዘፍናሉ፤ ያንጎራጉራሉ ። ከዚህም የተነሣ በሰብል ላይ ጥቃት አድራሾቹን ለመከላከል የቻለ በጦር እየወጋ፤ ያልቻለ በወጥመድ ወይንም በመንቀፊሎ እየያዘ፤ ሌላው ደግሞ በወንጭፍ ወይም በአበራሮ ጠጠር እየወነጨፈ በመግደል ሲከላከል «ወፍ ጠርጣሪ አይጥ መንጣሪ» እያለ ይፎክራል ። በተለይም የዝንጀሮንና የጦጣን፤ የነጎዴን ተንኮል አርሶ አደሩ ስለሚያውቅ
«ዝንጀሮ በዳገት ጦጣ በዛፍ ላይ፤
የማይበላ እህል ይጠበቃል ወይ?
ወፍ እጠብቃለሁ ነጎዴ ነጎዴ ፤
አምና ልጃገረድ ዘንድሮ ጎናዴ ።
ማሽላን ወፍ በላው እንኳን ወፍ ይብላው ነጎዴ፤
የሰው ነገር አትስማ ሆዴ— » በማለት ዝንጀሮና ጦጣ ባለበት ቦታ ላይ ዘርቶ ማፈስና መቃም እንደማይቻል እየተረተ ይጫወታል ። በተጨማሪም ሰብሉን አሳማ ገብቶ ካጠፋበት «አሳማ የገባው ገብስ፤ ጆቢራ የገባው ድግስ ዋጋ የለውም » እያለ በተረት የአራዊትን ክፉ ሥራ ይኮንናል ። አራዊቱም ጥፋት የሚያደርሱት ወድደው አይደለም ። ያው ኑሮ ትንቅንቅ ስለሆነባቸው ነው ።
በዚህ ዓይነት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደጀን ወረዳ ቆላና ደጋ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችም ከነሐሴ እስከ ጥር ድረስ ባለው ጊዜ ሰብላቸውን ከጃርትና ከልዩ ልዩ አራዊት ጥቃት የሚከላከሉት ከላይ በተገለጸው የመከላከያ ዘዴ ነው ። በተለይ ደግሞ የጃርት፤ የአሳማና የዝንጀሮ መንጋ ጥቃት በእጅጉ ከፍተኛ ስለሆነ አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ሌትም ቀንም በትጋት መጠበቅ አለባቸው ። ሰብላቸውን በአግባቡ ካልጠበቁ ግን በሰነፎች ላይ በአራዊቱ ሰዋዊ አንደበት ግጥም እየገጠሙ ይሳለቁባቸዋል ። አዝመራቸውን በአራዊት አናስበላም፤ አናስጠቃም ብለው የሚጠብቁትንም ጀግኖች እነጃርት ያሞግሷቸዋል ። ተወልጄ በአደግሁበት በአለቅታም አቦና ሚካኤል አካባቢ ዛሬ በትዝታ የማስታውሳት ‘’ አዘነጋሽ’’ የተባለች ጃርት ትኖር ነበር። የአገሬ አርሶ አደሮች ይህን ዓይነት ስም ያወጡላት በተለይ በመስከረም፤ በጥቅምት፤ በኅዳርና በታኅሣሥ ወር ላይ አድብታና አዘናግታ ወደ ጓሮአቸውና ማሳቸው በመግባት የደረሰ ዱባቸውን ሠርቃና ያፈራ በቆሏቸውን ሸልቅቃ ስለምትግጥባቸውና ያሸተና ያኮረተ የባቄላ፤ የአተርና የዘንጋዳ፤ የገብስ እሸታቸውን… እየፈለፈለችና እየሸመጠጠች ስለምታጠፋባቸው ነው።
‘’ አዘነጋሽ’ ይህንን የጥቃት ዘመቻ የምታደርሰው አርሶ አደሩ በቀን ሥራ ደክሞና ዝሎ ሌሊት ጧ ብሎ በሚተኛበት ጊዜ ነው ። በዚህ ዓይነት በሌሊት የማይነቃ ገበሬ ስታገኝ ከደስታዋ ብዛት የተነሣ ቂ…ቂ… ብላ እየሣቀች ወደ ጓሮው ትገባና የልቧን ትሠራለች ። ከነቄዎች፤ ከልባሞችና ከታታሪ ገበሬዎች ጓሮ ጨርሶ ዝር አትልም። ምክንያቱም ልባም ገበሬዎች በአንካሴ ስለሚወጓትና ወጥመድ እያጠመዱም ስለሚይዟትና በዱላም ስለሚደበድቧት ነው። እንዲያው አዘነጋሽ በተንኮሏ ስለታወቀች ነው እንጂ እርሷ የምትመራው የጃርት ባታሊዎን ጦር ብዙ ነው ። የጃርት ሠራዊት እንደ ተምች፤ እንደ ቸነፈር ስለሚቆጠር በሰብል ወቅት ላይ መከላከያውን አንካሴ የማያስል፤ ጦርና ዘገር የማያዘጋጅ ፤ጨርቅ የለበሰ ጭምብል በየጓሮው የማያቆም አርሶ አደር አይኖርም ። የብረት ሥራ ለሚሰሩ ገበያቸው የሚደራው በሰብል ወቅት ነው ። በዚህ ወቅት መጥረቢያ፤ ማጭድ፤ አንካሴ፤ ጦር ፤ ዘገር የማያስል ሰው አይኖርም ።
ቢሆንም ብረት ያሳለው ሁሉ ጀግና ሆኖ ጃርት ላይወጋ ይችላል ። ይኽ ሁሉ ጦር ለእርሷና ለወገኖቿ የተዘጋጀ መሆኑን በደመ ነፍስ ብታውቅም እንደ አይጥ «እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል» እያለች ማምለጫዋን ጭምር ታዘጋጃለች ። ሰነፉን አርሶ አደር ደግሞ አዘነጋሽና አጥቂው ሠራዊቷ ስለሚያውቁት በሌሊት የነቃው ታታሪ አርሶ አደር አጣድፎ ሲያባርራቸው ወደ አያ ሰነፌ፤ ወደ ጋሸ አይነቄ ጓሮ ይዘምታሉ እንጂ ጭራሽ በርግገውና አገር ጥለው አይሸሹም ። እነ አዘነጋሽ ሲደረስባቸው ጦርነት ይገጥማሉ፤ የጃርት ወስፌያቸውን ወደ ጠላት እያስፈነጠሩ ይፋለማሉ ። የጃርት ጦር በቀላሉ ዓይን ላይ ሊሰካ ስለሚችል ጃርት ጠባቂ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል ።
አዘነጋሽ አርሶ አደሩን በምትሐቷ አሞኝታ፤ አዘንግታና አድብታ ፤ ወደጓሮው ከገባች የዓመቱን አዝመራ በአጭሩና በዕንጭጩ ለማስቀረት ችሎታ አላት። እና ከዕለታት በአንዱ ሰነፍ ከሆኑት ከአቶ አዳሙ ፈረደ ጓሮ ገብታ በቆሎ ስትሸለቅቅ የአቶ አዳሙ ባለቤት ሰምተው ኖር « አዳሙ ኧረ ተነሥ! ጃርት ገብታ እያጠፋችኮ ነው ‘’ ይላሉ ። አቶ አዳሙም ከእንቅልፋቸው መነሣት ስለአስጠላቸው ‘’ ሴትዮ አርፈሽ ተኚ ጃርቷ የለችም ‘’ ብለው ለጥ ይላሉ ። ጃርትም የልቧን አድርሳ ከጠገበች በኋላ እንደዚህ ብላ ዘፈነችባቸው።
አዳሙ ፈረደ እንዴት ይወድደኛል፤
ከመሃል ቁጭ ብዬ የለችም ይለኛል ።»
አንዲት የነጋባት የመስከረም ጃርት ሰው አየኝ አላየኝ ብላ ሁልጊዜ የዓይን አሩን (ጩቁን) ከማይጠርገው ከአያ ምንተስኖት ጓሮ ሹልክ ብላ በመግባት የልቧን ትሠራለች ። በራስጌ በኩል ገብታ እያሰሰች በግርጌ በኩል ስትወጣ አያ ምንተስኖት ዓይኑን እያጭለመለመ ወደ ጓሮው ሲመጣ ታየዋለች። ነገሩ አስገረማትና
“ በራስጌ ገብቼ በግርጌ ስወጣ፤
አያ ምንተስኖት ጩቁን ጠርጎ መጣ ‘’
በማለት ተመፃድቃበታለች። አቶ አሞኘ የተባለው ደግሞ የነቃና ታታሪ አርሶ አደር በመሆኑ ገና ወደ ጓሮ ለመግባት ስትሞክር ነቅቶ ስለሚያባርራትና ስለሚመታት
‘’ ሲሄድ እንዳሞራ ሲማታ ልብራስ፣
ከአያ አምኘ ጓሮ አልቀምስም አንድራስ»
እያለች ትናገር ነበር ይባላል። እንደዚሁም ተዘራ የተባለ ወፍራም ሰው በዚያው ይኖር ነበር። አያ ተዘራ እግሩን የዝሆኔ በሽታ ስለያዘው ሲራመድም ቀስ እያለ ነው እና ጃርቲቱ አዘነጋሽ የሰውየውን ሁኔታ አጥንታ አንድ ዕለት ከጓሮው ዘው ብላ በመግባት ዱባውንና በቆሎውን ሙልጭ አድርጋ በላችበት። ጥፋቷ ሳያንሳት ደግሞ በአቶ ተዘራ ላይም እንደዚህ ስትል ተረተችበት።
‘’ ተዘራ በቀለ የጠብደል ኮሳሳ፣’’
በልቼ እጠግባለሁ እግሩን እስቲያነሣ”
የአቶ ተዘራ በቀለ ባለቤት ወ/ሮ ዓይኔ ቢሰነብት ጃርቷ /አዘነጋሽ/ ባለቤቷን በመስደቧ ‘’ ቆይ ይህችን መልከ ጥፉ አሳያታለሁ ከእርሷ የከፋ ኩስና አስቀያሚ ፍጥረት አለ አንዴ?» እያለች በጃርቷ ላይ መፎከር ታበዛለች ። አጋጣሚ ሆኖ የዓይኔ ቢሠነብት ዓይን ሸውራራ ነበር። ጃርትም ይህንኑ ታወቀው ስለነበር ሁለቱን መልከ ጥፉ ባልና ሚስት ልታዋርዳቸው ጊዜ ትጠብቅ ጀመር። አንድ ቀን ያአያ ተዘራ ታናሽ ወንድም አቶ ዘገየ በቀለ ልጁን ይድር ነበርና ጃርት እያጨበጨበች ወደዳስ በመግባት የሚከተለውን ዘፈን በአቶ ተዘራና በወ/ሮ ዓይኔ ቢሰነብት ላይ ዘፈነችባቸው።
«ግምን ግም አይስተው ውብን ውብ አይስተው፣
ዓይኔን ለተዘራ ማን አመለከተው ።
ዘገየ በቀለ አንተ የዋልክበት፤
ሠርግህ ያማረ ነው ሸጋ የበዛበት ።»
ብላ ስትዘፍን ለሠርግ የተጠራው ሁሉ በተዘራና በዓይኔ ላይ ሣቀባቸው። እንዲሁም ሠርግህ ያማረ ነው ያለቺው አቶ አማረ የተባለ አርሶ አደር ሲናገር ድምፁ የትም ቦታ ይሰማ ስለነበርና ከብቶቹን ነድቶ ከመኖሪያ ቤቱ «ዛዳ» እስከተባለው የእርሻ ቦታው እስኪደርስ ባቄላውን በልታ ጠግባ ከድንበር ላይ ተጎምራ በመዝናናት ላይ እያለች የሰውየውን ድምጽ የሰማቺው አዘነጋሽ በዚህ ተገርማ
«አንተ በርቀት ላይ ከንቱ ስታገሳ
ባቄላው ያለቀው ገና ሳትነሣ ።
አያ አማረ እጅጉ አርፍደህ ማለዳ፤
ድሪቶህን ለብሰህ ከብቶች ስትነዳ ፣
እኔ ዛዳ ሆኚ በሣቅ ልፈነዳ ። »
ብላ አንጎራጉራበታለች። ዛዳ የበቆሎ፣ የአተር፣ የባቄላና የገብስ አዝመራ የሚበቅልበት የአለቅታሞች የእርሻ ቦታ ነው ። የአዘነጋሽና የወገኖቿ ምሽግም እዚያው የዛዳ ቁጥቋጦና ጫካ ነበር። በተመሳሳይ ብላታ እውነቱ አለማው /የአካባቢው አጥቢያ ዳኛ/ ሳይቀሩ ከመንገድ ዳር በቆሎ ዘርተው መጠበቅ ሲገባቸው በመስከረም ወር ጠንታ ከተባለ ቦታ የሚኖሩ የሩቅ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ስለሄዱና እንደልቧ አዘነጋሽ በደረሰ በቆሎአቸው ላይ ስለፈነጨችበት
«አያ እውነቱ አለማው ለነፍሱ ያደረ፣
ከመንገድ ዳር ዘርቶ ጠንታ ተሻገረ ።»
ብላ ዘፍናባቸዋለች ። ጠንታ ከደጀን ማዶ ጉበያ አካባቢ የሚገኝ መንደር ነው ። እንደዚሁም ዋሌ ዓለሙ የተባሉ አርሶአደር ሌሊት ጓሯቸውን መጠበቅ ሲገባቸው ተኝተው እያደሩና ማለዳ ብቻ እየተነሡ በቆሎና የባቄላ አዝመራቸው በጃርት መበላቱን ባዩ ቁጥር «እማዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ወይኔ ዘንድሮ መሰደዴ ነው፤ ያገር ያለህ፤ የዘመድ ያለህ ፤በአዝመራየ ተጫውታበት የለ አንዴ? ወይኔ ወይኔ » እያሉ ሲያለቅሱና ሲያዝኑ ጃርት ሰ ምታቸው ኖሮ
‘’ እንኳን በራስጌው ላይ በግርጌ ተጥሶ፣
ማነው የሚከርመው ያያ ዋሌን ለቅሶ ።
ማለዳ ማለዳ እያለቃቀሰ ፤
አያ ዋሌ መጣ ዓይኑን አባበሰ ።
በቆሎውን ነቅቶ መቅራት ነበረበት፣ ሌት እየፎከረ፤
ስሜን ያጠፋዋል ተኝቶ እያደረ»
ብላና አልቃሻ መሆናቸውን ገልጣ ጃርቲቱ እንደቀለደችባቸው ባላገሮቹ ይናገራሉ ። ሀብታም ባልና ሚስት በዚያው በአካባቢ ይኖራሉ ። ለሀብትና ለገንዘብ ግድ የሌላቸው መሆናቸውን ለካ አዘነጋሽ አስቀድማ አውቃለች ። እናም የጓሮ በቆሏቸውን ሙልጭ አድርጋ ስትበላ ሳይናገሯትና ሳይቆጧት በመቅረታቸው የልብ ልብ ስለተሰማት
«ተሜ ባይናገር ሰገድ ባትቆጣ ፤
ከማጀት ገብቼ ቅራሪ ብጠጣ » አለች ይባላል ።
እንደዚሁም አቶ አያሌው ትሳሱ የተባሉት ቁመታቸው አጭር መሆኑን ጃርቲቱ ስላወቀች ባወጣ ያውጣው ትልና ከጓሯቸው በመግባት ትልቅ ዱባ አንሥታ ይዛባቸው ስትሮጥ እርሳቸውም እየሮጡ ይከተሏታል ። ግን ሳይደርሱባት ስላመለጠች እንዲህ ብላ ቀለደችባቸው ።
“አያሌው ትሳሱ ድኩሜ ድኩሜ፤
አልደርስብኝ አለ ዱባ ተሸክሜ ።”
ከላይ የቀረቡትን የግጥም ዘለላዎች ራሷ ጃርት ከአእምሮዋ አመንጭታ ቤት መትታ፣ሐረግ ደርድራ፤ አንደበት አውጥታ ያስተላለፈቺው አይደሉም ። ጃርት ሰነፉን አርሶ አደር እየነቀፈች፤ ትጉኁን ደግሞ እያወደሰች እንደማትናገር ይታመናል ። ይልቁንም በጃርት አንደበት የሚናገሩላት ራሳቸው የፈጠራ ችሎታ የአላቸው አርሶ አደሮች ናቸው ። በደቦ፤ በሰንበቴ ማኅበር ፤ በበዓል ቀን ሲገናኙ ጃርትኮ እገሌን እንዲህ ብላ ሰደበቺው፤ አሞገሰችው፤ እንዲህ ብላኮ በአንተ ላይ ቀለደች እየተባባሉ እርስ በእርስ ይተቻቻሉ ። ይህም እርስበርስ የመተቻቸት ጥበብ ማኅበራዊ ኂስና ስለምን ጨዋታ ይሰኛል። ይህ ሁሉ ስለምን ጨዋታና ማኅበራዊ ኂስ የሚያሳየን ያልተማሩና ፊደል ያልቆጠሩ አርሶ አደሮች በማኅበራዊ ሕይወታቸው ምን ያህል እንደሚግባቡ፤ እንደሚረዳዱና ንቃት፤ ጥንቃቄ፤ ኅብረት፤ ታታሪነት ትጋት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ነው ። የእያንዳንዱን አርሶ አደር የሥራ ችሎታና ዘዴ በሚተቸው በዚህ ቀልድ መሰል ማኅበራዊ ኂስ አማካይነት አርሶ አደሮች እርስ በርስ እየተሣሣቁና እየተግባቡ ከስሕተታቸው ይማሩበታል እንጂ መቀያየም፤ መጣላት ብሎ ነገር በእነርሱ ዘንድ የለም ።
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2012
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)