ችግር ፈቺ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮች ለሀገር ዘርፈ ብዙ ለውጥ የሚያበረከቱት አስተዋጽኦ የጎላ ነው። ለዚህም ነው ሀገራዊ የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታት በሀገር ደረጃ ጥረት በመደረግ ላይ ያለው፤ ሀገር በቀል የሆኑ የፈጠራ ስራዎች መነሻቸው አካባቢያዊ ችግር ነውና ችግሮቹን ለመፍታትና መፍትሄ ለመስጠት ቁልፍ ሚና አላቸው።
በሀገር ልጅ ለሀገራዊ ችግር መፍትሄ ይሆናሉ፤ የማህበረሰቡን ችግር ይፈታሉ ተብለው ተስፋ የሚጣልባቸውን የፈጠራ ስራዎች ማበረታታት ጠቀሜታ የላቀ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው። ውስብስብ የሆኑ ጥናቶችን ከሚጠይቁ ጥልቅ ሳይንሳዊ ምርምሮች ጀምሮ በቀላሉ አካባቢያዊ የሆኑ ቁሶችን በመጠቀም አስገራሚ ፈጠራ የታከለበት አዲስ የቴክኖሎጂ ወይም ነባሩን መጠቀሚያ ቁስ በማሻሻል የሚሰሩ ፈጠራዎች ከጠቀሜታቸው አኳያ በእርግጥም ትኩረትን ይሻሉ።
የፈጠራ ስራ የግል ጥረትና ተደጋጋሚ ሙከራ የሚጠይቅ፤ ሳይሰለቹ በትጋት የሚወጡት፣ በላቀ ፍላጎትና በፍቅር የሚሰራ ተግባር ነው። ለዚህም አካባቢያዊ ሁኔታ ለፈጠራ ስራና ለምርምር ብቻ ባልሆነበት ሁኔታ እንኳን አስደናቂ የሆኑ የፈጠራ ውጤቶች መታየታቸው የባለሙያው ወይም የፈጠራ ስራው ባለቤት ትጋት መሆኑ ማሳያ ነው። አሁን ላይ በሀገር ደረጃ የራሳቸውን ጥረት በማድረግ እጅግ አስገራሚ የፈጠራ ስራ የሚሰሩ ወጣቶች መመልከት ተለምዷል።
በአካባቢያቸው ያገኙትን የወዳደቀ ቁስ በመጠቀም አዕምሯቸው ውስጥ የተፈጠረውን አዲስ እና ፋይዳው የጎላ፤ ለማህበረሰቡ የላቀ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ቁሳቁስ ወይም የቴክኖሎጂ ውጤት በመፍጠር ለማህበረሰቡ ግልጋሎት ለማዋል የሚታትሩ ወጣቶች ስናይ ሀገራችን በመስኩ ያላትን የወደፊት ብሩህ ተስፋ መገመት ያስችላል። ሀገራዊ እድገት ማረጋገጫው መንገድ ደግሞ ሳይንስ ነውና ትኩረት ተሰጥቶበታል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ ወደፊት የተራመዱ ሀገራት ቅድሚያ ያሰለፋቸው ዋንኛ ምክንያት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትኩረት በመስጠታቸው፤ ብሎም ለዘርፉ ከፍተኛ በጀት በመመደብ በወጣቱ ትውልድ ላይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እውቀት በማስረፅና በማላመድ እንዲሁም የሚፈጠሩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ትልቅ አቅማቸውን በመጠቀም ወደ ተግባር ሊያውሉ ባደረጉ ጥረት መሆኑ እሙን ነው።
በቀላሉ ቴክኖሎጂን ማስረፅ የሚያስችልና በዘርፉ ከፍ ያለ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ወጣቶች ላይ ትኩረት በመስጠትና በመጠቀም ፈጠራዎችን እንዲያመነጩ ማበረታታት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ወጣትነት ተግተው ከሰሩበት ሀገርንና እራስን ለመለወጥ መሰረት የሚጣልበት፣ ሮጠው የማይደክሙበት፣ ያሰቡትን ለማሳካት ከታተሩ ስኬትን መጎናፀፍ የሚቻልበት ምርጡ የእድሜና ዘመን ጊዜ ነው።
በዚህ ጊዜ የጣሉት መሰረት፤ በዚህ ወቅት የከወኑት ተግባር በእድሜ ዘመን የሚመነዘር በህይወት ቆይታ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር የሚያስችል መቆሚያ የሚያበጁበት ነው። ተግተው ከሰሩ ጥሩ እመርታን ማስመዝገብ የሚቻልበት መሆኑ ማሳያ የሚሆን አንድ ወጣት የፈጠራ ባለሙያ በዛሬው የሳይንስ አምዳችን አነጋግረን ስለ ፈጠራ ስራው በዚህ መልክ ለማቅረብ ወደናል።
በ21ኛ ክፍለ ዘመን ዓለም በቴክኖሎጂ ርቆ ሄዷል። ዘመኑ ሰልጥኖ መንጥቋል እየተባለ በሚወራበት፣ የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ መጥቆዋል ተብሎ በሚለፈፍበት ዛሬ ላይ ቆመን ቀን ካልሆነ ብርሀን የማያይ፤ በፋኖስ ካልሆነ ድግዝግዙን ጭለማ የመግፈፍ እድል ያልገጠመው ህዝባችን በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ዛሬም በርካታ ነው። ይህ እየመረረንም ቢሆን የምንቀበለው ያለንበት ሀቅ ነው። ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝባችን በመብራት እጦት ጭለማ ውስጥ መሆኑ እጅጉን ያስቆጫል።
የዛሬው የሳይንስ አምድ እንግዳችን የፈጠራ ስራው ዋንኛ መነሻ ምክንያት ይሄ ቁጭት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ባለ ከፍተኛ ፍላጎት የመነጨ በጎ ሀሳብ ስለመሆኑ ይናገራል። ወጣት ኪሩቤል አወቀ። በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ኪሩቤል ሰዓቱን በአግባቡ የሚጠቀም በልጅነቱ ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ተሰምቶት የህዝብን ችግር ለመቅረፍ የሚተጋ ብላቴና ነው።
የወጣት ኪሩቤል ህልም ለዚህ ህዝብ ብርሀን ማሳየት፤ የተጋረጠበትን ጭለማ መግፈፍ ነው። ታዳጊው ከልጅነቱ ጀምሮ ያሰበውን የማህበረሰቡን የጭለማ ጉዞ ወደ ብርሀን የመለወጥ ውጥኑን አሳክቷል። በፈጠራ ስራው ብርሀንን መፍጠር የሚያስችል ቀላል የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ተርባይን ፈጥሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ሊሆን በቅቷል።
የፈጠራ ስራው ምንነት፡-
ገና ታዳጊ ልጅ ሳለ በትምህርት ቤት ደረጃ በተለያዩ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች በማቅረብ ውድድር ያደርግ የነበረው ወጣት ኪሩቤል አወቀ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሸለመበት የፈጠራ ስራው ቀላል የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይነር ነው። ሙሉ በሙሉ የግል ፈጠራው ውጤት የሆነው ቀላል የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይን በአሁኑ ሰዓት በወጣቱ በየጊዜው የማሻሻልና አቅሙን የመጨመር ስራ እየተሰራለት ይገኛል።
የወጣት ኪሩቤል የፈጠራ ስራ ትኩረት አግኝቶ ከተደገፈ በሀገር ደረጃ እየተሰራ ያለው የኃይል ምንጮችን የማጠናከርና ተደራሽ የማድረግ እቅድ የሚያግዝ፤ ብሎም መብራት ያልተዳረሰበትን የገጠሩ የሀገራችን ክፍል የፈጠራ ስራውን በማሰራጨት ትልቅ መፍትሄ ሊያስገኝ የሚችል እንደሆነ የፈጠራ ባለሙያው እምነት ነው።
ኢንዱስትሪዎች ማምረት የሚፈልጉትን ያህል ምርት ለማቅረብ ዳገት የሆነባቸው፤ በሀገር ደረጃ የታሰቡ ትልልቅ የልማት ስራዎች ፍጥነታቸውን በመግታት የተፈታተናቸው የኃይል እጥረት ችግር ለመፍታት በእርግጥም ወሳኝ ዘርፍ ነው። ይህንን ለመግታት ደግሞ የኃይል አማራጮችን መጠቀምና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ መፍትሄዎችን ማፈላለግ እንደ ሀገር እየተሰራበት መሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው።
የወጣቱ የኪሩቤል ቀላል የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ የፈጠራ ስራ የኤሌትሪክን ኃይል በብርቱ ለሚፈልጉት ኢንዱስትሪዎች ችግር ለመፍታት ምሉዕ መፍትሄ ባይሆንም ከተሰራበት የሰፋውን የኃይል እጥረት የራሱን ለመቅረፍ የራሱን ድርሻ ሊወጣ የሚችል መሆኑን የፈጠራ ባሙያው ይገልፃል።
የፈጠራ ስራው መነሻ ምክንያት፡-
ገና ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ በትምህርት ቤት የሚዘጋጁ የፈጠራ ስራዎችን ሲመለከት የፈጠራ ስራ ምንነት መመርመር እንደጀመረና ወድቀው ከሚያገኛቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች በመገጣጠም አዲስ ነገር ለመፍጠር በመሞከር መጀመሩን ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ኪሩቤል ይናገራል። በልጅነቱ የሚሞክራቸው የፈጠራ ስራዎች ለዛሬ መቆሙ መሰረት እንደሆኑትና በሰራቸው ስራዎችም ያገኛቸው ማበረታቻዎች እንደጠቀሙት ያስረዳል።
ለአዲሱ የፈጠራ ስራው ምክንያት የሆነው ሀገራዊ ሁኔታን መነሻ ያደርጋል። በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል የመብራት አለመዳረስና የማህበረሰቡ በኃይል እጥረት ምክንያት ሲቸገር ማየቱ ለዚህ የራሱን መላ መዘየድ እንዳለበት በማመኑ እንደሆነ ያስረዳል። የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት መማሰኑ፤ የወገኖቹን መብራት መናፈቅ መረዳቱ መፍትሄ አስገኘለት።
ለፈጠራ ስራ ያለው ልዩ ፍቅር ለፍሬ አበቃው። የምርምር ወይም የፈጠራ ስራ ውስጣዊ በሆነ ተነሳሽነት፤ በልዩ ፍቅር የሚሰራ መሆኑን የሚናገረው ኪሩቤል ለርሱም ውጤታማ እንዲሆን ያስቻለው የሙያው ፍቅር መሆኑን ያስታውሳል።
በፈጠራ ስራው የተገኙ ሽልማቶችና እውቅናዎች
በ2011 በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የፈጠራ ስራ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ወጣቱ ኪሩቤል በፈጠራ ስራ ሽልማቶችን ማግኘት የጀመረው ገና አፍላ ወጣት ሳለ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ነው። የቀለም ትምህርት በቀሰመባቸው የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማግኘት በዞንና በክልል ደረጃ በፈጠራ ስራዎች ተወዳድሮ የተለያዩ ሽልማቶች ማግኘቱንም ይገልፃል።
በክልል ደረጃም የተለያዩ የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይና ውድድሮች ላይ በመሳተፍም ሰርተፍኬቶችንና የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል። ካገኛቸው እውቅናና ሽልማቶች በተጨማሪ ከተለያዩ ተቋማት ማበረታቻና የገንዘብ ሽልማቶችን ማግኘቱንና ለፈጠራ ስራው ማሻሻያ አድርጎ እንደተጠቀመበት ይናገራል።
የፈጠራ ስራው ፈታኝ ገጠመኞች
በፈጠራ ስራ ሂደት ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነውና ተሳክተው አይገኙም። ከፊት የሚገጥምን ችግር ለመፍታት በወኔ መታጠቅና የገጠመን ችግር በማቅለል ለችግሩም መፍትሄ በማበጀት ወደፊት መጓዝ የተመራማሪ ልምድ የፈጠራ ባለሙያ የሁልጊዜ ገጠመኝ ነው። የፈጠራ ባለሙያዎች የድካም ፍሬ የሆነው የፈጠራ ውጤታቸውን ሲመለከቱ ከፍ ያለ ደስታ የሚሰማቸውም በዚሁ ምክንያት ነው።
በጥረታቸው የገጠማቸው ፈተና ተቋቁመው፤ በስራቸው የሚቀርባቸውን ችግር ተሻግረው ያገኙትን ውጤት በትልቅ ፍስሀ ይመለከቱታል። ወጣት ኪሩቤል በፈጠራ ስራ ሂደት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ገጥመውታል። የሚታሰበውን አዲስ ነገር ወደተግባር ለማዋል የሚጠቅሙ ቁሳቁሶችን በቅርበት አለማግኘት፤ ለፈጠራ ስራው የሚጠቅመው የገንዘብ አቅም ማነስ፤ ለምርምር እና ለፈጠራ ስራ ምቹ የሆነ አካባቢያዊ ሁኔታ አለመኖር በፈጠራ ሂደት ውስጥ የገጠመው ትልቁ ፈተና እንደሆነ ወጣት ኪሩቤል ይናራል።
የፈጠራ ስራውን አሁን ላይ በብዛት አምርቶ ገበያ ላይ ለማዋልና ለማህበረሰቡ የሚሠጠው ጠቀሜታ የላቀ ለማድረግ የገጠመው የገንዘብ እጥረት ዋንኛ እንቅፋት ሆኖበታል። የኃይል እጥረት በተደጋጋሚ በሚፈጠርበት፤ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ ለኃይል ምንጭነት የሚያገለግል አማራጭ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራትና እንደሱ አይነት የፈጠራ ስራዎች በፋይናንስ ተደግፈው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበት መንገድ ሊመቻች እንደሚገባ ኪሩቤል ያሳስባል።
“ወደፊትም በፈጠራና በምርምር መስክ መቀጠልና ሀገራዊ ችግሮች የሚቀርፉ ጉዳዮች ላይ የመስራት እቅድ አለኝ፤ አሁንም ጥረት ላይ ነኝ” የሚለው ኪሩቤል በዩኒቨርሲቲ የሚማረው ትምህርት የፈጠራ ስራው በወጉ እንዳያካሂድ እንዳደረገው ይገልፃል። ነገር ግን ያለውን ትርፍ ጊዜ ለፈጠራ ስራው በማዋል ሁሌም የማሻሻልና አዳዲስ ፈጠራዎች የማከል ስራ እየሰራ መሆኑን ይናገራል።
በብዙ ጥረትና ያላሰለሰ ትጋት እውን የሚሆኑት የፈጠራ ስራዎች ሀገራዊ ጠቀሜታቸው የላቀ እንዲሆንና በኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ ያላቸው ሚና ለማጉላት ለግኝቶቹ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፤ መልዕክታችን ነው። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2012
ተገኝ ብሩ