ዘይትና ስንዴ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ይመረታል
አዲስ አበባ፦ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብሩ የፋይናንስ ተቋማት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ተገለፀ:: በመርሐ ግብሩ ትግበራ ከውጭ የሚመጣውን ዘይትና ስንዴ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውም ተጠቁሟል::
ባንኮችን ጨምሮ በፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተሳተፉበትና በሃገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ያተኮረው የውይይት መድረክ ትናንት በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ በተከፈተበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት፤የኢኮኖሚ ዕድገቱን ቀጣይነት በማረጋገጥ ለወጣቶች ብቁ የሆነ የሥራ ዕድሎችን መዘርጋትና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል::
ለዚህ ተግባራዊነት የኢኮኖሚ ማሻሻያው ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ፕሮግራሙን ለመተግበር ከፍተኛ ፋይናንስ እንደሚጠይቅና ምንጩም ከሀገር ውስጥ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል:: በዚህ ረገድ ተፈላጊውን ፋይናንስ ለማሰባሰብ የፋይናንስ ተቋማቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል::
በፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ እንዲሁም በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ዘርፍ የላቀ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ላይ የማዳበሪያ ሃሳቦችን በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት እንደሚኖርባቸውም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል::
መርሐ ግብሩ በኢኮኖሚ ማሻሻያው በተገኙ ስኬቶች ላይ በመንተራስ ያጋጠሙ መሰናክሎችን በማስወገድ እንዲሁም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ መስተጋብሮችን በመፍጠር የመደመር መርህን፣ ዕድገትን፣ ብልፅግናን እና ራዕይ የሰነቀ መሆኑን ተናግረዋል።
የውይይቱን ዓላማ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብሩን ከህዝብ ጋር በሚደረግ ውይይት ማበልፀግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ለዚህም ተከታታይ መድረኮች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል::
መድረኩ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ያሉ በርካታ ተዋናዮች፣ የባንክ ፕሬዚዳንቶች ፣የቦርድ አባላትና ኢኮኖሚስቶች በሰነዱ ላይ ሊጨመሩ የሚገባቸውን ግብአቶች እንዲሰጡ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣መርሐ ግብሩ የኢኮኖሚውን ዕድገት ከማስቀጠል አልፎ ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና ጎዳና እንደሚመራት ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል::
ኢትዮጵያ ላገጠማት ችግር የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲቀረፅ ተግባራዊ የሚደረጉ በርካታ ተግባሮች መኖራቸውን የተናገሩት ዶክተር ኢዮብ፣ዘይትና ስንዴ በሀገር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ማምረት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውስጥ መካተቱን ጠቅሰዋል::
ስንዴ በሀገራችን አምርተን ከውጪ የሚገባውን ስንዴ በሁለት እና ሦስት ዓመታት ለማስቆም ተጀምሮ እየተሰራ ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣በዚህ ዓመት ስንዴ 50ሺ ሄክታር በሚያህል መሬት ላይ ይለማል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል::
ዘይት ከውጭ ማስገባትን ለማስቆምም ትላልቅ የዘይት ፕሮጀክቶች በተለያዩ ክልሎች ተግባራዊ እየሆኑ እንደሚገኙና ከእነዚህ መካከልም የተወሰኑት በዚህ ዓመት ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል::
እንደ ዶክተር እዮብ ማብራሪያ፤እንደ ቱሪዝምና ማዕድን ዓይነት ዘርፎችን ከወደቁበት ለማንሳት መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው::የቱሪዝም ሀብትን ለማሳደግ ለተጀመረው ስራ የቤተመንግሥት ፕሮጀክት በአብነት ይጠቀሳል:: በየቦታው የተጣለውን የቱሪዝም እምቅ አቅም በመሰብሰብ ለዓለም ማሳወቅና ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል በሚል መርሐግብር ተዘርግቶ ዘርፉን ለማልማት ወደ ሥራ እየተገባ ነው::
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2012
ኃይለማርያም ወንድሙ