በአንድ ወቅት አንድ በአካባቢያቸው የተከበሩ ብልህ አዛውንት ነበሩ፡፡_አንድ ቀን ታዲያ የጎረቤታሞች ንብረት የሆኑ ሁለት ውሾች ሲጣሉ አይተው “እባካችሁ እነዚህን ሁለት ውሾች ገላግሏቸው፤ ካለበለዚያ ችግር ይፈጠራል፡፡” ይላሉ፡፡_ምክራቸውን ሰምቶ የተገበረ ግን አልነበረም፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንዱ ልጅ ከአንደኛው ቤት ወጥቶ ሁለቱ ውሾች ሲጣሉ ባየ ጊዜ ሌላኛውን ውሻ በዱላ መታው፡፡ በዚያው ቅፅበት ሌላኛው የጎረቤት ልጅ ከቤቱ እየወጣ ስለነበር የራሱ ውሻ በዱላ ሲመታ ሲያይ “ምን ብትደፍረኝ ነው ውሻዬን የምትመታው?” በማለት ሁለቱ ልጆች መደባደብ ጀመሩ፡፡_
ብዙም ሳይቆይ አንደኛዋ እናት ከቤቷ ወጥታ ልጇን እየደበደበ ያለውን ልጅ መምታት ጀመረች፡፡ ከዚያም የተመታው ልጅ እናት ወጥታ “እንዴት ብትደፍሪኝ ነው ልጄን የምትመቺው?” ብላ ሁለቱ እናቶች እርስ በርስ መደባደብ ጀመሩ፡፡_ ወዲያው የአንደኛዋ ባል ሲወጣ ሚስቱ እየተደበደበች መሆኑን ባየ ጊዜ ደብዳቢዋን መምታት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የሌላኛዋ ሴት ባል ወጥቶ ሲመለከት ሚስቱ በሌላ ወንድ ስትደበደብ ሲያይ እርሱም ድብድቡን ተቀላቀለ፡፡
ወዲያው የሁለቱ ሰዎች ጎሳዎች በመሃከላቸው ትንሽ ጦርነት ፈጠሩ፡፡ በጦርነቱም ከእያንዳንዱ ወገን ስምንት ሰዎች ሞቱ፡፡ ከዚያም የሃገር ሽማግሌዎች ተጠርተው ግጭቱን እንዲፈቱ ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ በሃገሬው ባህል መሰረት ከአንደኛው ጎሳ ለተገደለ አንድ ሰው ከሌላኛው ጎሳ አንድ ሰው መገደል ወይም አንድ መቶ ከብቶች በካሳ መከፈል ነበረበት፡፡
ይህ በመሆኑ የሃገር ሽማግሌዎቹ “ለእያንዳንዱ ለተገደለ ሰው መቶ ከብቶች ካሳ መስጠት ካለባቸው ከእያንዳንዱ ወገን ስምንት መቶ ከብቶች ለካሳ በመፈለጋቸው በአጠቃላይ 1600 ከብቶች ማለት ሲሆን ይህም ማለት ከብቶቹ በሙሉ መሄዳቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስምንት ሰዎች ከእያንዳንዱ ወገን መገደል ካለባቸው በድምሩ 16 ተጨማሪ ሰዎች ሊገደሉ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በአጠቃላይ 32 ሰዎችን ማጣት ማለት ነውና ይህ ለሁላችንም ትልቅ ሃዘን ነው፡፡ ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም” እያሉ መምከር ጀመሩ፡፡_
በዚህ ጊዜ አንድ ሌላ ብልህ አዛውንት ሰው በአካባቢው ያልፍ ነበርና “ይህ ሁሉ ችግር ምንድነው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡_እነርሱም “በጣም ትልቅ ችግር ገጥሞናል፤ በማለት ከመጀመርያው ጀምሮ የተከሰተውን ጉዳይ አስረዷቸው፡፡ አዛውንቱም ብልህ ነበሩና እንዲህ አሏቸው፡፡ “ሁላችሁም ‹ሜታ› ተብሎ የሚጠራውን ከብር የተሰራ የአንገት ጌጥ ከሁለቱም ወገን ወስዳችሁ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፡፡
ከዚያም ያለፈውን ሁሉ ረስታችሁ እርስ በርስ ይቅር ተባባሉ፡፡” በማለት የአካባቢውን ባህላዊ የእርቅ ሥነሥርዓት መነሻ በማድረግ ችግሩን መፍታት እንደቻሉ ይነገራል፡፡
አዎ ግጭት አነሳሱ እንደ እሳት ነው፡፡ እሳት ሲቀጣጠል ቀስ ብሎ በመጀመርያ እየጨሰ ይጀምርና በመጨረሻ ግን ለቁጥጥር እስከሚከብድ ድረስ ሁሉንም ብቻዬን ካልበላሁ የሚል “ሆዳም” ይሆናል፡፡ ግጭትም እንዲሁ ነው፡፡ የትኛውም ግጭት ሲጀምር ከትንሽ ትንኮሳ ወይም ከአንድ ቦታ ይጀምርና ቀስ በቀስ ግን እየሰፋና ባህርይውን እየለወጠ ይሄዳል፡፡ በተለይ በግጭት ውስጥ የሰው ህይወት መጥፋት ሲጀምር ግጭቱ የመስፋት እድሉ እየጨመረ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ በሁለት ሰዎች መካከል የሚጀምር ፀብም መልኩን ለውጦ የመንደር፣ የአካባቢ፣ የብሄር ወይም የማህበረሰብ ወደ መሆን ይሄዳል፡፡
ግጭት አሁን የተጀመረ የማህበረሰብ ቀውስ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ማህበራዊ ህይወት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አብሮ የኖረና ቀስ በቀስም እያደገ የመጣ ክስተት ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ማህበረሰቡ እንደዘመኑ የስልጣኔና የማህበራዊ ህይወት የእድገት ደረጃ ግጭቶችን የሚከላከልበትና ሲከሰትም የሚፈታበትን መንገድ አዳብሯል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ችግሮቻቸውን የሚፈቱባቸው ጠንካራ ባህላዊ እሴቶች ነበሯቸው፡፡ በነዚህ ባህላዊ እሴቶቻቸውም አማካይነት ህብረተሰቡ ጥፋተኛውን እየተቀጣና የተበደለውንም እየካሰ በሰላም ኖሯል፡፡
ያም ሆኖ ግን እነዚህ ባህላዊ እሴቶቻችን ቀስ በቀስ እየቀነሱና እየጠፉ የሄዱበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ይህ ማለት ግን ጠፍተዋል ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም ቢሆን በአገር ሽምግልናና ባህል በርካታ ማህበራዊ ችግሮች በሰላም የሚፈቱበት አግባብ አለ፡፡ በቅርቡም በጋሞ ብሄረሰብ ግጭትን የማስቆም ሃይል በአገር ሽማግሌዎች እጅ መኖሩን አይተናል፡፡ ለዘመናት የቆየው የገዳ ሥርዓትም በዴሞክራሲያዊነቱና በርካታ ማህበራዊ ችግሮችን በሰላም ከመፍታት አንፃር ያለው ፋይዳ ዛሬም ቢሆን ጠንካራ መሰረት ያለው ነው፡፡ ሌሎችም በርካታ ባህላዊ የእርቅ ሥነሥርዓቶች በአገራችን በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍታት ማህበረሰቡ ወደ ቀውስ እንዳይገባ ትልቅ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ኖረዋል፡፡
እኔም ለዛሬ መነሻ ያደረኩት የአላባ ብሄረሰብን የእርቅ ሥነሥርዓት ነው፡፡ መረጃውን ያገኘሁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂዩማኒቲስ፣ የቋንቋዎች ጥናትና የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ኮሌጅ የአማርኛ ቋንቋ፣ስነ ጽሁፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል “ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በሃላባ ብሄረሰብ” በሚል ርዕስ ኤልያስ ወላንሳ ለማስተርስ ዲግሪ ማሟያ ካቀረቡት ጥናት ነው፡፡ “ኦገቴ” የሚባለው ይህ የአላባ ብሔረሰብ ባሕላዊ ሸንጐ ግጭትን ለመፍታት ጠንካራ መሰረት ያለው እንደሆነም ጥናቱ አመላክቷል፡፡ “ኦጋቴ” በአብዛኛው ወንዶች የሚሳተፉበት ሆኖ በተወሰነ ጊዜ ወይም አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመም ከመደበኛ ጊዜ ውጭ እየተሰበሰቡ ስለብሄረሰቡ አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔ የሚያሳልፉበት ባህላዊ ተቋም ነው፡፡
የሰው ልጅ በየዕለቱ በሚያደርጋቸው የሕይወት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከመኖሪያ ቤቱ ጀምሮ እስከ አጎራባቹ በባህላዊ፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ እርስበርስ መገናኘቱ የማይቀር የተፈጥሮ ግዴታው ነው፡፡ በዚህ የርስበርስ ግንኙነት ውስጥ መልካም ግንኙነቶች እንደ መኖራቸው ሁሉ አለመስማማቶችም እንዲሁ ይኖራሉ፡፡ በሀላባ ብሔረሰብም ጎረቤትን ከጎረቤቱ የሚያገናኙት ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ በዋናነት የመገልገያ ቁሳቁስ በጋራ የመጠቀምና የመዋዋስ፣ በአዋሳኝ መሬቶች አካባቢ የግጦሽ ሣር አጠቃቀም፣ የእርሻ ማሳዎችን አንድ አካባቢና በኩታ ገጠም መጠቀምና የወሰን መገፋፋት፣ የቤት እንስሳትን ቀላቅሎ ማሰማራትና በጋራ በአንድ ኩሬ ወይም ወንዝ መጠቀም፣ የአንዱን ንብረት ያለፈቃድ መጠቀምና መውሰድ የመሳሰሉት ቁልፍ ግንኙነቶች ናቸው፡፡
ከዚህም ሌላ የሃላባ ብሄረሰብ ከሃዲያ፣ ከከምባታ፣ ከስልጤና ከአርሲ ኦሮሞ ጋር በተለያ አቅጣጫዎች ተዋስኖ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ልክ እንደ ጉርብትና የግጭት ዓይነቶች ሁሉ በሀላባ ብሔረሰብ ጐሣን ከጐሣ አለመግባባት ውስጥ የሚከቱ ቁልፍ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ማለትም የውሃ፣ የግጦሽ ሣር፣ በድንበር አካባቢ የሚገኘውን መሬት የይገባኛል ጥያቄዎች፣ በቂም በቀል ተነስቶ መኖሪያ ቤት ማቃጠል፣ እንስሳትን አለአግባብ የእርሻ ቦታዎች ውስጥ መልቀቅ፣ የሴት ልጆች ጠልፎ የማግባት ሁኔታና የቤት እንስሳት ስርቆት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የነዚህ ዓይነቶቹ አለመግባባቶች ከባድና አደገኛ የግጭት አይነቶች ተብለው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ግጭቶች ግን በኦጋቴ አማካይነት በቀላሉ ሲፈቱ ኖረዋል፡፡
ማንኛውም ባህላዊ የእርቅ ሥርዓት በሀላባ ብሔረሰብ ዘንድ ‘አገቴ ሴሪ’ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ የ ‘አገቴ’ ሥርዓት አራት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን እነርሱም በአንድ ቤት ውስጥ የሚፈጠርን ግጭት የሚፈታ ‘ሚኒ አገቴ’ በመባል የሚታወቀው ባህላዊ ተቋም ሲሆን እቤት ውስጥ አባት ወይም እናት ካልሆነም ደግሞ ታላቅ ወንድም የሚሸመግልበት ሂደት ነው፡፡ በመቀጠል ‘ቦኪ ሙሪች’ የሚባል ደረጃ አለ፡፡ ይህ ደረጃ ደግሞ በአንድ ቤተሠብ ውስጥ የተፈጠረን ችግር (ግጭት) የሚፈታ ተቋም ነው፡፡ የሚከወነውም በወንድማማቾች ቤት ግጭት ቢፈጠር ይህንን ግጭት ለማስወገድ የቤተሠቡ ታላቅ የሆነው ሰው ሰብስቦ ችግርን የሚፈታበት ሂደት ነው፡፡ ግጭቱ ግን ጠንከር ብሎ ከዚህ ደረጃ ከፍ ካለ ቀጥሎ ወዳለው ደረጃ እንዲሄድ የቤተሠቡ መሪ ያስተላልፈዋል፡፡ ቀጥሎ ያለው ደረጃ ‘ደቦ መሪቾ’ በመባል ይታወቃል፡፡ የቤተሠቡ መሪ ይህንን ጉዳይ ለጎሣ ሸንጎ (ደቦ አገቴ) አሳልፎ ሰጠ ማለት ጉዳዩ ወደ ጥላ ስር ደረሰ ማለት ነው፡፡ ይህ ደረጃ በሀላባ ሴራ ኦገቴ በሁለተኛ ደረጃ ይገኛል፡፡
የመጨረሻው የሀላባ ብሔረሰብ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ደረጃ ‘ሀላቢ አገቴ’ ወይም ‘ጎጎታ’ ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ሸንጎ ላይ ግን በብዛት የሚታዩት ጉዳዮች ዋና ዋና ጉዳዮች ለምሳሌ፡- ከአገራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን መፍታት፣ ድርቅና ረሀብ ካለ በነዚያ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገር፣ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳትና የመሣሠሉት ናቸው፡፡ ሌሎች በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው የቀረቡ ጉዳዮች ቢመጡ በየደረጃቸው ለጎሣና ለቤተሠብ ሸንጎዎች ተመልሰው እዚያው በተፈጠሩበት ቦታ እንዲታዩ ይደረጋል፡፡
እንግዲህ ይህ የአላባ ባህላዊ የእርቅ ሥነሥርዓት በአገራችን ከሚገኙ ቱባ ባህላዊ እሴቶቻችን አንዱ ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ ባህላዊ እሴቶች በየማህበረሰቡ አሉ፡፡ ቁምነገሩ እነዚህን ባህላዊ ሥርዓቶች ምን ያህል እየተጠቀምንባቸው ነው? ህብረተሰቡስ እነዚህን ባህላዊ እሴቶቻችንን ምን ያል ያከብራቸዋል የሚለው ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ዝምታ አገር ይጎዳል፡፡ “በእንቁላሉ በቀጣሽኝ” እንዳለው ልጅ እንዲህ አይነት ግጭቶች በእንጭጩ ካልተቀጩ ልንወጣው ወደማንችለው የርስ በርስ ግጭት ውስጥ ሊከቱን ይችላሉ፡፡ አሁን አሁን በአገራችን እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶችና መፈናቀሎችም ገና በእንጭጩ ያሉ ጎጂ ድርጊቶች በመሆናቸው ቶሎ ሊደረስባቸውና ከመሰረቱ ሊፈቱ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ባህላዊ እሴቶቻችን ትልቁን ድርሻ ሊወስዱ ይገባል፡፡
እኛ ደግሞ ለዚህ እጅግ የዳበረ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች አሉን፡፡ ለዚያውም አማርጠን ልንጠቀምበት የሚያስችለን፡፡ የሲዳማው፣ የኦሮሞው፣ የትግራዩ፣ የአማራው የጉራጌው ወዘተ የየራሳቸዉ ልዩ የሆነ አስጋራሚና እጅግ የተዋጣለት የችግር አፈታት ባህል ባለቤቶች ሆነን እያለ ጊዜ አመጣሽ የሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን ወደፊት እያመጣን አንተ ከዚህ ነህ፤ አንቺ ከዚያ ነሽ ውጣ፣ ውጪ ወዘተ መባባሉ ለሁላችንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ማህበረሰቡ ሳይሆን ጥቂት የማበጣበጥ አላማን ያነገቡ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ልክ እንደ ውሾቹ በመጀመሪያ እነዚህን አካላት በመለየት ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ወደ ህዝቡ ውስጥ ሰርጎ ሳይገባ በእንጭጩ መቅጨት ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የርስበርስ ግጭት ስጋት እንደተጋረጠብንና እስካሁን የታየው የግጭት አፈታት ዘዴያችን አስተማማኝ አለመሆኑን አምነን ለመቀበልና ሁነኛ መፍትሄ ለማስቀመጥስ ለምን አቃተን የሚለው ሊፈተሽ ይገባል፡፡ በተለያዩ ክልል ህዝቦች መካከል በተከሰተው ግጭት የተፈጸመው የእርስ በርስ መገዳደልና መፈናቀል ወዘተ መንስኤው ምንድነው፤ እንዴትስ ይፈቱ የሚለው ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለሀገራችን በዚህ ደረጃ ቀውስ ውስጥ መግባት ማንም ከማንም ሳይለይ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን፡፡ የሁላችንም ድክመት መሆኑን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡ ዋናው የችግራችን ምንጭ የዴሞክራሲ ባህላችን አለመዳበሩና የረባ ጥረትም አለማድረጋችን ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ራስ ወዳድነታችንና ስግብግብነታችን ያስከተለው ጣጣ መሆኑን መቀበል ይኖርብናል፡፡
በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን አፈናቅሏል፤ የብዙዎችን ህይወትም ቀጥፏል፡፡ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል፣ በቦረና አካባቢ፣ በቡራዩ፣ በሀዋሳ፣ በደቡብና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ወዘተ የተከሰቱ ግጭቶችና ያስከተሉት ኪሳራ ከፍተኛ እንደሆነ አይተናል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከአሶሳ ተነስቶ ወደ ቶንጎ ሲጓዝ በነበረ ሚኒባስ ላይ የደረሰውን የፈንጂ አደጋ ስንመለከት ደግሞ አገራችን ወዴት እየሄደች ነው የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ በቀውስ የሚታመሱ አገሮችንም ያስታውሰናል፡፡ ይህ ደግሞ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ጥያቄ ሊሆን ይገባል፡፡ ለመፍትሄውም ሁሉም የየራሱን ድርሻ ሊወስድ ይገባል፡፡
ለዘመናት በሰላም በኖርንበት መንደር አሁን ላይ አብረን መኖር እንኳን እየተሳነን አንዳችን ባለሀገር ሌሎቻችን ሀገር አልባ፣ አንዳችን ተፈናቃይ ሌሎቻችን አፈናቃይ፣ አንዳችን ተባራሪ ሌሎቻችን አባራሪ እየሆንን በእርስበርስ ጥላቻ እየተናቆርን በዚህ ሁኔታ አስከመቼ መዝለቅ እንችላለን? እናም ዛሬ ላይ እዚህም እዚያም የሚታዩትን ግጭቶች በእንጭጩ መግታት ካልቻልንስ ነገ መቆጣጠር እስከሚያቅተን የርስ በርስ ግጭት የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ እናም እናስብ፣ አሁንም ደጋግመን እናስብ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
ውቤ ከልደታ