
ሃዋሳ፡- የሃዋሳ ከተማ የውሃ አቅርቦት በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 61 ከመቶ በአሁኑ ወቅት መቶ በመቶ ማድረስ መቻሉን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ከዓለም ባንክ የፋይንናስ ድጋፍና ብድር በተገኘው 270 ሚሊየን ብር የተገነባው ይህ የውሃና ፍሳሽ ፕሮጀክት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ከትናንት በስቲያ ተመርቋል፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ ፕሮጀክቱን መርቀው ሲክፍቱ እንደገለጹት የከተማዋን የመጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት ባደረገው ርብርብ ከተማዋ የንፁሕ መጠጥ ውሃ ፍላጎቷ መሟላቱን ጠቅሰዋል፡፡ ከከተማዋ ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የውሃ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ዘጠኝ የጥልቅ ጉድጓዶችን በማጎልበት በቀን 25 ሚሊየን ሊትር ውሃ ለከተማዋ ማህበረሰብ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡ በአጠቃላይም ዕለታዊ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱ በፊት ከነበረበት 7ሺ ሜትር ኪዩብ ወደ 44 ሺህ 575 ሜትር ኪዩብ ማደጉን ሚኒስሩ ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የልማት ሥራዎች አዝጋሚ ስለነበሩ የህብረተሰቡን ቅሬታ ማስከተላቸውን ጠቅሰው ይህም አሁን ለመጣው ለውጥ መነሻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ መንግሥትም አሁን የጀመራቸው የልማት ሥራዎች የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ አቅም በመሆናቸው አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የውሃ ፕሮጀክቱ በአገሪቱ ከሚገነቡ አራት ትልልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፤ ይህ በአንድ በኩል የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ያሟላ በሌላ በኩል ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፎና ተመርቶ ለ24 ሰዓት ንፁሕ የመጠጥ ውሃን የሚያስገኝ ፕሮጀክት በመሆኑ ህብረተሰቡ በአግባቡ በቁጠባ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ለከተማዋ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት አገልግሎት መስጠት እንደሚችልም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
በፊዮሪ ተወልደ
0
0
0
0