በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ታሪክ በርካታ አስርት ዓመታትን ያስቆጠሩ ክለቦች አሉ። ከነዚህ መካከል አንድ ክፍለ ዘመን ለመድፈን ሲሶ የቀረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ብቻ ነው። ይህ አንጋፋ ክለብ በነዚህ ሁሉ ዓመታት የኢትዮጵያን እግር ኳስ ጅማሮ ከማብሰር አንስቶ በየጊዜው በሚኖረው መውጣት እና መውረዶች ውስጥ ስሙ አብሮ ሲነሳ ዛሬ ላይ ደርሷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አሁን ሰማኒያ ሶስተኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል። ይህ የእድሜ ባለፀጋነቱ ደግሞ ከክለብም አልፎ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሰፊ ድርሻ እንዲኖረው አድርጎታል። በእርግጥ የአገሪቷ እግር ኳስ በሚፈለገው ፍጥነት እና የእድገት ደረጃ ላይ ባይገኝም እጅግ ተወዳጅ የሆነው ስፖርት እንዲስፋፋ ክለቡ የአንበሳውን ድርሻ መውሰዱ የማይቀር ነው።
ክለቡ የምስረታ በዓሉን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብር ነበር። አሁንም ይሄን ባህሉን አስጠብቆ ለማክበር አስቧል። ከዚህም ሌላ ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ በአገር ውስጥ ለሚገኙ አቻ ክለቦቹ አዲስ መንገድ ለማሳየትም ቆርጦ የተነሳ ይመስላል። ስፖርትን በተለይ ደግሞ እግር ኳስን ከበጎነት እና መልካም ተግባር ጋር በማያያዝ የምስረታ በዓሉን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ይገኛል። እኛም ከደጋፊ አባላቱ እና ከስፖርት ማህበሩ አመራሮች ጋር ቆይታ አድርገናል። ወደዚያ በቀጥታ ከማምራታችን በፊት ግን በጥቂቱ ስለ ክለቡ ታሪክ ዳሰሳ ለማድረግ ወደናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ እንዴት እና መቼ?
ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ክለብ ሆኖ የተመሰረተው በአዲስ አበባ ፒያሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ነው። በታህሳስ ወር 1928 ዓ.ም በአብሮ አደጎቹ ተስፋዬ አጥናሽና ጆርጅ ዱካስ እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በወቅቱ ቡድኑ ሲመሰረት እግር ኳስ ጨዋታን በኢትዮጵያ ያደርጉ የነበሩት የውጪ ሀገር ቡድኖች ብቻ ስለነበሩ እንጂ ክለብ ለመባል እና ተፎካካሪ ለመሆን የሚያስችል አቅምና አደረጃጀት እንዳልነበረው ይነገራል። ማንኛውንም ወጪዎች የሚሸፍኑት ተጨዋቾቹ ከግል ኪሳቸው በማዋጣት ነበር። እንደቡድን ተቋቁሞ ለ11 ዓመታት በተጨዋቾቹ የግል ጥረትና ፍላጎት ከተጓዘ በኋላ በ1940 ዓ.ም ወደ ስፖርት ማህበርነት ተሸጋግሯል። በ1940 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለንተናዊ መልኩ ለውጥ በማድረግ ህዝባዊ አደረጃጀትን ተላብሷል።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ክለቡ ወደ ስፖርት ማህበርነት ሲሸጋገር ልዑል አልጋወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋወሰን የክብር ፕሬዚዳንት ነበሩ። በምስረታ ብቻ ሳይሆን በህዝባዊ አደረጃጀትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ በአዲሱ ስፖርት አደረጃጀት እስከ 1969ዓ.ም ተጓዘ። በኋላም መንግስት በአወጣው አዲስ የስፖርት አደረጃጀት መሠረት በደረሰበት የመፍረስ አደጋ ከ1970-1974ዓ.ም ከውድድር ተገልሎ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በ1975ዓ.ም ወደ ውድድር ሲመለስም በአደረጃጀትና ስያሜው ግን እንደቀድሞ አልነበረም።
ህዝባዊው ክለብ ሆኖ «አዲስ አበባ ቢራ» በሚል ስያሜ ወደ ውድድር ሲመለስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በባለቤትነት እያስተዳደረው ነበር። የቀድሞ የክለቡ ዝነኛ ተጨዋቾች ሚናም ቀላል የሚባል አልነበረም። በቋሚ ሠራተኝነት ተቀጥረው ይሰሩ ስለነበር በእነርሱና ክለቡ በነበረው የህዝብ ድጋፍ ግፊት ሊቋቋም እንደቻለ የክለቡ ታሪክ ያስረዳል፡፡
የክለቡን የሰማኒያኛ ዓመት የምስረታ በዓል በማስመልከት የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይዘውት በወጡት ዳሰሳ ላይ እንደተመለከተው በውድድር በቆየባቸው 50 ዓመታት አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለያየ ጊዜያት እና በተለያዩ ምክንያቶች የስም ለውጥ ለማድረግ መገደዱ ተገልጿል። ለመጀመሪያ ጊዜ ክለቡ የስም ለውጥ እንዲያደርግ የተገደደው በጣሊያን ወረራ ወቅት ሲሆን «ሊቶሪያ ውቤ ሠፈር አራዳ» ተብሎ ነበር። ከ1975-1983ዓ.ም «አዲስ አበባ ቢራ» ከ1984 – 1988ዓ.ም «ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ» ተብሎም በተለያዩ ውድድሮች ላይ በቢራ ፋብሪካው ባለቤትነት እንዲሳተፍ ተደርጓል።
ወደ ህዝባዊ ክለብነቱ የተመለሰው በ1988ዓ.ም መጨረሻ 60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሲያከብር ነበር። ዛሬ ስፖርት ክለቡ የሚመራው በስራ አመራር ቦርድና በቋሚ ስራ አስኪያጅ ሲሆን ቦርዱ ክለቡን በባለቤትነት ከሚያስተዳድሩ ልዩ ልዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተውጣጡ 9 አባላት አሉበት። በዚህ አደረጃጀትም እስካሁን ድረስ ቆይቶ 83ተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛል።
የክለቡ ህዝባዊ ወገንተኝነት
ወጣት ሚኒሊክ ግርማ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነው። የዘንድሮውን የምስረታ ክብረ በዓል አስመልክቶ ሲናገር «ከደጋፊዎቻችን ጋር በትብበር ነው የምናከብረው» በማለት ይጀምራል። ክለቡ በሚታወቅበት የማህበራዊ ተሳትፎ ላይ ይበልጥ ትኩረት ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ይናገራል።
የክለቡ ደጋፊዎች እና የስፖርት ማህበሩ የዘንድሮውን በዓል የጀመሩት ድጋፍ የሚያስፈ ልጋቸው የካንሰር ህሙማን መንከባከቢያ ማህበር ውስጥ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ታማሚዎችን በመጠየቅ ነበር። በተለይ ደግሞ የካንሰር ታማሚዎች አልሚ ምግብ ማግኘት ስለሚኖርባቸው ይህን በመረዳት ከ1ሺ 600 በላይ እንቁላሎችን፣ ከ1ሺ 500 የታሸገ አንከር ወተት እንዲሁም 70 ሊትር ያልታሸገ ወተት ድጋፍ አድርገዋል። ከምንም ነገር በላይ ግን ስፖርት የመተሳሰብ እንዲሁም የመደጋገፍ ዓላማን ያነገበ መሆኑን ከታማሚዎቹ ጎን በመሆን አሳይተዋል።
ወጣት ሚኒሊክ፤ የምስረታ በዓሉ በዋናነት የበጎ ስራዎችን ከማከናውን ጋር የተገናኘ ቢሆንም የክለቡን ታሪክ እና ክብረ ወሰኖች የሚያሳዩ ኤግዚቢሽኖች ብሎም የስነ ፅሁፍ ምሽቶችን እንደሚዘጋጁ ይናገራል። ከዚህ ቀደም እንደተለመደው «የደም ልገሳ» ለአስረኛ ጊዜ የሚካሄድ መርሃ ግብር ይኖራቸዋል። ከዚህ ባለፈ ታሪካዊ ተጫዋቾችን የሚያስታውስ በደጋፊዎች በስታዲዬም ውስጥ የሞዛይክ ትእይንት ይደረጋል።
«ይህን መሰል የበጎ አድራጎት እና የምስረታ በዓል አከባበር በየዓመቱ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል እንፈልጋለን» የሚለው ወጣት ሚኒሊክ፤ ለዚህ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የስፖርት ማህበራችን አባላት እና ደጋፊዎቻችን ናቸው ይላል። ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን መስዋዕት አድርገው ከሚወዱት የእግር ኳስ ክለብ እና ከወገናቸው ጋር ለመቆም ዝግጁ መሆናቸው ያስመሰግናቸዋል። ፅህፈት ቤቱ ደግሞ ይህ ባህል ቀጣይነት ኖሮት ስኬታማ እንዲሆን የማስተባበር ስራ ይሰራል።
በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር ላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለያዩ አምባ ጓሮዎች ይነሳሉ። በዚህ ተጎጂ ከመሆን በዘለለ የችግሩ ምንጭ እስከመሆን የደረሰው አንጋፋው ክለብ ክስተቱን ለመቀልበስ እና ወደ ቀድሞው ጨዋነቱ ለመመለስ የምስረታ በዓሉን ሁነቶች እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀምባቸው አስቧል።
«ክለቡን ከስሜት ወጥቶ 90 ደቂቃ መደገፍ እና ማስተዋወቅ በማንኛውም ጨዋታ ላይ ተገቢ ነው» የሚለው ወጣት ሚኒሊክ፤ ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክለቡ ደጋፊዎችም ሆነ በሌላ አካላት የሚፈጠሩ አላስፈላጊ አምባጓሮዎች ስህተት መሆናቸውን ይናገራል። ይህ ተገቢነት የጎደለው ተግባር እንዲቀርም የክለቡ ደጋፊዎችን በተለያየ መንገድ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት የማስተማሩ ስራ ቀጥሏል። በተለይ ይህን መሰል በበጎ ምግባር ላይ ተሰማርቶ ስፖርቱን እና አንጋፋውን ክለብ የማስተዋወቅ ስራ ሲካሄድ ደግሞ «ስፖርት ለመደጋገፍ፣ ለሰብአዊነት፣ ለመዝናኛ እና ለጤንነት» ብቻ የሚውል መሳሪያ መሆኑን ደጋፊዎች እንዲረዱት ለማድረግ ታልሟል።
«የክለቡ የበጎ አድራጎት ተግባር ቀደም ባሉት ዓመታትም የሚጠቀስ ነው። በተለይ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ በተስፋፋበት ወቅት ለታማሚዎች ብርድልብስ ከማቀበል አንስቶ የተለያዩ ድጋፎች ያደርግ ነበር» የሚለው ወጣት ሚኒሊክ፤ የህዝብ ክለብነቱን የሚያስመሰክርበት አንዱ መንገድ ይህን መሰል በጎ አላማዎች ላይ መሳተፍ ሲችል እንደሆነ ይናገራል።
ወጣት እሌኒ ተስፋዬ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊ እና የምስረታ በዓሉ አከባበር የኮሚቴ አባል ናት። በተለይ የበጎ አድራጎት እና ማህበራዊ አገልግሎት ስራውን ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር በመሆን እያስተባበረች ትገኛለች።
«ቅዱስ ጊዮርጊስን የምደግፈው በምክንያት ነው። ኢትዮጵያዊ ክለብ ከመሆኑ ባለፈ አገር ውስጥ ላሉ ሌሎች ክለቦች አርአያ የሚሆን ነው» የምትለው እሌኒ፤ ለመጀመሪያ ግዜም ፋሽስት ኢትዮጵያን በወረረበት በአምስቱ ዓመት ቆይታው ነጮችን በሜዳ ላይ ማሸነፍ የቻለ ክለብ መሆኑን ትገልፃለች። ከዚህም ሌላ በስፖርት አመራር ትልቅ ዝናን ያተረፉትን እና አፓርታይድን በይፋ የተቃወሙትን የኢትዮጵያ የእግር ኳስ አባት ክቡር ይድነቃቸው ተሰማን የመሰሉ ባለታሪኮች ያለፉበት ክለብ መሆኑም ከምንም በላይ ሃያል ያደርገዋል ትላለች።
ክለቡ አሁንም ድረስ ከማህበረሰቡ መውጣቱን የሚያሳዩ ተግባራት ላይ ተሳታፊ መሆኑም የሚያኮራ መሆኑን ታነሳለች። ከዚህ መነሻ ክብረ በዓሉን ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ወገኖች ጋር በተለያዩ ተግባሮች ላይ በመተባበር ለማሳለፍ መወሰናቸው እና ለተግባራዊነቱም እየተጉ መሆናቸውን ትገልፃለች።
«ክለቡ አንጋፋ እና በርካታ ሚሊዮን ደጋፊዎች ያሉት ነው። ሆኖም ሁሉም ይህንን ተረድቶ እና በሚገባ አውቆ አይደለም የሚደግፈው» በማለትም አሸናፊ ክለብ ብቻ በመሆኑ እርሱን ፈልገው የሚደግፉ ወጣቶች እየበረከቱ መምጣታቸውን ታነሳለች። ሆኖም ግን ቀስ በቀስ የሚቀረፍ ችግር መሆኑን ተናግራ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አንዳንድ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች በጊዜ ሂደት ይስተካከላሉ የሚል ዕምነት አላት።
ሌላኛው የምስረታ በዓሉ አከባበር ኮሚቴ አባል እና የክለቡ ደጋፊ ወጣት ሄኖክ አበጀ ነው። የሚደግፈው ክለብ እና ጓደኞቹ እግርኳስን ለሰብአዊነት እና ለመተባበር ዓላማ ለማዋል ቆርጠው መነሳታቸው ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረበት ይገልፃል።
«ክለባችን እና እኛ ደጋፊዎቹ ይህን መሰል የበጎ አድራጎት ስራ ላይ በየዓመቱ መሰማራታችን የህሊና እርካታን ያጎናፅፈናል» የሚለው ወጣት ሄኖክ በተለይ አሁን አሁን በስታዲየሞች ውስጥ የሚታየው ረብሻ ስፖርቱን እንደማይገልፀው ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው ይላል። ከዚህ ሌላ ክለቡ በማህበረሰቡ ተቀባይነት እንዲኖረው የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ ነው። አብዛኛው ሰው ስፖርት የሰላም፣ የመተባበር እንዲሁም የአንድነት መገለጫ መሆኑን ከተረዳ ከረብሻ ይልቅ ወደ ሰላምና መተባበር ይመጣል የሚል እምነት አለው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
ዳግም ከበደ