ጎበዝ ስህተት ስንሰራ ቆይተናል፤ ማለቴ ያለአግባብ የሰው ስም ስናጠፋ ቆይተናል፡፡ የአንድ ሰው እንኳን አይደለም፤ በጅምላ ነው ስም ስናጠፋ የቆየነው፡፡ ‹‹ወጣቱ ትውልድ አንባቢ አይደለም›› እየተባለ ስንት ጊዜ ተወቀሰ! በእርግጥ ወጣቱም መከራከሪያ አላጣም፤ ‹‹ምን የሚነበብ ነገር አለና ነው?›› እያለም ይሞግት ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ‹‹አንባቢ ነው የሌለው፣ የሚነበብ ነው የሌለው›› የሚል ክርክር የተለመደ ነበር፡፡
አይ ቅሌቴ! እኔም እኮ አንባቢ የለም እያልኩ ስንት ጊዜ ስከራከር ነበር (እኔ ራሴ አንባቢ አልመስልም?) ጉድ እንደተሰራሁ ያየሁት እኮ ሰሞኑን ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደ አሸን እየፈሉ ነው (ኢህአዴግ ስታይል)፡፡
ታዲያ እኔን የገረመኝ አንባቢም እንደ አሸን መፍላቱ ነው፡፡ ለካ እውነትም የሚነበብ አጥቶ እንጂ ይሄ ወጣት አንባቢ ነበር (ቸኩለህ እንዳትኮፈስ ገና የምንወቃቀሰውም አለን)፡፡
የምር ግን የመጽሔቶችና የጋዜጦች መብዛት በዚያው ልክ አንባቢ ትውልድ እየፈጠረ ይሆን? እስኪ ልብ ብላችሁ አይታችኋል? በየካፌው ውስጥና ጋዜጣ በሚዞርባቸው አካባቢዎች ሁሉ ጋዜጣና መጽሔት የያዘ ብዙ ወጣት ነው የሚታየው፡፡ ማህበራዊ ድረ ገጾች ራሱ ስለነዚህ ጋዜጦችና መጽሔቶች ማውራት ጀምረዋል እኮ፤ ታዲያ ይሄ ለውጥ አይደለም?
አንድ ዕለት ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ እየወጣሁ ነበር፤ ከዚህ በፊት ምንም አይነት ጋዜጣ አዟሪ አይቸባቸው የማላውቃቸው አካባቢዎችና ካፌዎች በር ላይ ጋዜጣ አዟሪ አየሁ፡፡ ወደ ውስጥ አሻግሬ ሳይ ሁለትና ሦስት መጽሔት ወይም ጋዜጣ ከፊቱ አስቀምጦ ከአንደኛው ላይ ደግሞ በተመስጦ የሚያነበው ሰው ብዙ ሆነብኝ፡፡ በእኔ ዕድሜ ከዚህ በፊት ያለመድኩት ስለሆነ ቀልቤን ያዝ አደረገው፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ልብ ብየ ማስተዋል ጀመርኩ፡፡ ብዙ አካባቢዎች የጋዜጣና መጽሔት አንባቢዎችን እያየሁ ነው፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችም አሉበት፡፡ ይሄ የጎጠኝነት ጣጣው ጎልቶ እየወጣ መሆኑን አስተውያለሁ፡፡ ጋዜጦችና መጽሔቶች ራሳቸው በመንደር ሊሆኑ ምንም አልቀራቸውም፤ አንባቢዎችም በዚያው ልክ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የሚያነቡት እነርሱ የሚፈልጉትን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ እንዲያውም ይህን ነገር ጋዜጣና መፅሄት የሚነበብባቸው አካባቢዎች ቆም ብለን መታዘብ እንችላለን፡፡ በተለይም በወጣትነት ዕድሜ ላይ ያሉት ገጽ የሚቆጥሩ የሚመስሉም አሉ፡፡ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ምስጥ ብለው ሲያነቡ ነው የሚታዩት፤ ወጣቶቹ ግን ርዕስ አይቶ ዞር የሚያደርጉት ይበዛሉ፤ እንዲያው ለእነርሱ የማይመጥን ሆኖ ይሆን? ምንም እንኳን ጥናት ቢጠይቅም እኔ ግን አንድ ግምት አለኝ፡፡
ትልልቆቹ ለጉዳዩ ቅርብ ናቸው (ይገባቸዋል ማለት ነው)፡፡ ምናልባት ወጣቶቹ ግን ከዚህ በፊት አንባቢ ካልነበሩ ቶሎ ይሰለቻሉ፡፡ የሆነ ስሜታዊ የሆነ ጽሑፍ ካልሆነ ታሪክና ፖለቲካው እያሰለቻቸው ይመስለኛል (በፌስቡክ የለመደ እኮ ረጅም ጽሑፍ ይሰለቸዋል)፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ዋናው ነገር የመጽሔቶችና ጋዜጦች መብዛት እየታየ ነው፡፡ ሁሉም ማለት ባይቻልም አንዳንዶቹ ጋዜጦችና መፅሄቶች ምርጥ ምርጥ የምርመራ ዘገባዎችን የሚሰሩ ናቸው፤ ይሄ ጥሩ ነው፡፡ ለፖለቲከኞችም ሆነ ለህዝቡ መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡ አንዳንዶቹ ግን ምንም ከፌስቡክ የተሻሉ አይደሉም፡፡ ስማቸውን መጥቀስ ባያስፈልግም ቀጥታ ከፌስቡክ ‹‹ኮፒ ፔስት አድርገው›› ማተሚያ ቤት የሚሄዱ መጽሔቶችም እንዳሉ መታዘብ ይቻላል፡፡
ወጣቶች ሆይ አንድ ነገር ልምከራችሁ (አንተን ብሎ መካሪ አይባልም!) እኛ እኮ የዚህ ዘመን ምስክሮች መሆን አለብን፡፡ አሁን አባቶችን የምንጠይቀው እኮ የኖሩበት ዘመን ምስክር ስለሆኑ ነው፡፡ አሁን ያለንበትን ዘመን እየኖርንበት ካልሆነ በቃ ምስክር መሆን አልችልም ማለት ነው፤ አልነበርንም ማለት እኮ ነው፡፡ ልጆቻችን እኮ ‹‹በዚያን ጊዜ ምን ነበር?›› ብለው ይጠይቁናል፤ ያኔ ምን ልንመልስ ነው?
የኖርንበትን ዘመን ለማወቅ ደግሞ ማንበብ፤ ታሪክን ሰንዶ ማስቀመጥ፤ እንዲያውም ከበረታን ደግሞ የታሪክ ጸሐፊ መሆን፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ዜና የሆኑ ነገሮች እኮ ከዘመናት በኋላ ታሪክ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደቀላል ማለፍ የለብንም፡፡ ስለዚህ እናንብብ፡፡ ‹‹እንደ አሸን የፈሉ›› የሚለው ለአንባቢዎችም መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
ዋለልኝ አየለ