አገራት በኢኮኖሚ አቅማቸውና በዕድገታቸው በቅደም ተከተል ለመሰለፋቸው ዋና ምክንያት የሳይንስና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን መሰረት ያደርጋል። ዓለምን ለመቆጣጠር፤ ጊዜን ለመመጠን በሳይንስና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሻሉ ሆኖ መገኘት ግድ ይላል። ለዚህም ነው ዘርፉ መጠንከር አለበት። ዘመኑን የሚመጥን ዘመነኛ ምላሽ የሚሰጥና ወቅቱን ያገናዘበ ለውጥ ይገባዋል የሚባልው፤ በሳይንስ የማይፈታ ችግር፤ የማይገኝ መፍትሄ የለም።
ለዚህም ነው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት እንደ ሀገር የሚሰጠው ልዩ ትኩረት ዘርፉ በሚያስገኘው የላቀ ውጤት ለመጠቀምና የተሻሻሉ አሠራሮች በመከተል በአቋራጭ የላቀ ውጤት ላይ መድረስ ያስችላል የሚባለው፤ የፈጠራ ሥራ የፈጣሪው አዕምሮ ውጤት የሆነና በተለያዩ ማህበራዊና እኮኖሚያዊ ችግሮች መነሻነት ችግሮቹን ለመፍታት በሚደረግ ጥረት የሚመነጭ ነው። ተመራማሪዎች አሊያም የፈጠራ ባሙያዎች የፈጠራና የምርምር ሥራቸው እውን ሆኖ ሲመለከቱ፤ የገጠማቸውን ችግር ፈትተው፣ ያለሙትን አሳክተው ውጤት ላይ ሲደርሱ የሚያገኙት የህሊና እርካታ ቀላል አይደለም።
ሳይንሳዊ ምርምሮች ችግር ፈቺነታቸው ታምኖበት ተግባዊ መሆን ከቻሉ ዛሬ ላይ ሀገራችን ከተዘፈቀችበት ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያላቅቁና ኢኮኖሚያዊ እመርታን የሚያስገኙ ለመሆናቸው ማስረጃ አያሻውም። የሚገጥሙን እያንዳንዱ ችግሮች ከጀርባቸው የሚይዙት ትልቅ የመፍትሄ ቁልፍ ደግሞ መክፈቻው ሳይንስ፤ መግለጫው ብሩህ አዕምሮ ነው።
በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚደረጉ ጥረቶች ጅምር ላይም ሆነው የሚያመላክቱት ውጤት አበረታች ቢሆንም፤ በሀገር ደረጃ ብዙ መሥራት እና ልዩ ትኩትት የሚያሻው ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎች መጥቀስ ይቻላል። በግለሰቦች ደረጃ በሚደረግ ብርቱ ጥረት የሚፈጠሩ የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ውጤቶች ትልቅ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።
ተመራማሪና የፈጠራ ባሙያዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ የሚያደርጉት የላቀ ተሳትፎ እየተጠናከራ በሄደ ቁጥር በማህበረሰባችን ዘንድ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በአጭር ጊዜ እልባት ሊገኝላቸው ይችላል። በተለያዩ ተቋማትና በመንግሥት ድጋፍ ሳይደረግላቸው የምርምርና የፈጠራ ሥራቸውን በራሳቸው ብርቱ ጥረት ብቻ ከስኬት ላይ የሚያደርሱ የፈጠራና የምርምር ባለሙያዎች በሀገራችን የተለየዩ አካባቢዎች የሚገኝ ማህበረሰብ ችግር የመቅረፍ ዕቅድና ህልማቸውን በማሳካት ላይ ይገኛሉ።
መምህራን ሁሌም ተመራማሪ፤ ሁሌም ፈጣሪ ናቸውና በምርምርና በፈጠራ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። ከሚያስምሩት ትምህርት ባለፈ የሚመለከቱት የማህበረሰቡ ችግር ለምርምር ሥራቸው መነሻ ሆኖ የተለያዩ መፍትሄዎችን አበጅተው ለማህበረሰቡ በማቅረብ የላቀ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
ከመማር ማስማር ተግባራቸው ባለፈ ተማሪዎቻቸውን በቀለም ትምህርት ቀርፀው በእውቀት የጎደለውን አዕምሮዋቸው በቀለም ከመሙላት በተሻገረ ሃላፊነት በፈጠራ ሥራቸው ስኬታማ የሆኑ መምህር ስለ ፈጠራ ሥራቸው ምንነት፤ የፈጠራ ሥራቸው አሁን ያለበት ደረጃና በፈጠራ ሥራቸው ያገኙትን ውጤት እና የወደፊት ህልማቸውን በወፍ በረር ለመዳሰስ እንሞክር።
መምህር አዲሱ ደሴ ይባላሉ። በአማራ ብሔራዊ ክልል አዊ ዞን ቲሊሊ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርና የፈጠራ ባለሙያ ናቸው። አቶ አዲሱ አካባቢያቸው ላይ የተመለከቱትን ችግር ለመቅረፍ የሚታትሩ፤ መላ የሚዘይዱ የቲሊሊ “አባ መላ” ናቸው። አቶ አዲሱ የሚያስምሩት የኬሚስትሪ ትምህርት ለምርምር ሥራቸው ጅምር መሰረት ጥሎላቸዋል። የሚያስምሩበት መጽሐፍ ተማሪዎቻቸውና የማስተማሪያ ቁሳቁሶች ደግሞ ለምርምር ሥራቸው ግብዓት በመሆን ምርምር ‘ሀ’ ብለው ጀምረው በማስፋት ዛሬ ላይ ከ13 ያላነሱ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን ለማህበረሰቡ በማበርከት ትልቅ ለውጥ መፍጠር የቻሉ ታታሪ መምህር ናቸው።
ዋነኛ ሥራቸው ማስተማር ቢሆንም፤ የሚያዩትን ችግር በለዘብታ ማለፉ አልሆን ቢላቸው ከቀለም ትምህርት ማስተማር ባሻገር በፈጠራ ሙያ ያላቸውን ክህሎት በመጠቀም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይጀምራሉ።
የበዛ ጊዜና ትኩረታቸውን የሰጡት የፈጠራና የምርምር ሥራ ለመምህርና የፈጠራ ባለሙያው አቶ አዲሱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደጋጋሚ ተወዳድረው አሸናፊ መሆን አስቻላቸው። ችግርን አይተው እንዴት ብፈታው ይሻላል ሳይሉ የማያልፉት ትጉሁ ሰው ከተመለከቱት የመማር ማስተማሪያ ቁሳቁስ ፈጠራ ውጭ በአካባቢያዊ ችግር መነሻነት የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ማበርከት ችለዋል።
መምህርና የፈጠራ ባለሙያ የሆኑት አቶ አዲሱ ከ13 ያላነሱ የምርምር ሥራዎች የማበርከታቸው ምክንያት ጠንካራና ብርቱ ሠራተኝነታቸውና ለሙያው ያላቸው ፍቅር መሆኑ ልብ ይሏል። ከሠሩ የሥራን ውጤት ማግኘት የተለመደ፤ ከጣሩ የጥረትን ፍሬ መቋደስ ተፈጥሮአዊ ሕግ ነውና የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ባለቤት መሆን አስቻላቸው።
ከምርምርና ፈጠራ ሥራቸው በተጨማሪ፤ በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት የፈጠራና የምርምር ሥራ ለማካሄድ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች በማገዝ ለፈጠራና ለምርምር ሥራ እራሳቸውን እዲያዘጋጁና የተሻለ ውጤት በዘርፉ እንዲያስመዘግቡ በመርዳት ላይ ይገኛሉ።
የፈጠራ ሥራው ምንነት
መምህርና የፈጠራ ባለሙያው አቶ አዲሱ የሠሯቸው የፈጠራ ሥራዎች በቁጥር 13 ሲሆኑ፤ በአሁን ወቅት ተግባራዊ በማድረግ እውቅና ሽልማት ያገኙባቸው፡-ፀረ ተባይ መድሃኒት፤ ነዳጅ፤ ቀለም፤ ሰንደል፤ ሽቶ፤ የኬሚስትሪ ትምህርት ቀመር፤ የተለያዩ የቤተ ሙከራ ኬሚካሎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ሁሉም ከተረፈ ምርት የሚዘጋጁና ጥቅማቸው የላቀ መሆኑን ተመራማሪው ይናገራሉ።
የፈጠራ ባለሙያውና መምህሩ አቶ አዲሱ የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳየት እነዚህን በዋናነት ጠቀስን እንጂ በሌሎች ቁጥራቸው የበረከተ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች በመሥራት አካባቢያዊ ችግሮችን በመቅረፍ ላይ ይገኛሉ። በተለይም በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ ገበሬዎች የተፈታተናቸውንና ምርት በመቀነስ ሠርተው እንዳይጠቀሙ ያደረጋቸውን የበቆሎ ተምች ለማጥፋት ያስችላል። የፀረ ተባይ መድሃኒቱ በራሳቸው መንገድ የተለያዩ ግብዓቶችን በመጠቀም የተሠራና ውጤታማ መሆኑንም ይገልፃሉ።
ለፈጠራ ሥራው ያነሳሳው ምክንያት፡-
ምርምርና የፈጠራ ሥራ መነሻው አካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ችግር መሆኑ እሙን ነው። ፈጠራ ወይም ምርምር ያጋጠመን ችግር ለመፍታት የሚያደረግ ሙከራ አሊያም ደግሞ ያለውን ለማሻሻልና የተሻለ ጥቅም እና አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ ወይም ተግባር ነው።
በተለይም በአንድ ምርምር በማህበረሰብ የሚከሰትን ችግር መፍታትና መፍትሄ ማስቀመጥ ፍላጎት መኖር ለምርምር ሥራው ጋባዥ ምክንያት ነው። የመምህር አዲሱ ወደ ምርምር ሥራው መግባት ምክንያትም ይሄው ነው። መምህርና የፈጠራ ባለሙያው አቶ አዲሱ በሚኖሩበት አካባቢ ያለውን የገበሬዎች ችግር እና በሚያስምሩት የትምህርት አይነት ላይ ያለ የመርጃ መሣሪያ እጥረት ለመቅረፍ ባላቸው ውስጣዊ ፍላጎት የምርምርና የፈጠራ ሥራቸው መነሻ ሆኗቸዋል።
ወደ ምርምር ሥራው ከመግባታቸው በፊት ደጋግመው ችግሮቹን መፍቻ መንገድ ያስቡ የነበሩት ተመራማሪና የፈጠራ ባለሙያው አቶ አዲሱ ምርምር እና ፈጠራ ለመጀመር ሙከራዎችን ማድረግ ጀመሩ። የሚገጥማቸውን ችግር በመቋቋም ሙከራቸውን ሳያቋርጡ እዚያው አካባቢ ባለ እና በሚታይ ችግር ላይ ሙከራዎችን ለማድረግ ቆረጡ።
ለማሳካት ያሰቡት እና ለመፍታት ያቀዱት ችግር ሰምሮ ዛሬ ላይ የበዙ የምርምር ውጡቶችን ለማበርከት በቁ። በዚህም በወረዳ፣ በዞን፣ በክልልና ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ በምርምርና በፈጠራ ሥራ ተወዳድረው ማሸነፍና ሽላማቶችን ማግኘት ቻሉ።
በፈጠራ ሥራው የተገኘ እውቅናና ሽልማት
የሠሩትን ሥራ ወደማህበረሰቡ ደርሶ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግና ፈጣሪውን ለማበረታታት እውቅና መስጠት ትልቁ ተግባር ነው። አሁን በሀገር ደረጃ ለተመራማሪና ለፈጠራ ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት መስጠት የተዘወተረ ተግባር ሆኗል። መምህሩና የፈጠራ ባለሙያው አቶ አዲሱ በምርምርና በፈጠራ ሥራቸው ከተለያዩ አካላትና ተቋማት እውቅናና ሽልማት አግኝተዋል።
በተጨማሪም፤ ከሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት፤ ከወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት፤ ከዞን፤ በክልል ደረጃ፤ የምርምርና የፈጠራ ሥራ ከሚሠሩ ተቋማት፤ ከክልልና ከፌዴራል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተሰጡ የተለያዩ የምስክር ወረቀቶች፤ የገንዘብ፤ የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማቶች ለመምህሩ የምርምር ሥራ እውቅናና ማበረታቻዎች ተጠቃሾቹ ናቸው።
የምርምርና የፈጠራ ባለሙያና መምህሩ አቶ አዲሱ በፈጠራና ምርምር ሥራ ያገኙዋቸው እውቅናና ሽልማቶች በፈጠራ ሥራቸው የሚያገኙት ውጤት አጠንክሯቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሦስት ጊዜ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚዘጋጀው የፈጠራ ሥራ ውድድር ላይ በመሳተፍና አሸናፊ በመሆን የወርቅ፤ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል።
የፈጠራ ሥራዎቹ አሁን ያለበት ደረጃ
“በግለሰቦች ጥረት ተግባራዊ የሚሆኑ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች በአቅም ማጣት ምክንያት የጅማሬያቸውን ያህል አይቀጥሉም” የሚሉት ተመራማሪው አቶ አዲሱ የእርሳቸው የተወሰኑት የፈጠራና የምርምር ሥራዎች በግል ጥረታቸው ተግባር ላይ ውለው ጥቅም እየሰጡ ቢሆኑም፤ አንዳንዶቹን ግን ወደተግባር ለመለወጥና ውጤታማ ማድረግ አለመቻላቸውን ይናገራሉ።
“የምርምር ሥራ በወረቀት ተዘጋጅቶ በመደርደሪያ ላይ መቀመጡ ምንም ፋይዳ የለውም” የሚሉት ተመራማሪው አቶ አዲሱ፤ “በተለየዩ ግለሰቦች የተፈጠሩና ብዙ አገልግሎት መስጠት፤ ለለውጥም ምክንያት የሚሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ተግባራዊ ሳይሆኑና ወደ ምርት ሳይደርሱ የሚቀሩበት አጋጣሚ ብዙ ነው” በማለት የምርምር ሥራ ወደ ተግባር መለወጥ ወሳኝ ተግባር መሆኑን ያስረዳሉ።
አንድ የፈጠራ ወይም የምርምር ሥራ ተግባራዊ ሆኖ የታለመለትን ችግርን መቅረፍ ካልቻለ በመፈጠሩ በራሱ ካለመፈጠር የሚለየው የለም። በሀገር ደረጃ የፈጠራ ሥራ ውጤታማ ሆኖ ከግብ እንዲደርስና ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል መስራት የሚገባ መሆኑን ይገልፃሉ። “የፈጠራ ባለሙያዎች ክህሎት ማሳያና የአዕምሮ ውጤት የሆኑት ፈጠራዎች ለጥቅም ለማዋል መሥራት ከባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቅ ተግባር ነው፤” ሲሉ አቶ አዲሱ ይገልፃሉ።
“በግለሰብ ደረጃ በግል ጥረት የሚፈልቁ የፈጠራ ሥራዎች ተግባር ላይ ቢውሉና ወደ ምርት ሂደት ቢሸጋገሩ ለሀገር የሚሰጡት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አላቸው” በማለት የሚያስረዱት አቶ አዲሱ፤ “ነገር ግን የፈጠራ ባለሙያዎች ያለባቸው የገንዘብና የቁሳቁስ ችግር ትልቅ እንቅፋት እንደሆነና ይህም ሊቀረፍ የሚገባው ችግር መሆኑን ያስረዳሉ።
ወደፊት ብዙ የምርምር ሥራዎችን የመሥራት ዕቅድ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ አዲሱ፤ ለምርምር ሥራዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠር ለእርሳቸው የምርምር ሥራ እገዛ እንደሚያርግና በሀገር ደረጃ የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲበራከቱና አመርቂ ሥራ መሥራት የሚያስችላቸው መሆኑን ይናገራሉ። ለፈጠራ ሥራ ምቹ የሆነ አካባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር ሀገራዊ የምርምር ሥራዎችን የሚያጠናክር ችግር ፈች የሆኑ የፈጠራ ውጤቶችን የሚያስገኝ ነውና የባለ ድርሻዎቹ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥል! መልዕክታችን ነው። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2012
ተገኝ ብሩ