በአንድ ወቅት አንድ ሰውዬ የጉበት በሽታ በጣም ያመውና ሃኪሙን ያማክረዋል። ሃኪሙም ሙያው በሚጠይቀው መንገድ ቀስ ብሎ «በቃ አንተ ሰውዬ ጉበትክ ከዚህ በኋላ በጣም አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል መሞትክ ነው» ብሎ ይነግረዋል። ከዚያ ወደ ሰፈር ይሄድና ያገኘውን ሰው ሁሉ ሰላም እያለ ምን ሆነሃል ባክህ ሰውነትህም አያምርም ደህናም አይደለህም? ይለዋል፤ እሱም ኤች አይ ቪ ኤድስ ይዞኛል እባክህ መሞቴ ነው ይለዋል። ወደ ሌላኛውም ይሄድና ሰላም ሲባባል ምን ሆነሃል ሲሉት ሁሉንም ኸረ ኤድስ ይዞኛል ይላቸዋል። ከዚያን ሚስቱ ግራ ገባትና አንተ ሰውዬ ዶክተሩ እኮ ጉበት ነው ያመመክ ነው ያለህ፤ ለምንድ ነው ኤች አይ ቪ ነው የያዘኝ እያልክ እራስክን የምታስጨንቀው? ስትለው «ዝም በይ ባክሽን እኔ ከሞትኩ በኋላ ማንም ወደ አንቺ እንዳይመጣ ብዬ ነው» አላት ይባላል።
የዘንድሮው የዓለም የኤድስ ቀን የተባበሩት መንግስታት የፀረ ኤድስ ፕሮግራም/ ዩ ኤን ኤድስ/2018 እ.ኤ.አ የአለም የኤድስ ቀን አከባበር «ለኤች አይ ቪ ይበልጥ ተጋላጭ ነን እንመርመር ራሳችንን እንወቅ /Know your status/ በሚል የወጣ መሪ ቃል ነበር፤ ማዕከላዊ ሀሳቡም ሶስቱን ዘጠናዎች ማሳካት ነው። ይህም ሲባል እ.ኤ.አ በ2020 ከኤች አይ ቪ በደማቸው ከሚገኝ ወገኖች 90 በመቶ ራሱን ያውቃል፤ ከኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ዜጎች 90 በመቶ የፀረ ኤች አይ ቪ ህክምና ይጀምራሉ፤ 90 በመቶ ህክምና ያገኙት ዜጎቻችን በደማቸው ውስጥ የሚገኘው ቫይረስ መጠን በሚፈለገው ልክ ይቀንሳል፡፡ በ2017 መረጃም በአለም አቀፍ ደረጃ 75 በመቶ ከኤች አይ ቪ ጋር የሚኖሩ ራሳቸውን አውቀዋል፤ ከነዚህም 79 በመቶ የፀረ ኤች አይ ቪ ህክምና ያገኙ ሲሆን 81 በመቶ ደግሞ የቫይረሱን ጫና ለመቀነስ ችለዋል።
ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣር በመንግስት፣ በህዝብና በአጋር ድርጅቶች በተደረጉ ጥረቶች በሀገራችን አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም አሁንም ኤች አይቪ ኤድስን በመከላካል እና በመቆጣጠር ረገድ ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል።
ህዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም በዱከም ከተማ የአለም የኤድስ ቀን በተከበረበት ላይ የኔፕ ፕላስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ መኮንን ዓለሙ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ያለ ሰው አስፈላጊውን ክትትልና ህክምና በማድረግ እንደ ማንኛውም ሰው ፖዘቲቭ የሆነ መልካም ኑሮ መኖር እንደሚችል የሚመክር አስተላልፈዋል። አቶ መኮንን እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት ሃገራችን የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ምላሽ በተጠናከረ ሁኔታ ንቅናቄ በመደረጉ ስርጭቱን መግታት እና ቫይረሱ በሀገር እና በህዝብ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ከፍተኛ የሆነ የጤና የማህበራዊና የስነልቦናዊ ቀውስ መቀነስ ብሎም ማስቀረት መቻሉ ከማንም በላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖችና ቤተሰቦች ለተገኘው ውጤት መሪ ተዋናይና ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ላለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስትና ዜጎች ለቫይረሱ ትኩረት ባልሰጡበት፥ ስለበሽታው ግንዛቤና እውቀት ባልዳበረበት ጊዜ ጀምሮ ቀድመው የወረርሽኙን አሳሳቢነትና ተጽዕኖውን በመረዳት ትውልድ ይዳን በኛ ይብቃ በማለት አድሎውና መገለል ሳይበግራቸው በስቃይና በሞት አፋፍ ሆነው ዝምታውን ሰብረው በመውጣት የቫይረሱን ስርጭት መከላከል ተፅዕኖውንም አጉልቶ በማሳየት ወረርሽኙን መቀልበስና በሃገር እና በህዝብ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ተፅዕኖ በማስቀረት ለተገኘው ውጤት ጉልህ ድርሻ ማበርከታቸው አሁንም በማበርከት ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
ለዚህም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን ርብርብ በተጠናከረ ሁኔታ ማስቀጠል ካልተቻለ ለቀጣይ ፈተና ከመሆኑም ባሻገር እንደሃገር በ2020 በኤች አይ ቪ የመያዝ ምጣኔን እና ቫይረሱ የሚያስከትለውን ሞት እና ተፅዕኖ ለመግታት የተያዘውን እቅድ እንዲሁም በ2030 ኤች አይ ቪ ኤድስ የህብረተሰብ ጤና ችግር በማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት አዳጋች እንደሚሆን ከሁሉም በላይ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍሎች በይበልጥ ይረዳሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ስለሆነም በሁሉም ደረጃ ያሉ አመራሮች የቫይረሱን ተፅኖና ስርጭቱን ለመቀነስ አጀንዳ በማድረግ በቀጣይነትና ቀጣይነት ያለው አመራር በመፍጠር በተለይ በወጣቱና ማህበረሰቡ ዘንድ ኤች አይቪ ኤድስ የሌለ እስኪመስል ድረስ እየተቀዛቀዘ የመጣውን ጥንቃቄና የመከላከል ስራ ይበልጥ አጠናክሮ እና አነቃቅቶ መቀጠል ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል። የፀረ ኤችአይቪ ህክምና አቅርቦትንም በተመለከተ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች ላይ ባመጣው የጤና፣ የስነልቦና እና የማህበራዊ አዎንታዊ ለውጥ አምራች ጤናማ እና ውጤታማ ህይወት እንዲመሩ ማስቻሉም ትልቅ ስኬት ነው ብለውናል።
ከዚህም ጎን ለጎን በህብረተሰቡ በተለይም በወጣቱ እና በአዲሱ ትውልድ ኤች አይ ቪ ኤድስ የሚያስከትለውን ሁለንተናዊ ተፅእኖ በግልፅ የሚያይበትና የሚረዳበት ሁኔታ ባለመኖሩ በእለት ከእለት ህይወታቸው ይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚያደርጉ ባህሪና ተግባር ውስጥ ገብተዋል።
በሀገራችን በየዓመቱ አዲስ በኤች አይ ቪ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በመቀነስ እ.ኤ.አ በ2020 እናሳካዋለን ያልነውን የሶስት ዘጠና ግቦች እና የመከላከል ፍኖተ ካርታ ላይ የተቀመጡትን ተግባራት ለማሳካት ጠንካራ ስራ ይጠብቀናል። ምንም እንኳን የስርጭት ምጣኔው እንደ አገር የቀነሰ ቢሆንም ከክልል ክልል የተለያየ ሲሆን የአብዛኛዎቹ ክልሎች የስርጭት ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑ፤ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም የስርጭቱ ሁኔታ ከአጠቃላይ ማህበረሰቡ በእጅጉ እንደሚለይና ከፍተኛ እንደሆነ እና ወጣቶች በተለይም የሴቶች ለኤች አይቪ ተጋላጭነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
በተለይ በሴት እህቶቻችን ላይ ያለው ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች በስፋት ያሳያሉ። በተባበሩት መንግስታት መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳምንት 7000 እድሜያቸው ከ15-24 ያሉት ወጣት ሴቶች በቫይረሱ ይያዛሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገሮች በበሽታው ከሚያዙ እድሜያቸው ከ15 እስከ 19 የሆኑ አራት ወጣቶች መካከል ሶስቱ ሴቶች ናቸው። እንዲሁም እድሜያቸው ከ15-24 የሆኑ ወጣት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ሁለት እጥፍ ከበሽታው ጋር ይኖራሉ።
በሀገራችን ኢትዮጵያም በተደረገ ጥናት መሰረት ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ቋሚ የወሲብ ደንበኛ ከሌላቸው ሰዎች ውስጥ 20% ሴቶች እና 51% ወንዶች ብቻ ኮንዶም ተጠቅመዋል። ቀሪዎቹ 80% ሴቶች እና 49% ወንዶች ኮንዶም አልተጠቀሙም። ከዚህም እንደምንረዳው በተለይ በሴቶች ላይ ከፍተኛ የተጋላጭነት ሁኔታ መኖሩን ነው።
በተለይ የሴቶችን በቫይረሱ የመያዝ አጋጣሚዎች መከላከል በሀገር ደረጃ በሽታውን ለመከላከል ትልቅ ድርሻ እንዳለው በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ስለዚህ መንግስት ብሎም ባለድርሻ አካላት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትንም ከመከላከል እንዲሁም የኑሮ ዘይቤን ከመለወጥ አንፃር የሴተኛ አዳሪነትን ሁኔታ በማየት አስፈላጊውን የመከላከል እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።
በተያያዘም እ.ኤ.አ በ2020 ኤድስን በመግታትና የማህበረሰብ ጤና ችግር እንዳይሆን ለማድረግ የተያዘውን አገራዊ ራዕይ ለማሳካት ተጋላጭነትን ትኩረት ያደረገ የኤች አይ ቪ ምርመራና ምከር አገልግሎት እና ጠንካራ የሆነ የትስስርና የቅብብሎሽ ስርዓት በመዘርጋት ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች በአስቸኳይነት ስሜት የድጋፍና ክብካቤ እንዲሁም የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት እንዲያገኙ በማድረግ መሰራት ይኖርበታል። ከዚህ ጎን ለጎን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት መስጠትና ህክምናውን የጀመሩ እንዳያቋርጡና የሚያቋርጡ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት የሚያስችል ስልት መዘርጋት አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
በኃይሉ አበራ