በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የእግር ኳስ ሜዳዎችን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ዛሬ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የመስክ ምልከታ እንደሚያደርጉ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ በሆኑት ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የእግርኳስ ሜዳዎችን ዛሬ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ሲጎበኙ የአዲስ አበባ ወጣቶች ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለሰማዕት መርሀ ጥበብ እና የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይለኢየሱ ፍስሀ (ኢንጂነር) እንዲሁም ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት እንደሚገኙ ታውቋል።
ቡድኑ በጉብኝቱ ከሚያካትታቸው የእግር ኳስ ሜዳዎች መካከል ያለፉትን ሁለት ዓመታት በግንባታ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆመው እና አሁን ግንባታው ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሶ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የአበበ ቢቂላ ስታድየም አንዱ ሲሆን፤ ለረጅም ጊዜያት ግንባታው ያልተጠናቀቀው እና አሁን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው የአቃቂ ስታድየምም ይገኝበታል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢምፔሪያል አካባቢ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ ከአስር ዓመት በላይ ያስቆጠረው እና እስካሁን በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ያልተጠናቀቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ሊያስገነባው ያሰበው ስታድየም የጉብኝቱ አካል ሲሆን፤ ጀሞ አካባቢ በቅርብ ዓመታት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ስታድየም በጉብኝት ሥነ ስርዓቱ ተካቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የሚጎበኙ ሲሆን ምክትል ከንቲባው ከጉብኝቱ ባሻገር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ አቅጣጫ ያስቀምጣሉም ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
ቦጋለ አበበ