ህብረተሰቡ በሚኖርበትና በሚሰራበት አካባቢ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማዘውተር ጤናማ እንዲሆን የስፖርት ፖሊሲው ይደነግጋል። ሰራተኛው ማህበረሰብ በብዙ ተቋማት በሚሰራበት አካባቢ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በስፋት ሲሳተፍ ባይስተዋልም ዓመታዊ የሰራተኞች ስፖርት ውድድሮች ላይ ሲሳተፍ ይታያል። ይህም የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ)በዓመት የተለያዩ መርሃግብሮች የሚያከናውናቸው የተለያዩ የስፖርት መድረኮች ናቸው። ከነዚህ የኢሠማኮ የስፖርት መድረኮች ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውም ዓመታዊው የሰራተኞች የበጋ ወራት የስፖርት ውድድር በጉልህ ተጠቃሽ ነው።
የሰራተኞች የበጋ ወራት የስፖርት ውድድር በአገራችን ስፖርት ታሪክ መካሄድ ከጀመረ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረና አንጋፋ ከመሆኑ ባሻገር አገርን ወክለው የመካከለኛና ምስራቅ አፍሪካ(ሴካፋ) ዋንጫን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች መሳተፍ የቻሉ ስፖርተኞችን ያፈራ ስለመሆኑ ይነገራል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት የተለያዩ ማህበራትን እያሳተፈ የሚገኘው ይህ ውድድር የመገናኛ ብዙሃን ትኩረትን እየሳበ ይገኛል። ይህም አዳዲስ ተሳታፊ ማህበራትን ወደ ውድድር ከመሳብ በዘለለ ቀድሞ ዝነኛ ተፎካካሪ የነበሩና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከውድደሩ የራቁ ማህበራትን ወደ ውድድር እየመለሰ ይገኛል።
ኢሠማኮ የሚካሄደው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ሦስት አይነት ገፅታን የተላበሰ ከፉክክርም በላይ በርካታ አላማዎችን የሰነቀ የስፖርት መድረክ መሆኑን የኢሠማኮ ማህበራዊ ክፍል ሃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍሰሃፂዮን ቢያድግልኝ ይናገራሉ። ረጅም ወራትን ሠራተኛው በስፖርት አማካኝነት አብሮነቱን የሚያጠናክርበትና ልምድ የሚለዋወጥበት የበጋ ወራት የስፖርት ውድድር የበርካታ ድርጅትና ተቋማት ሠራተኞችን ማዕከል ያደረገ የውድድር መድረክ ሲሆን፤ የሠራተኛውን ዓመታዊ በዓል ታኮ የሚካሄደው የሜይ ዴይ ውድድር ሌላኛው አካል ነው። ክረምት ወራት ላይ በውቡ የወንጂ ሁለገብ ስቴድየም የሚካሄደው አገር አቀፍ የሠራተኞች ውድድርም በድምቀቱና አገር አቀፍ ሠራተኞችን በአንድ ላይ ለሁለት ሳምንታት በትንሿ ከተማ ይዞ የሚከርም ነው።
ሦስቱም የውድድር ገፅታዎች ሠራተኛውን ከማቀራረብና ልምዱን እንዲለዋወጥ እድል ከመፍጠር ባሻገር በሠራተኛው መካከል ቤተሰባዊ ስሜት እንዲጎለብት ሚናቸው ቀላል እንዳልነበረ ባለፉት ዓመታት ውድድሮች ለመታዘብ ተችሏል።
በነዚህ ውድድሮች ቀደም ሲል በተለይም የእግር ኳስ ስፖርት ደማቅና የተሻለ ፉክክር እንዲኖረው በማሰብ ከሰራተኛው በተጨማሪ አንድ ማህበር ሁለት ወይንም ሦስት ሰራተኛ ያልሆኑ ተጫዋቾችን ማካተት ይፈቀድለት ነበር። ይህም ውድድሩ የሰራተኛው ብቻ ሆኖ ሳለ ሌሎችን ማካተት አዘጋጆቹን ሲያስወቅስ የነበረ ጉዳይ ነው። ዘንድሮ ግን ማህበራቱ በየትኛውም ውድድር ከሰራተኛ ውጪ አንድም ተጫዋች እንዳያካትቱ መወሰናቸውን ተከትሎ የሰራተኛው ስፖርት የሰራተኛው ብቻ ሆኖ እንደሚቀጥል አቶ ፍሰሃፂዮን ገልፀዋል።
ከታህሳስ አንስቶ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ የሚዘልቀው ይህ ትልቅ የስፖርት መድረክ ነገ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከማለዳው ሁለት ሰዓት አንስቶ እንደሚጀመር የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል ሃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ለአዲስ ዘመን ገልፀዋል። ይህ ውድድር ቀደም ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ ስቴድየም ተጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሲከናወን ቆይቶ መቋጫውን አዲስ አበባ ስቴድየም የሚያደርግ ቢሆንም ነገ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ጅማ አባ ጅፋር የግብፁን አል አህሊን በመግጠሙ ምክንያት የቦታ ለውጥ እንደተደረገ ታውቋል።
ከዓመት ወደ ዓመት የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ በመጣው የበጋ ወራት የሰራተኞች ስፖርት ውድድር ዘንድሮ ከአርባ በላይ ማህበራት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል። ከነዚህ ማህበራት የተውጣጡ 1215 ወንዶችና 245 ሴቶች በአጠቃላይ በ1460 ሰራተኞች አስር በሚሆኑ የስፖርት አይነቶች ተሳታፊ ይሆናሉ።
ትልቅ ትኩረት በሚሰጠውና ከፍተኛ ፉክክር በሚያስተናግደው የእግር ኳስ ውድድር ሃያ ሰባት ማህበራት የተውጣጡ 675 ሰራተኞች ተሳታፊ ይሆናሉ።
የወንዶች ቮሊቦል ውድድር ከአስር ማህበራት 150 ሰራተኞችን ሲያሳትፍ በሴቶች ከአምስት ማህበራት 75 ሰራተኞች ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ ታውቋል።
ከፍተኛ ፉክክር በሚደረግበት የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በወንዶች አስራ ሁለት በሴቶች አምስት ማህበራት ተሳታፊ ናቸው። በዳርት፤ በዳማ ጨዋታ ፤ በከረንቦላ፤ በቼስ ስፖርት ፤ በገበጣ፤ ገመድ ጉተታና አትሌቲክስ ውድድሮችም በርካታ ማህበራት ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል። ከዚህ ቀደም ባልነበረው የቅርጫት ኳስ ውድድርም በሴቶች መካከል እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ውድድሩ ነገ በይፋ ሲከፈት በተለያዩ ውድድሮች የመክፈቻ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። በእግር ኳስ በሚካሄደው የመክፈቻ ጨዋታ አንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ከኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ(ኮካ ኮላ) ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ተጠባቂ ነው። በሴቶች መካከል የሚካሄደው የስምንት መቶ ሜትር የሩጫ ውድድር እንዲሁም በወንዶች መካከል የሚካሄደው የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የአትሌቲክስ ፉክክርም ይኖራል። ከዚህ በዘለለ አዝናኝ በሆነው የገመድ ጉተታ ውድድር በሁለቱም ፆታ የፍፃሜ ውድድር እንደሚካሄድ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
ቦጋለ አበበ