ሰውየው የጎረቤት ምቀኛ ይገጥማቸውና ሁልጊዜ በሆነ ባልሆነው ይነጋገራሉ፤ ይጣላሉ፤ በአጥር ወሰን ይጋጫሉ። በቤት እንስሳት፣ በልጅ…ትልቅ ትንሹ ሁሉ ያነጋግራቸዋል። በተለይ አንደኛው ጉረቤቱ ምንም በጎ ነገር ቢያደርግለት ስሙን በክፉ ያነሳው እንደሆን እንጂ የትም ቦታ በምንም ጉዳይ በቀናነት ስሙን አይጠራም።እንዳውም ይባስ ብሎ በዱር ከብቶችህ ከብቶቼን ተቀላቀሉ ማለት ሁሉ ይከጅለዋል። ውስጠ ምቀኛ አይነት ነው አሉ።
ልጆች ሲጨዋወቱ አንድ እቃ (እንደዛሬው የከተማ ልጅ የሚነጥር ኳስ እንኳን የለም) በጨርቅ የተሰፋ ኳስ፣ የተሰጣ ልብስ በንፋስ ከአጥሩ አልፎ በግቢው ከገባ ወይም ደግሞ ውሻና ከብት ያለው እንደሚባለው የቤት እንስሳቶች አጥር ሾልከው ወደ ጎረቤቱ ከዘለቁ በቃ እድሜያቸው አጠረ ነው። በማሳ ላይ የማይረባ ጨርቃ ጨርቁን ሁሉ እየጠቀለለ ይጥልበታል። እንዳው ጸብ ጸብ የሚላቸው ሆነው እንጂ ለክፋትም ባይሆን በሌላ ሰዎች እጅ ላይ የወደቀ በንፋስ፣ በእንስሳት ተጓጉዞ እዛ የደረሰ የሆነ የተለየ ነገር ከተገኘ ያ ምቀኛ ዛሬ ደግሞ ምን ጣለብኝ እየተባባሉ ብቻ ይፈላለጋሉ። የዱር አይጥ ሞታ ከተገኘች ደግሞ ሟርት ምናም የሚሉ የጥላቻና የጥርጣሬ ገመዶች ይጎተታሉ።
በዚህ መልኩ አንዱ አንዱን ለማጥቃት የሚፈላለጉት ጎረቤታሞች ሁሌም አየሁሽ አላየሁሽ ይጠባበቃሉ። ምሽት እየጠበቁ አጥር ስር ሲሰረስር አገኘው ይሆናል እየተባባሉ ይፈላለጋሉ። አንድ ቀን እንደተለመደው ነገረኛው ተጎራባች ከተኛበት ተነስቶ ቆመህ ጠብቀኝን ተሸክሞ ከጓሮ ወደ ፊት ለፊት ሲሄድ አንድ ወንድ በግቢው በር አጠገብ ያያል። ይሄን ጊዜ ጠላቴን አገኘሁት ብሎ ማነህ እንኳን ሳይል ተደብቆ ተኩሶ ይመታዋል። ይህን የሰሙ የቤተሰቡ አባላት ግልብጥ ብለው ወጥተው የተመታውን ሲያዩ አጎታቸው ሆኖ ያገኙታል። የተመታውም ሰውዬ ማዳን ሳይቻል ቀርቶ ህይወቱ ያልፋል።
እንግዲህ ቀደም ሲል በነበረው አሁን አሁን እንኳን በብዙ ቦታዎች ቀርቷል።ሰው ሲሞት አስለቃሽ ይቀጠራል። በዚሁ መሰረት አስለቃሽ መጣች። አስለቃሾች መጀመሪያ የሚያደርጉት ስለሟች ሁኔታ በሚገባ ማጥናት ነው። የሀብቱን ፣ስልጣኑን ፣ታዋቂነቱን፣ ደግነቱን (ባይሆንም) ለቅሶ ለማሳመር ሁሉን ካጠናች በኋላ ነው የለቅሶ ግጥሞቿን የምትደረድረው። በዚህ ጊዜ ታዲያ ስለ ሟች ስትጠይቅ ሟቹን የገደለው የእህቱ ባል ነው ብለው ይነግሯታል። ይህን የሰማች አስለቃሽ ታዲያ እንዲህ አለች አሉ። «የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ » ብላ አረፈችው።
አሁንም በሀገራችን የምናየው የሰላም መደፍረስ የሚያሳየን ይሄንኑ ነው። ማን ነው ማንን የሚገድለው፣የሚያፈናቅለው የሚጎዳው፣ የሚገርፈው የሚያሰቃየው የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚያደርሰው ማን ነው? ማን ላይ ነው? አስለቃሽዋ እንዳለችው አይነት ይሆንብኛል። የራሱን ዜጋ በራሱ ዜጋ ስቃይ፣ እንግልት፣ ድብደባ ፣ዘረፋ …. የመሳሰለው ሲፈጸም ሲታይ የሞተው ወንድምሽ የገደለው ባልሽ አይነት ይሆንብኛል። ወንድም ወንድሙን ሲገድል፣ ሲያሰቃይ፣ ሲዘርፍ እንደማየት አስከፊ ነገር የለም።
አሁን አሁን ከዚህ ቀደም የምንደረድረው ሰበብ አስባብ የለም። የውጭ ወራሪ ሀይል አልመጣብንም፤ በውጭ ያሉትን የፖለቲካ ተቃዋሚዎችንም በሰላማዊ ትግል ሀገራችሁ ላይ ሆናችሁ ታገሉ የሚል ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ አገር ቤት ገብተዋል። አብዛኞቹም ሰላማዊ የትግል መንገዱን መርጠው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። እንዳውም አልፈው ተርፈው ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ጋር ውህደት ለመፍጠር የተስማሙም አሉ።
ለምሳሌ በእነ ሌንጮ ለታ የሚመራው ኦዴግ ከኦዴፓ ጋር ውህደት ፈጥሮ ለመስራት ስምምነት ተፈራርሟል። እንዲሁም በዳውድ ኢብሳ የሚመራውም ኦነግ በሚያግባቧቸው አብሮ ለመስራት በማያግባቧቸው ላይ ደግሞ ተቀራርቦ ለመወያየት መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
አዴፓም የትጥቅ ትግሉን ፈትቶ ወደ አገር ውስጥ ከገባው አዴሃን ጋር ውህደት መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።
ሌሎች ፓርቲዎችም በዓላማ ፣በርዕዮተ ዓለም በሚያስማማቸው ፓርቲዎች ጋር ውህደት፣ ግንባር በመፍጠር 80 አካባቢ የሚሆነው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቁጥር ወደ አራትና አምስት ዝቅ ለማድረግ ውይይት ላይ ናቸው። ይሄ የሚያሳየው ማንም የማንም ጠላት ሳይሆን ወንድምና እህት ነው። ያለችውም አንድ አገር ናት – ኢትዮጵያ። የሁሉም ትግልና ልፋት የተሻለች አገርን ለመገንባት ነው። የተሻለች አገር ለመገንባት፣ ዴሞክራሲን ለማጎልበት ሁሉም እኩል ተጠቃሚ የሚሆንባትን አገር ለመፍጠር ደግሞ አንዱ የሌላኛው ጠላት መሆን ወይም እንደ ጠላት መታየት አይኖርበትም። አንዱ አባራሪ ሌላው ተባራሪ መሆንም አይገባውም። ቢቻል ተስማምቶ በኢትዮጵያዊ አንድነት ስሜት አብሮ መስራት፣ አብሮ ማደግ …። ካልተቻለ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ መታገል የተሻለ አማራጭ ይሆናል። የ21ኛው ክፍለ ዘመንም የሚጠይቀው ይሄንኑ ነው። በመነጋገር፣ በመወያያት፣ በመደማመጥ መደማመጥ ።
በ2012 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የምናካሂደው ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በአገር ላይ እንዲሰፍን መስራት ፣ ሁሉም የሚከተለውን ርዕዮተ ዓለም ለህዝብ በማቅረብና ህዝብ እንዲያውቀው በማድረግ በቀጣይ በምርጫ ሂደት የህዝብን የመመረጥ ወይም ያለመመረጥ ውሳኔ መጠበቅ ይሆናል። ይሄ ሲሆን ለውድድር የቀረበውም አካል ያገኘውን የህዝብ ድምጽ ተቀብሎ ያሸነፈው ወደ መንበረ ስልጣኑ፤ የተሸነፈው ደግሞ ለቀጣዩ ምርጫም ዝግጅቱን የሚጀምር ይሆናል። ምን ጎደለኝ? ምን መስራት አለብኝ? ለሚለው በቀጣይ የዝግጅት ጊዜ ይሆናል። ራሱን ይገመግማል፤ በህዝብ ተወዳጅና ተመራጭ የሚያደርጉ መንገዶችን መቀየስ ይጀምራል። ይሄም ሆኖ በአገራዊ ጉዳይ ለተመረጠው መንግስት ከመሰረተው ድርጅት ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ለህዝብ ለሀገር የሚበጀውን አብሮ በመስራትም አጋርነቱን ይቀጥላል። በዚህ መልኩ በሰለጠነው ዓለም ያየነውን የሰማነውን ማድረግ የምንችለው ከክፋት፣ ከምቀኝነት፣ እኔ ብቻ ከሚል የተሳሳተ የፖለቲካ አስተሳሰብ ወጥተን ማሰብ ስንችል ነው። ከጠርሙስ ውስጥ የራቀ አስተሳሰብን ማዳበር ስንችል ነው። ይሄ የሰለጠነ መንገድና አካሄድ ነው።
አሁን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩት የፖለቲካ ሂደቶች ግን ይሄን የሚያመጣ ነወይ? ተብሎ ሲታሰብ ግን ብዙ ነገሮች አስፈሪ ሆነው ይታያሉ። በማህበራዊ ሚዲያው የሚተላለፉ መልዕክቶች (የጥላቻ መርዝ በሚረጩ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች) በየመድረኩ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሳ ፣ ፓርቲና ህዝብን ለይተው የማያዩ ሆነው ይታያሉ። በምሽግ ውስጥ የተጠመደ ፈንጂ አይነት አስተሳሰቦች ብቅ ብቅ እያሉ ነው።
ባለፉት 27 ዓመታትም የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ያለውን ማሰር፣ መግረፍ፣ በጨለማ ቤት ማሰቃየት፣ አካል ማጉደል ፣ጥፍርን በፒንሳ መንቀል፣…. እጅግ በጣም አሳዛኝና አሰቃቂ የሆነ ድርጊት የተፈጸመው የምታከብረውና የምታስከብረው ህገ መንግስት አላት በምትባልበት አገር ነው። ይሄ ሲታይ በእውነት ህገ መንግስቱ ነበር ወይ? ወይም በስልጣን ላይ የነበሩት አካላት ህገ መንግስቱን ያውቁትና ያስከብሩ ነበረ ወይ? ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል። ያለፉት ጊዜያት ስህተቶች አሁንም እንዳይደገሙ ነው አሁንም በፅኑ መታገል የሚገባው፤ በአጥፊዎችም ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድ መባሉ፤ እንደከዚህ ቀደሙ ቂምን በቂም መመለስ ከሆነ ግን አሁንም የገደለው ባልሽ … ከሚለው አባባል የሚያድነን አይሆንም።
ይሄ ሁሉ አስከፊ ግፍ በተፈፀመበት አገር በዜጎች ላይ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽሙና ሲያስፈፅሙ የነበሩ አካላት በህግ ተጠያቂ ይሁኑ ሲባልም አንዳንዶች የብሄር ጉዳይ አድርገው ተቃውሞ ሲያሰሙ ተደምጧል። ነገር ግን ሌብነትም ሆነ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈፀም የማንንም ብሄር የሚመለከት ጉዳይ መሆን የለበትም፤ ሊሆን አይገባም። እንዳውም አጥፊዎችን የህግ ተጠያቂ ማድረግ በቀጣይም ህጉም ሆነ ህገ መንግስቱ እንዲከበር ማስተማሪያ ይሆናል። ስለዚህ አሁንም ይሄንን ህግ የማስከበር፣ ተጠያቂዎችንም ተጠያቂ የማድረጉ ጉዳይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። እያንዳንዱ እርምጃም በህግና በህግ ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል። ይሄን ያደረጉትን እንበቀል ብሎ አጠፋዊ እርምጃ ለመውሰድ መሞከር ግን አስለቃሿ ያለችውን መድገም ነው፤ ሀገርም እንደ አገር መቀጠሉ ያሳስባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)