ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሶሪያ የሚገኙ ሁለት ሺህ የአሜሪካ ወታደሮች ከአገሪቱ እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ውሳኔያቸውም አንጋፋ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትን እንዳበሳጨና አንዳንድ የአሜሪካ አጋሮችንም እንዳስደነገጠ ተዘግቧል፡፡ ፕሬዝደንቱ ራሱን እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራውን ቡድን በመሸነፉ ወታደሮቹ እንዲወጡ ማዘዛቸውን ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት በበኩላቸው ወታደሮቹን ከሶሪያ የማስወጣት ስራው በመጭው ጥር ወር አጋማሽ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዝደንት ትራምፕ ውሳኔያቸውን ለቱርኩ አቻቸው ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን በስልክ እንደነገሯቸውም ስማቸውን ያልገለፁ የትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አገራቸው መመለስ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ የፕሬዝደንቱ ውሳኔ ከአማካሪዎ ቻቸውና ከአሜሪካ ወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ትንታኔ በተፃራሪ የቆመ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ አሸባሪው እስላማዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ስላልከሰመና የሌሎች ታጣቂ ቡድኖች እንቅስቃሴም አስተማማኝ በሆነ መልኩ ስላልተገታ ወታደሮቹን ማስወጣት ተገቢ ውሳኔ እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ሲናገሩ ነበር፡፡ አንጋፋ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ፕሬዝደንቱ ስለውሳኔያቸው ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
የአልጀዚራው ዘጋቢ አለን ፊሸር ‹‹ፕሬዝደንት ትራምፕ ይህን ውሳኔ የወሰኑት ቱርክ ከጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ ትራምፕ በሚደግፏቸው የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን ላይ የምታደርገውን ጫና እንድታላላ ለማድረግ ነው ብለው የሚያስቡ አካላት አሉ›› በማለት ከዋሺንግተን ዲ.ሲ ዘግቧል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት አባል የሆነችው ቱርክ ከሶሪያ ጋር በምትዋሰንበት ደቡባዊ አቅጣጫ በኩል በማንኛውም ጊዜ ዘመቻ ልትጀምር እንደምትችል አሳውቃ ነበር፡፡ ቱርክ በአሜሪካ የሚደገፈውንና የኩርድ ሕዝቦች ጥበቃ ኃይል (Kurdish People’s Protection Units – YPG) በመባል የሚታወቀውን ቡድን ቱርክ ውስጥ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር እየተዋጋ የሚገኘው ቡድን ቅጥያ አድርጋ ስለምትመለከተው ቡድኑ በአሜሪካ መደገፉ ለኤርዶጋን መንግሥት ምቾት አልሰጠውም፡፡ ቱርክ አሜሪካ ለቡድኑ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቋርጥም ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡
አሜሪካ እ.አ.አ በ2015 ወታደሮቿን ወደ ሶሪያ ከማስገባቷ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በእስላማዊ መንግሥት ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ በማካሄድ አሸባሪውን ቡድን እንዳዳከመችው ይነገራል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
አንተነህ ቸሬ