የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስለ ፍርድ ቤት ዘገባ ለመገናኛ ብዙኃን በቅርቡ በሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ በተሳታፊዎች አንዳንድ ፈገግ የሚያደርጉ ግን በቀላሉ የማይታዩ ነገሮች ነበሩ የተነሱት፡፡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከምስክርነት ጋር በተያያዘ ካጋጠሙ ችግሮች በመነሳት በመፅሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን ከሚፈጸም የምስክሮች ቃለ መሐላ ተጨማሪ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡
ሰነዱ በአካባቢያቸው ማህበራዊ ጉዳይ ከሚያስፈጽሙበትና ከሚገኙበት ሥራ ጋር በማያያዝ ነው የተዘጋጀው፡፡ የመሐላ ሰነዱ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ ምስክሮች መሸሽ መጀመራቸው ነበር በሥልጠናው ላይ የተነሳው፡፡‹‹እኔ በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን መስሎኝ ነው እንጂ በዚህማ ከሆነ…›› ብሎ የሚመለስ ምስክርም እያጋጠመ ነው፡፡ ነገሩ ፈገግ ቢያደርግም ጥያቄ ያጭራል፡፡ ይሄን መነሻ በማድረግ ለክልሉ የፍትህ ሥርዓት እንቅፋት በሆኑትና በተጀመሩ አዳዲስ አሰራሮች ላይ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ናስር ፋሪስ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
በቃለመሐላ ምስክርነት ላይ
ያጋጠሙ ክፍተቶች
ለወንጀልም ይሁን ለፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ከሚቀርቡት የሰነድና የተለያዩ ማስረጃዎች በተጨማሪ ምስክር ለፍትሕ ሥርዓቱ ደጋፊ ነው፡፡ ወንጀል ሲፈጸም ምስክሮች ናቸው የሚያረጋግጡት፡፡ወንጀል በፖሊስና በዓቃቤ ህግ ተመርምሮና ተጣርቶ ነው ክሱ በዓቃቤ ህግ ፍርድ ቤት የሚቀርበው፡፡ፍርድ ቤቱም ተከሳሹን አስቀርቦ ቃሉን ተቀብሎ የግራ ቀኙን ምስክር ሰምቶ አመዛዝኖ ነው ውሳኔ ላይ የሚደርሰው ወይንም የሚወስነው፡፡ ጉዳዩ በቀረበው ክስ መሰረት ካልተረጋገጠ ወይንም ጥርጣሬ ካለ በተለይ ወንጀል ከሰው መብት ጋር ስለሚያያዝ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
ተከሳሾች በመከላከያ ማስረጃቸው በበቂ ሁኔታ ከተከላከሉ ተከላክለዋል ተብሎ ነፃ የመውጣት ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል፡፡ የዓቃቤ ህግ ምስክር ካላረጋገጠ ነፃ ነው የሚወጡት፡፡ አረጋግጠዋል ቢባልም እንዲከላከሉ ዕድል ተሰጥቷቸው የራሳቸውን የመከላከያ ማስረጃ ካቀረቡ ተከላክለዋል ተብሎ ነፃ የሚወጡበት ዕድል ይኖራል፡፡ የመከላከያ ማስረጃ አቅርበውም አልተከላከሉም ተብሎ ውሳኔ የሚሰጥበት አጋጣሚ አለ፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመው ዋና ችግር የሐሰት ምስክርነት ነው፡፡ በፍትሐ ብሔርም የሚያጋጥም ቢሆንም በወንጀል ጉዳይ ላይ ግን ችግሩ ይጎላል፡፡ ምስክሮች ያላዩትን፣ ያዩትንም ቢሆን ጨምረውበት በሐሰት ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ የሚሰጡት ምስክርነት በወንጀሉ የሌለበትንም ሰው ለእንግልት የሚዳርግ ሊሆን ይችላል፡፡
ሰዎች በእምነታቸው ቃለ መሐላ እንዲፈጽሙ በማድረግ የሚከናወነው የፍርድ ሂደት ለምን እንከን ያጋጥመዋል? በሚል መነሻ፣ ችግሩም በመደጋገሙና ባልፈጸሙት ወንጀል የሚጎዱ ሰዎች በመኖራቸው በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን በሚፈጸም ቃለ መሐላ ብቻ የፍርድ ሂደቱን ማከናወን በቂ አለመሆኑ ግንዛቤ ተይዞ ተጨማሪ ሰነድ ማዘጋጀት አስፈላጊነቱ ታምኖበት በ2001ዓ.ም ላይ ጥናት በማካሄድ በሚተዳደሩበት ሥራ ወይንም የአካባቢው ነዋሪ በጋራ የሚያከናውነው ማህበራዊ ጉዳይ ላይ መሰረት ያደረገ የቃለ መሐላ መመሪያ ሰነድ በማውጣት ተግባራዊ ሆኗል፡፡
ቃለ መሐላ የሚፈጽመው ሰው ገበሬ ከሆነ፣ የሚዘራው ዘርና የሚያረባው ከብት እንዲጠፋበት በእርሱና በኑሮው ላይ ችግር እንዲደርስበት እንዲሁም በአካባቢያቸው ከፍተኛ ክብር በሚሰጡት ነገር እንዲምሉ ማድረግ ይጠቀሳል፡፡ ለእነርሱ ቅርብ በሆነ ነገር እንዲምሉ በመደረጉ ብዙዎች በመፍራት ጥንቃቄ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለፍትህ ድጋፍ ለመስጠት በተዘጋጀው ሰነድ እንዲምሉ ጎን ለጎን ግንዛቤ በመስጠት የፍትህ መዛባትን ለማስቀረት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ በመሆኑም ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ቀንሰዋል፡፡
ሰነዱ ከመውጣቱ በፊት በጸሐፊዎችና በኦፊሰሮች አማካኝነት ይፈጸም የነበረው ቃለ መሐላ ችሎቱን በሚያስችል ዳኛ እንዲፈጸም መደረጉም ጉዳዩ ክብደት እንደተሰጠው ማሳያ ተደርጎ በመወሰዱ ለአሰራር መሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት በየጊዜው ክፍተቶችን እያዩ ማስተካከል ይገባል፡፡
በምስክሮች በኩል የሚስተዋለውን ችግር በዚህ መልኩ ለማስተካከል ጥረት ቢደረግም በፍትህ አካላቱ በኩልም የወንጀል ቅሬታ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ የበሰለ የምርመራ ሂደት በማከናወን ላይም ክፍተት ይስተዋላል፡፡ የሥነምግባር ችግሮችም ጥራት ያለው ፍትህ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ለምርመራው የሚያግዙ ግብዓቶች አለመሟላትም ለክፍተቱ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም እርምጃዎች ሁለንተናዊ መሆን ስላለባቸው በዚህ ረገድም ታይቷል፡፡
የሐሰት ምስክርነትና ተገቢ ያልሆነ መረጃ ማሳያዎች
በመቀራረብና በጥቅም በተሰጠ የሐሰት ምስክርነት ያልሞተ ሰው ሞቷል ተብሎ በመግደል ወንጀል ተፈርዶበት የእስር ጊዜውን ጨርሶ ሲወጣ ሞተ የተባለው ሰው የተገኘበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ የእስር ጊዜውን ጨርሶ የወጣው ሰውም ሳይሞት ሞቷል የተባለውን ሰው ሲያገኘው አላግባብ በእስር እንዲቆይ ስላደረገው ተናዶ በመግደሉ ችግር ውስጥ የገባበት አጋጣሚ አለ፡፡
በፍትሐ ብሔርም የልደትና የሞት ምዝገባ ባለመኖሩ ከውርስ ጋር በተያያዘ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በይርጋ ጊዜ እንዳይጠየቁ የሚፈልጉ ወገኖች ባለንብረቱ የሞተበትን ጊዜ ወደኋላ በማድረግ፣ በይርጋ ዕድል ለመጠቀም የሚፈልጉ ወገኖች ደግሞ የራሳቸውን ማስረጃ በማቅረብ በክርክር ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡ ፍችም ሲፈጸም ንብረት ላለማካፈል በሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትና በጥቅም በመደለል የተጓደለ ፍትህ ይሰጣል፡፡ በውል ማስረጃ ላይም የውሉን ይዘት በትክክል ባለመግለጽና ስለውሉም በአግባቡ ባለመረዳት ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡
ችግሮችን መነሻ በማድረግ የተሠሩ
ሥራዎች
በወረዳ፣ በዞን፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ በ2001ዓ.ም የሥነምግባር ደንብ ወጥቶ እየተሠራበት ነው፡፡ በይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ በቅርቡ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ተሻሽሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ያልነበረ አሁን በተሻሻለው አዋጅ ውስጥ የተካተተው የክልልና የዞን ሥነምግባርን የሚከታተል ቡድን እንዲሁም የዳኞች አስተዳደር ጉባዔን ተቀብሎ የሚያስተናግድም ተቋቁሟል፡፡
ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል እንዲቻልም ሌላ ቡድን ተቋቁሟል፡፡ የማኅበረሰብ ግንዛቤን በማሳደግ የሙስና፣ የወንጀልና ከፍትህ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል በዳይሬክቶሬት ደረጃ የሚሠራ ክፍል ተቋቁሟል፡፡ ባለጉዳዮች ጉዳያቸው የትና? እንዴት? ተፈጻሚ ሊሆንላቸው እንደሚችል እንዲያውቁ፣ እንዳይታለሉ፣ በሙስና ጉዳያቸውን ለማስፈጸም እንዳይሞክሩ፣ እንዳይንገላቱ በችሎት ግቢ ውስጥ ግንዛቤ ለመስጠትም የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ በህግም ያልተካተቱትን በማካተት የህግ ተደራሽነትን ለማስፈን እየተሠራ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ለወረዳ ተከላካይ ጠበቃ አልነበረም፡፡ በነበረው አሰራር አምስትና ከአምስት ዓመት በላይ ፍርድ ለሚሰጥበት ጉዳይ ነበር ተከላካይ ጠበቃ የሚጠየቀው፡፡ አሁን ግን ለማንኛውም የወንጀል ክስ ጉዳይ ያለጊዜ ገደብ ተከላካይ ጠበቃ የማቆም መብት ተሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ዘንድሮ በወረዳዎች 84 የተከላካይ ጠበቃ ቅጥር ይፈጸማል፡፡ በጀት ሲሟላ በክልሉ ለሚገኙት 304 ወረዳዎች ሁሉ ይሟላላቸዋል፡፡
በትላልቅ ከተሞች ከቤት፣ ከካርታና ከመሬት ጋር በተያያዘ በስፋት የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚያስተናግዱ የከተማ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል፡፡ ፍርድ ቤቶቹ ሌሎች የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችንም ያስተናግዳሉ፡፡ አሰራሩ በአንድ ወረዳ ላይ የሚከማች አሰራርን ለማቃለል ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
ከአራቱም የክልሉ አቅጣጫዎች ለሚመጡ ባለጉዳዮች ቋሚ ችሎት በማቋቋምና በተጨማሪ በተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎት በመስጠት የባለ ጉዳዮችን እንግልት ለመቀነስ እየተሠራ ነው፡፡ የወንጀልም ሆነ የፍትሐ ብሔር ጉዳይ በፍርድ ቤት ውስጥ አልፎ ነው በኦሮሚያ ሰበር የሚታይበት አሰራር በመዘርጋት የፍርድ ሂደቱን ለማቀላጠፍ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡ ተደራሽነትን የበለጠ ለማረጋገጥና በጥራት ፍትህ ለመስጠት ተጨማሪ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አቶ ናስር አመልክተዋል፡፡
ዳኞች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሠሩና ቅሬታ የሚበዛባቸውንም ለይቶ ትኩረት መስጠት ከተወሰዱት አዲስ የአሰራር እርምጃዎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ዳኞችን እያዟዟሩ መሥራት ባለመለመዱም በተመደቡበት ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመሆን ሥራቸውን የለቀቁም አሉ፡፡
ባህላዊ የፍርድ ሥርዓትን ማጠናከር
በአሁኑ ጊዜ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ 550ሺ ጉዳዮች ናቸው የሚታዩት፡፡በ2010 በጀት ዓመት ብቻ ወደ 617ሺ ጉዳዮች ናቸው የታዩት፡፡ የጉዳዮች መብዛትም በራሱ ችግር ስለሆነ ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው በእርቅ የመፍታት ባህል ማዳበር ነው፡፡ በዚህ ላይ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓት መልካም የሆነ ተሞክሮ ስላለው በማጠናከር የፍትህ ሥርዓቱን እንዲያግዙ ማድረግ ነው፡፡በተሻሻለው አዋጅም ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት ተካትቶ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
በፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች
በፍርድ ቤት ላይ ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል ከገጠር መሬት ጋር የተያያዘው ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ የባልና ሚስት እና የውርስ ጉዳዮች በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ፡፡
የሴቶችና የቤተሰብ ችሎት
አዲስ በወጣው የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ውስጥ የሴቶችና የቤተሰብ ችሎት በሚል ተካቶ ቀደም ሲል ከነበረው አሰራር የሴቶችና የህጻናት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በተለይ ለተለያየ ጥቃት የሚጋለጡ ሕፃናት በችሎት ሲቀርቡ በተለየ የአሰራር ሥርዓት እንዲስተናገዱ የሚያደርግ ነው፡፡ ዳኛውና ሕፃናቱ በተለያየ ክፍል ውስጥ ሆነው ግን ጉዳያቸው የሚታይበት የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋቱ
ሕፃናቱ በነፃነት የደረሰባቸውን ጉዳት ያስረዳሉ፡፡
በፍትህ ሥርዓቱ በዳኞችና በጠበቆች ይስተዋል የነበረውን የሥነምግባር ጉድለት፣ ማስረጃ ከሚጠየቁ አካላት ትክክለኛ የሆነ ማስረጃ አለማግኘት፣ በተበዳይ በኩልም የተሟላ ማስረጃ ይዞ አለማቅረብ፣ የሐሰት ምስክርነትንና ሌሎችንም ክፍተቶች በመፈተሽ እየተከናወነ ያለው ተግባር አበረታች ቢሆኑም ተደራሽነትን በሚያረጋግጥ ጥራት ያለው ፍትሕ በማስፈን በኩል ብዙ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
ለምለም መንግሥቱ