በሰሜናዊቷ ኮከብ መቀሌ ከተማ ላይ በነበረው የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ጉባኤ ላይ ከተመለከትናቸው ልዩ ክስተቶች መካከል በማህበራዊ ሚዲያው በሰፊው የተሰራጨውና የብዙዎችን ስሜት የኮረኮረው የሰላም ሚኒስትሯ የክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በእንባ የታጀበ መልዕክት ነበር። በመልካም አስተዳደር ንፍገትና በስርቆት ብዙዎችን ሲያስለቅሱ የነበሩ በርካታ አመራሮችን በተመለከትንባት ሀገር የሀገርና ህዝብ ጉዳይ አሳስቧቸው አልቅሰው የሚያስለቅሱ እንስት ሚኒስትሮችን ለማየት መቻላችን መታደልና በዶክተር አብይ አህመድ የተመራው ለውጥ አንዱ ፍሬ ነው ብዬ እገምታለሁ።
ኢትዮጵያ ሀገራችን የሚለው ስም ልዩ ትርጉምና በቃል ሊገለጽ የማይችል ልዩ ኃይል አለውና በርካቶች በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮችና በሙዚቃና ቴያትሮች ሲያነቡለት ደጋግመን አስተውለነዋል። ደራርቱ ቱሉና ኃይሌ ገብረስላሴ በኦሎምፒክ መድረክ አስደናቂ ድል ካስመዘገቡ በኋላ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብላ ስትውለበለብ ካነቡት እንባ ጋር አብረን አንብተናል፤ ድርጊቱም በአዕምሯችን ውስጥ ተቀርጾ በልባችን ውስጥ ለዘላለም ይኖራል። የምንጊዜም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ የሆነው ጥላሁን ገሰሰ በእንባ እየታጠበ ያዜመው
እንኳንስ ደስታዬን የሰውነቴን ሰው፣
እንኳን ነጻነቴን ጸጋ ክብሬን ትቼው፣
በእናት ሀገር ምድር በሚያውቀኝ በማውቀው፣
ስቃይ መከራዬን በአንቺ ዘንድ ያድርገው።
ላኖረኝ ሰው ላረገኝ ፍቅርሽ፣
ዕድሜዬን ያድረገው ውለታሽን መላሽ፣
ለፈቃድሽ ጋሻ ለችግርሽ ደራሽ…..
የሚል ልብ ኮርኳሪ ሙዚቃ የእናት ሀገር ፍቅር ምን ያህል ጥልቀት እንዳለውና በትውልዶች ልብ ውስጥ እንደሰረጸ አሳይቶናል። ይህን ለማሳያ አነሳነው እንጂ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ነጻነትና ፍቅር ያላቸውን ጽናት ለማሳየት እንባ ሳይሆን መተኪያ አልባ ንጹህ ደማቸውን ያፈሰሱና ህይወታቸውን የገበሩ የብዙ ጀግኖችና ጀግኒት አገር ናት -ኢትዮጵያ!
በመግቢያዬ ካነሳሁት ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእርግጥም የአገራችንን ሁኔታ ስናስተውልም ሆነ ውሎና አዳሯን በመገናኛ ብዙኃን ስንሰማና ስንመለከት ዓይናችንን እንባ የሚሞሉ በርካታ ጉዳዮችን እናያለን። ወዴት እየሄድን ነው? መድረሻችንስ የት ነው? የሚለውም ጉዳይ ያሳስበናል። የወይዘሮ ሙፈሪያትንም እንባ ፈንቅሎ በአደባባይ እንዲያነቡ ያደረጋቸውም ይሄው ነው። የወይዘሮ ሙፈሪያትን እንባ የእርሳቸው እንባ ብቻ ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን እናቶች እንባ እንደሆነም ነው የምረዳው፡፡ እውነት ነው እኛ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ጽጌረዳ አበባ የደመቀና የተዋበ ልዩነቶች ህብር ነን። ሀገራችንም ባለብዙ ቋንቋ ባህልና ሃይማኖት ሀገር ናት። ይህ ልዩነት ውበትና ድምቀት ሆኖን እጅግ ብዙ የሆኑ አስደማሚ ባህሎች ሙዚቃዎችና እምነቶች ባለቤትም አድርጎናል።
የአማራው ዶሮ ወጥ፣ የኦሮሞው አንጮቴ፣ የትግራዋዩ ጥሕሎ፣ የጉራጌው ክትፎና የደቡቡ ቦርሳሜ ህብረ ብሄራዊነታችን ያጎናጸፉን ልዩ ጣዕሞቻችን ናቸው። ትምህርትና ሥልጣኔ ብዙም አልተስፋፋበትም እንዲሁም ድህነት የከፋ ተጽዕኖን አሳርፎበታል ተብለው በሚጠቀሱ ዘመናት የኖሩ አያት ቅድመ አያቶቻችን የሃይማኖትና የብሄር ልዩነት ሳያግዳቸው በኢትዮጵያዊነት ገመድ በአንድነት ተጋምደው ክፉና ደጉን በፍቅር አሳልፈው ለዚህ አድርሰውናል።
ዛሬ ዛሬ ትምህርቱና ሥልጣኔው በተስፋፋበት ካለፈው ጊዜ አንጻርም ሲተያይ የተሻለ አኗኗር በሰፈነበትና ብሄሮች በቋንቋቸው መጠቀምና ባህላቸውን እንደልብ ማስፋፋትና የፈለጉትን እምነት በነጻነት ማምለክ በቻሉበት ዘመን ታድያ ጥቃቅን ምክንያቶች እየተፈለጉ የሰው ህይወት በየጊዜው መጥፋቱ የእኔ ክልል ነው እየተባለ ዜጎች በገፍ መፈናቀላቸው ሀገሪቱ ስንት የምትጠብቅባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ዱላና ድንጋይ እንደ ጉድ ተሸክመው ለጥፋት ሲሰማሩ ሲስተዋል ማልቀስ ቢያንስ ነው የሚያስብል ነው።
ለረጅም ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ የብሄርና የሃይማኖት ጭቆናዎች ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝተዋል ሀገራችን በውስጧ አምቃ የያዘቸው የውሃ፣ የግብርናና የሰው ኃይል አይደለም ለሀገራችን ህዝብ ለዓለም መትረፉ ምንም ሳያጠራጥር፣ መሬቱ ሳይጠበን አዕምሯችን ጠቦ ለመገፋፋትና ለመጠፋፋት ሲለፋ ማየቱ እጅግ ያስገርማል። አባቶችና እናቶቻችን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩት መቻቻልና መከባበርስ የት ገባ ያስብላል።
የጭቆናና ሰቆቃ ዘመን አልፎ ዳግም ላይመለስ ተቀብሯል በተባለበት ዘመንም የተሰሙት እጅግ ዘግናኝ ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶች እንባ ከማፍሰስም በላይ የሰውን ስሜት በጥልቁ የወጉ ድርጊቶች ናቸው።
በቁጥጥር ስር በዋሉ ወንድምና እህቶቻችን ላይ ሊደረግ ቀርቶ ሊሰማ እንኳን ለጆሮ የሚቀፉ ኢ ሰብአዊ ተግባራት ሲፈጸሙባቸው እንደነበር ስንሰማ ሀገራችንና ህዝባችንን እንወዳለን ስንል ሌት ተቀን ስንናገረው የቆየነው ነገር የት ደረሰ ያስብላል። በዘመነ ደርግ ልጆቻቸውን በግፍ ተነጥቀው የነበሩ እናቶች ኢህአዴግ ሥልጣን በተቆጣጠረ ማግስት እጅግ የተለየ የኀዘን ስሜት ውስጥ በሚከት ለቅሶና ዋይታ ኀዘናቸወን ገልጸው እና በእነሱና በልጆቻቸው ላይ የደረሰው ግፍ ማንም ላይ ዳግም አይድረስ ብለው ተማጽነው ነበር። ሆኖም ይህ የኀዘን ጠባሳ ሳይሽርና ቁስሉ ሳይጠግግ ይህን መሰሉን ግፍ ሰምተናልና ለዚህ ማልቀስም ቢያንስ ነው እንጂ አይበዛም እላለሁ።
መግደል መሸነፍ ነው የሚለው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ አህመድ ታላቅ መልዕክት ከልባቸው ያልገባ በርካቶች መኖራቸውን ዛሬም በሞያሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ አጎራባቾች እንዲሁም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እየተፈጸሙ ካሉ ግድያዎች እየተመለከትን ነው። ወንድምና እህቱን ገድሎ ምንም እንዳላተረፈ እየተንሰቀሰቀ ተጸጽቶ የሚናገረው ሰው ድምጽ ከጆሯችን ሳይጠፋ ምንም ትርፍ ለሌለው ነገር ሌላው ዳግም ተነስቶ የወንድም እህቱን ደም ሲያፈስ እያስተዋልንና ልባችን እየደማ ነው። የወይዘሮ ሙፈሪያትን አዕምሮ ረብሾ እንባቸውን ካስፈፈሰው ተደማሪ ነገሮች አንዱም ይሄ ይመስለኛል። ገድሎ የህሊና ጸጸት ከማትረፍና በለጋ የወጣትነት ዕድሜ በማረሚያ ታጉሮ በጸጸት ዕድሜን ከመግፋት ውጪ ማንም ምንም ሲያተርፍ አልተስተዋለም። እና ለምን ይሆን በአንዱ ጥፋት ይሄን መማር አቅቶን በጥፋት ላይ ሌላ ጥፋት እየጨመርን ያለነው? እረ ጎበዝ እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ ከየት ነው የመጣው? መልስ የሚፈልግ ወቅታዊ ጥያቄ ነው።
እንኳን ለፍሬዎቿ ኢትዮጵያውያን የመንና ሶሪያን ጨምሮ ለተለያዩ የዓለም ህዝቦች መጠለያ በመሆን ላይ ባለችው ታላቅ ሀገር የተለያዩ ምክንያቶችን እየቆነጠሩ ከክልሌ ውጣ በሚል ብሂል ዜጎች ሲፈናቀሉ ማየቱም ልብን ሰብሮ በእንባ ያስታጥባል። ለተለያዩ አገራት ስደተኞች ማረፊያ የሆነች አገር በውስጥ ተፈናቃዮች ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተሰለፈች ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነገር እንደ አገርና ህዝብ መዋረድ አይደለምን? ከዚህስ ነገ ሀገሪቱን የሚረከበው አዲሱ ትውልድ ምን እየተማረ ይሆን? እጅግ ያሳስባል!
ከ1960ዎቹ የተካረረ ፖለቲካ የተወለደው የፍረጃና ብሽሽቅ ፖለቲካ መላቀቅ ዳገት ሆኖባቸው በሁለት ጽንፍ ላይ ቆመው የጥላቻ ንግግሮችን የሚወራወሩ ኃይሎችን ማየት ዛሬም አላቆምንም። የመሪዎቻችን ‹‹አንድ ገጽ ለያዘው አጥፊ መልዕክት ብለን ሙሉ መጽሀፉን አናቃጥልም፣ ሌባ ለብሄሩ ብሎ አይዘርፍምና መደበቂያ ጫካ አንሁንለት›› የሚል መልዕክት የህይወታችን መመሪያ አልሆን ብሎ ሁለቱም ጽንፎች የጥላቻ መልዕክቶችን ከዚህ ወደዚያ ለማሰማት ደፋ ቀና ማለታቸውም አልቀረም።
ሀገራችን እንኳን ለራሷ ዜጎች ለዓለም የምትበቃ ታላቅና ባለጸጋ ሀገር ናት። በጨዋነት በመከባበርና በመቻቻል የመኖር ተምሳሌት የሆኑ አባቶችና እናቶች መኖሪያም ናት። ምንም አይነት የፖለቲካም ሆነ ሌላ ልዩነት ይኑረን በሰላማዊ መንገድ ቀርቦና ተወዳድሮ አሸናፊ የሚሆንበት ዕድል እንዲኖርም ምቹ ጎዳና በመጠረግ ላይ ይገኛል። ‹‹ምንም ዓይነት የፖለቲካ አቋም ይኑራችሁ ኑና በነጻው ሜዳ ተወዳድረን ብልጫና ተቀባይነት ያገኘ ፓርቲ ይምራን›› የሚል መርህም በሥራ ላይ ውሎ ወደ መሬት ለማውረድ አስገራሚ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። ሰፊውን የሃሳብ ገበያ የሚያንጸባርቁ ነጻ የመገናኛ አውድ ተከፍቶ የግል መገናኛ ብዙኃን ቀን ተቀን እየተዋለዱና እየተራቡ ገበያውና ማጥለቅለቅ ይዘዋል።
ህዝቡም ይሄንን የህትመት ውጤት ስላነበብኩ ወይም ይህንን ቴሌቪዥን ጣቢያ ስለተመለከትኩ እገሌ ተብዬ እፈረጅና ይሄ ቅጣት ይጠብቀኛል ከሚል ስጋት ተላቆ በአደባባይ የፈለገውን መርጦ እያነበበና እየተመለከተ ይገኛል። አክቲቪስቶችም ሆኑ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ካላሉና የራሳቸው ህሊና ካልገደባቸው በስተቀር ሀሳባቸውን በሙሉ ነጻነት ለፈለጉት የኅብረተሰብ ክፍል የሚያደርሱበት ዕድልም በሰፊው ተከፍቷል። የጠላትን ሚዲያ ያህል ተፈርጀው የነበሩ መገናኛ ብዙኃንም ወደ ሀገር ቤት ገብተው ያለምንም መሳቀቅና ስጋት በነጻነት የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በመከወን ላይ ይገኛሉ።
በቂ ነው ተብሎ ባይታመንምና አሁንም እጅግ ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ቢታወቅም ከላይ የተዘረዘሩት ምቹ ሁኔታዎች በተፈጠሩበትና ሁሉም ዜጋ እንደ ልጅ መታየት በጀመረበት በዚህ ወቅት የወይዘሮ ሙፈሪያትንና ሌሎች እናቶችን እንባ የሚያስፈስሱ የጥፋት፣ የጥላቻና የመካረር ተቃርኖዎችን ሲፈጸሙ ማስተዋል ትርጉም አልባ ነው። ይልቁኑ ሰፊውንና ነጻውን የነጻነት የሰላምና የልማት መንገድ ተከትለን በመፍሰስ የእናቶቻችንን እንባ እናብስ ተስፋቸውና የኩራታቸው ምንጭ እንሁን የመደምደሚያ መልዕክቴ ይሆናል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
ፍቃዱ ከተማ