ሳይንስ የምርምርና የፈጠራ ራስ፣ የጊዜ ማዘመኛ መንገድ፣ የስልጣኔ መገለጫ ነው። ትናንት በብዙ ልፋት ይከናወኑ የነበሩ ስራዎች ዛሬ ጠፍቶ በሚበራና በአንዲት መጫን ብቻ ያለ ልፋት መተግበራቸው ለዚህ ማሳያ ነው። ሳይንስ በፈጠረው መልካም አጋጣሚ ለዘመናት ስንገለገልባቸው የነበሩ ቁሶች በአገልግሎት ደረጃ ከፍ ብለው፤ በእድሜ ጨምረውና በአተገባበር ቀልለው የመገኘታቸው ሚስጥር ደግሞ ሳይንስ ነው። ለዚህም ነው ዘመኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ነው ተብሎ ተደጋግሞ የሚነገረው።
ሳይንስ በየትኛውም መስክ ተፅዕኖ በመፍጠር ያለንበትን ሁኔታ መቀየሩ ግድ ሆኗል። የትናንት ውሎና አዳራችንን፤ ስራና ተግባራችንን ከዛሬ የተለየ ያደረገው ሳይንስ መሆኑም ልብ ይሏል። በአንድም በሌላም መልኩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የሳይንስ ግኝቶች ለኛ ቀርበው እየተገለገልንባቸው እራሳችንን ከዘመኑ ጋር ማራመድን ተላምደናል። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መገልገል ዛሬ የሁላችንም መሰረታዊ ነገር በመሆን ላይ ይገኛል።
ተማሪዎች የሚማሩባቸው መገልገያ ቁሳቁሶች የዘመናዊው ሳይንስ በጎ ተፅዕኖ መዳረሻ መሆናቸው አልቀረም። የመማሪያና ማስተማሪያ መጻሕፍት የወረቀትና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶች የተማሪዎችን ፍላጎትና ምቾት በሚጠብቅ መልኩ እየተለወጡ ዛሬ ላይ ለመያዝም ለአጠቃቀምም ምቹ ሆነው እየቀረቡ ይገኛሉ። በዚህ ዘርፍ ምርምር አድርገው አዲስ ፈጠራ በማስመዝገብ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያዎች ለሀገሪቱ ትምህርት እድገት ጉልህ ሚና በማበርከት ላይ ናቸው።
የዛሬ የሳይንስ አምድ እንግዳችን በመምህርነት ሙያ በማገልገል ላይ ያሉና በመማር ማስተማር ስርዓትና በትምህርት ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችል መተግበሪያ (ሶፍት ዌር) የሰሩ የፈጠራ ባለሙያ ሲሆኑ፤ የርሳቸውን አጠቃላይ የፈጠራ ስራ የተመለከተ ዝግጀት አሰናድተን በዚህ መልክ ማቅረብ ወደናል።
አቶ ኤፍሬም ሻሼጎ መምህር፤ የፈጠራ ባለሙያና ተመራማሪ ናቸው። የተማሪዎች ውጤት እየቀነሰ ለመምጣቱ ዋንኛው ምክንያት የሚገለገሉባቸው የትምህርት መርጃዎች እጥረት መሆኑን የተረዱት የፈጠራ ባለሙያው ለዚህ መላ መዘየድ እንዳላባቸው ከራሳቸው ጋር ቃል ኪዳን አሰሩ። ይህ በጎ እሳቤና ፍለጎታቸው ደግሞ የትምህርትን ስርዓት በማዘመን በተሻለ መልኩ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል ዘንድ የሚረዳ ሶፍት ዌር በማዘጋጀት ውጤት አስገኘላቸው።
የፈጠራ ስራው ምንነት
በመምህርና በፈጠራ ባለሙያው ኤፍሬም የተሰራው አጋዥ የትምህርት ሶፍት ዌር ሲሆን፤ ይህ ተማሪዎችን ለትምህርት ዝግጅት የሚያገለግላቸው በይዘቱ እና በትምህርት አይነቶች ብዙ ቁጥር ያላቸው መጻህፍት በሶፍት ኮፒ (በኮምፒዩተር ወይም በስልክ የሚነበብ ፅሁፍ) ለተማዎች የትምህርት ውጤታቸው መሻሻል እገዛ ሊያደርግ የሚችል መተግበሪያ ነው። ይህ መተግበሪያ ልዩ ልዩ የትምህርት አይነቶች ከመያዙም ባሻገር፤ ለሀገር አቀፍ ፈተናዎች መለማመጃ ጥያቄዎች የያዘ በመሆኑ ተማሪዎቹን ቀድሞ በማዘጋጀት ጠቀሜታው ያይላል።
በተመራማሪው የተሰራው ይህ ሶፍት ዌር በኢትዮጵያ አዕምሯአዊ ንብረት ፅህፈት ቤት የፈጠራ ስራ ባለቤትነት መብት የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) ያስገኘላቸው መሆኑ ከሌሎች መሰል መተግበሪያ ሶፍት ዌሮች የሚለይ ለመሆኑ ማስረጃ ነው። ከመዋለ ህፃንት እስከ 12 ክፍል ድረስ ያሉ ተማሪዎች ሊጠቀሙበት የሚችሉት ይህ የትምህርት መርጃ ሶፍት ዌር በድምፅና በምስል የተዘጋጁ ልዩ ልዩ የትምህርት አይነቶችን፣ ለፈጠራ ስራ ሊያነሳሱ የሚችሉ የምስል ስብስቦችን፣ የስምንተኛ፣ የአስረኛና የ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎችን መለማመድ የሚያስችሉ ጥያቄና መልሶችን፣ ትምህርታዊ ጨዋታዎችንና ሌሎች ማጣቀሻ መጽሐፍትን አብሮ ያካተተ ነው።
በመምህር ተመራማሪና የፈጠራ ባለሙያው ኤፍሬም የተሰራው ይህ ሶፍት ዌር በየጊዜው ማሻሻልና ተጨማሪ ትምህርታዊ ጉዳዮችን ማከል የሚቻልበት ሶፍት ዌር አሁን ላይ ከ4000 ያላነሱ በምስል የተቀነባበሩ ትምህርታዊ ማስተማሪያዎችን፣ ከ2500 የሚበልጡ ማጣቀሻ መጽሐፍቶችን፣ ከ1000 የማያንሱ ትምህርታዊ መጫዎቻዎችን አካቷል።
የፈጠራ ስራው መነሻ ምክንያት
የፈጠራ ባለሙያውና መምህሩ ኤፍሬም ለተማሪዎች እጅግ ጠቃሚ የሆነ የትምህርት አጋዥ ሶፍት ዌር ለማዘጋጀት ያነሳሳቸው ዋነኛ ገጠመኝ ከአምስት ዓመት በፊት ተማሪዎች እንደ አጋዥ የሚያገለግል መጽሐፍ አዘጋጅተው ለገበያ ያቀርባሉ። ይህ መጽሐፍ በኢንፎርሜሽና በቴክኖሎጂ ትምህርቶች ላይ መረጃዎችን የያዘና ለተማሪዎች ያግዛል በሚል ነበር አዘጋጅተው በጥራዝ መልክ ያቀረቡት፤
መጽሐፉ ለተማሪዎች እጅግ ወሳኝ ሀሳቦችን በውስጡ ቢያካትትም ተጠቃሚዎቹ ተማሪዎች ያለመገልገላቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ሲመረምሩ መጽሐፉን በቀላሉ ማግኘት አለመቻላቸውና ከአጠቃቀም አንፃርም በተሻለ መልኩ ማቅረብ እንዳለበት ያስባሉ። ለዚህ ደግሞ ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት አይነት በቀላሉ በያዙት ሞባይል ወይም ባላቸው ኮምፒዩተር መጠቀም የሚያስችላቸው መተግበሪያ ወይም አፕልኬሽን ለማዘጋጀት ወስነው ጥናት ማድረግ ይጀምራሉ።
የተነሱበት ሀሳብ በጎ፤ ያለሙት እቅድ በጥረት የሚሳካ ነበረና ዛሬ ላይ ከአራት ባላነሱ ትምህርት ቤቶች ላይ ተተግብሮ ውጤታማ የሆነ፤ በተማሪዎች ውጤት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ መፍጠር ያስቻለ መተግበሪያ በመፍጠርና ለተማዎቹ ምቹ በሆነ መንገድ በማዘጋጀት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ያለኢንተርኔት ግብዓት በሞባይልና በኮምፒዩተር ላይ አንዴ ተጭኖ ለተፈለገው ያህል ጊዜ መጠቀም የሚያስችለው ይህ ሶፍት ዌር ተማሪዎች በቀላሉ የትኛውም ቦታ ሆነው ሊጠቀሙበት የሚያስችላቸው ለትምህርት ውጤታቸው መሻሻል ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን የፈጠራ ባለሙያው ያስረዳሉ።
በፈጠራ ስራው የተገኙ ሽልማቶችና እውቅና
አሁን በትምህርት ቤቶች ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው ይህ ሶፍት ዌር ወይም የተመራማሪው የፈጠራ ስራ በ2011 ሀገር አቀፍ የፈጠራና የምርምር ስራ ላይ ለውድድር ቀርቦ በማሸነፍ በኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ለተመራማሪው አስገኝቶላቸዋል። የምርምርና የፈጠራ ስራቸው ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ከልዩ ልዩ ተቋማት እውቅናና ማበረታቻዎችንም ለተመራማሪው አስገኝቶላቸዋል።
አቶ ኤፍሬም በምርምር ውጤታቸው በክልል ደረጃም የተለያዩ የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይና ውድድሮች ላይ ተሳትፈው ከተለያዩ ሀገርና አለም አቀፍ ተቋማት ልዩ ልዩ ማበረታቻ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
ተመራማሪ፤ የፈጠራ ባለሙያና መምህር ኤፍሬም የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት አዳዲስ ፈጠራዎችን በመሞከርና ከትምህርት ጋር ተያያዥ የሆኑ ዘመናዊ መሳያዎች ማዘጋጀት የሚችሉበትን መንገድ በማሰብ ነው። የምርምር ስራ ለሀገር ማበርከት ከሚፈልጉት በጎ ስሜት የሚመነጭ መሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪው፤ የስራው አድካሚነት መጨረሻ ላይ በሚገኝ ውጤት የሚረሳ መሆኑን ይገልጻሉ።
የመምህር ኤፍሬም ሻሼጎ የምርምር ስራ ውጤታማነት በተለያዩ ተቋማት ማረጋገጫ የተሰጠው ሲሆን፤ ለተማሪዎች እጅግ ብዛት ያላቸው የትምህርት አጋዥ ማጣቀሻና መማሪያ መጽሐፍት በቀላሉ ማግኘት የሚስችል በመሆኑ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። መሰል አገልግሎት ከሚሰጡት በተሻለ መልኩ አገልግሎት መስጠት የሚችለው ይህ መተግበሪያ በፈጠራ ባለሙያው የተዘጋጀ፤ የተለያዩ የትምህርት ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ የተዘጋጁ ሀገራዊ ስርዓተ ትምህርት መሰረት ያደረጉ የትምህርት ይዘቶችን ያካተተም ጭምር ነው።
ገጠመኞች
ለአንድ ሀገር ትልቁ ሀብት የሰውን ልጅ አዕምሮ በመጠቀም የሚገኘው ውጤት መሆኑን የሚናገሩት መምህር፤ ተመራማሪና የፈጠራ ባለሙያው ኤፍሬም ሻሴጎ ለምርምር ስራዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የፈጠራ ስራዎችን ማበረታትና ተግባር ላይ የሚውሉበት መንገድ ማማቻቸት ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን ያስረዳሉ። ለምርምር ስራ ተገቢ ትኩረት ባለመሰጠቱ ሀገር በቀል የምርምር ስራዎች እንዳይፈልቁ ምክንያት ሊሆን እንደቻለ ያስዳሉ። ለዚህም እርሳቸው በፈጠራ ስራቸው ወቅት የገጠማቸውን ችግር በማሳያነት ያነሳሉ።
በግል የሚሰሩት የምርምር ስራ ወደ ተግባር እንዳይለወጥ የገንዘብ እጥረትና በምርምር ስራ የሚገኘው ገቢ አነስተኛ መሆን እንቅፋት የፈጠረባቸው መሆኑን ይናገራሉ። የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ ከተደረገላቸው ለሀገር ኢኮኖሚዊ እድገት ብሎም የቴክኖሎጂያዊ አቅም መዳበር ጉልህ አስተዋፅዖ ያላቸው መሆኑን ይናገራሉ።
የፈጠራ ስራዎች በተመራማሪና በፈጠራ ባለሙያዎች ብዙ ትጋት የሚጠይቁ በመሆናቸው ተግባራዊ ሆነው ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መቅረፍ ካልቻሉ መገኘታቸው ብቻ ጥቅም የሌለውና ትርፉ ድካም ብቻ ነው የሚሉት ተማራማሪው ለዚህ በሀገር ደረጃ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የፈጠራ ባለሙያው ኤፍሬም በምርምር ስራው የገጠማቸው የገንዘብ አቅም ማነስ ሌሎች ስራዎችን እንዳይሰሩና በምርምሩ ይበልጥ ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው ትልቅ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። ሀገርን በቴክኖሎጂው ውጤት ሩቅ ማስጓዝ ይቻል ዘንድ ለተመራማሪዎችና ለፈጠራ ባለሙያዎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ይናገራሉ።
የምርምር ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ በተመራማሪዎች ተሰርተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚመለከታቸው አካላት፤ በተለይም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው መስራትና የፈጠራ ስራዎቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል። ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች የግኝት ውጤታቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት የገንዘብ ድጋፍ፤ መነሻ የሚሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል። እንደ ተመራማሪው ገለፃ፤
ሳይንሳዊ ምርምርና የፈጠራ ስራ የሰው ልጅ የሚገጥመውን አካባቢያዊና ማህበራዊ ችግር መፍቻ መንገድ መሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ለዚህ ዘርፍ ትኩረት መስጠት ጠቀሜታው የጎላ እንዲሆን ያስችላል ይላሉ። ሀገራዊ የምርምርና የፈጠራ ስራን ማበረታታት ደግሞ ለዚህ ቁልፍ ተግባር ዋነኛ መነሻ ነው። ሳይንስ ዘርፈ ብዙ ችግር የሚፈታ መሆኑን በመጠቆምም በደንብ ከተሰራበት ደግሞ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን በመቀነስ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችል የፈጠራ ስራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ።
በምርምር ስራ ወቅት የገጠማቸውን የራሳቸውን ተሞክሮ በማንሳት ምክረ ሀሳባቸውን የሚያቀርቡት የፈጠራ ባለሙያውና መምህሩ ኤፍሬም፤ ወደ ምርምር ስራ የሚሰማሩ አዲስ ተመራማሪና የፈጠራ ባለሙያዎች ጠንካራና ብርቱ መሆን እዳለባቸው ያሳስባሉ። የዘርፉ ጀማሪ ባለሙያዎች ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋትና መልካም ውጤት በመመኘት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ፤ በዚህም መልካም ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ተሞክሯዋቸው በመጥቀስ ይመክራሉ።
ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማጠናከር ሀገር በስልጣኔ ጎዳና ፈጥና እንድትራመድ የሚያስችል መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው። ለዚህ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሀገር በስልጣኔ መንጥቃ ከሌሎች ጋር መሰለፍ እድትችል መስራት ይገባል። የምርምር ስራ ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ያላቸው አቅም የላቀ በመሆኑ ለፈጠራና ለምርምር ባለሙያዎች ድጋፍ ክትትልና ማበረታቻዎች ማድረግ ተገቢ መሆኑን መግለፅ እንወዳለን። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2011
ተገኝ ብሩ