አዲስ አበባ፡- በናይሮቢ ዲክላሬሽን /ስምምነት/ ን ተግባራዊ በማድረግ መፈናቀልን ማስቆም የሚያስችሉ እና ስደተኞችን ወደ ልማት ሊያስገቡ የሚችሉ ተጽእኖዎችን መፍጠር መቻሉን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የናይሮቢ ዲክላሬሽንና ትግበራ በስደተኛነትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ላይ የሚመክር የሚኒስትሮች 2ኛው ጉባዓ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት፣ ስደተኝነትን ወይም የግዴታ መፈናቀልን ማስቆም የሚያስችሉ ሥራዎች መሰራቱን ገልጸዋል።
ስደተኞችን ወደ ልማት ሊያስገቡ የሚችሉ ተጽእኖዎችን በመፍጠር በጎ ተግባር ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል። የኢጋድ አንዱ ዓላማ ስደተኝነትን ወይም የግዴታ መፈናቀልን ማስቆም መሆኑን ገልጸው፣ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ መልክ እየያዘ መምጣቱንና ይህም የትብብሩ አንዱ ውጤት እንደሆነም ጠቅሰዋል። ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎቱ ጨምሯል ብለዋል። የአውሮፓ ህብረት ለቀጣናው ብቻ ለዚህ ዓመት 380 ሚሊዮን ዩሮ፣ የዓለም ባንክ ሰኔ ወር አንድ ቢሊዮን ዶላር፣ የጀርመን መንግሥትም ድጋፍ እንዳደረጉ ጠቅሰዋል።
ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም አሁንም መፈናቀል ሊቆም አለመቻሉንም አቶ ዘይኑ አንስተዋል። ‹‹ከሶማሊያ፣ ከኤርትራና ከደቡብ ሱዳን ስደተኞችን እየተቀበልን እንገኛለን፣ ይህ መቆም አለበት›› ብለዋል። የእርስ በርስ ግጭት የመፈናቀል አንዱ መንስኤ እንደሆነ በመግለጽም፤ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን የማድረጉ ተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
የናይሮቢው ዲክላሬሽን ኢትዮጵያ በሊቀመ ንበርነት እየመራችው እንደምትገኝ የጠቆሙት አቶ ዘይኑ፤ ኢትዮጵያ ስምምነቱ ባግባቡ እንዲተገበር ከፍተኛውን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች ብለዋል። በቀጣናው የሚገኙ አገራት ህዝቦችም አብዛኛው ችግሮቻቸው ተመሳሳይ እንደመሆኑ፤ በጋራ መስራቱ ጠቃሚ መሆኑንና የናይሮቢ ዲክላሬሽን ትብብርም እነዚህን ጉዳዮች ከግምት የሚያስገባ ነው ብለዋል።
የኢጋድ የጤና እና የማህበራዊ ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር አልዋን ፋታህ፣ በምስራቅ አፍሪካ የሰፈነውን ሰላም ኢጋድ እንደሚያደንቀው ጠቅሰዋል። በሱዳን የተካሄደው ለውጥ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል። በደቡብ ሱዳንም አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታና ዕድገትም አድንቀዋል። ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲተባበሩም ጠይቀዋል። የናይሮቢ ዲክላሬሽን በዋናነት የስደተኞችን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚረዱ የትግበራ ዕቅዶችን ማፍለቅ መሆኑንም ገልጸዋል። በቀጣናው አገራት ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ያለው ትብብር የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢጋድ የትምህርት ፕሮግራም አስተባባሪው ዶክተር ከበደ ካሳ በበኩላቸው፣ ፖሊሲዎችን በማሻሻልና ህግና ሥርዓቶችን በማበጀት ላይ አተኩሮ ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉትን በክብር መመለስ፣ መቆየት የሚፈልጉትም በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ጥገኝነት የሚጠይቁበት መንገድ ማበጀት የሚያስችሉ ሥራዎች መሰራታቸውን አጠቅሰዋል። አገራቱ ፖሊሲዎቻቸውን ፈትሸው ለስደተኞች የሚመች ህግ ወጥቶ ስደተኞች ከህብረተሰቡ እኩል ተጠቃሚ ሆነው እንዲኖሩ የሚያስችል ሥራ መስራት ተችሏል ብለዋል።
ናይሮቢ ዲክላሬሽን የኢጋድ መሪዎች በ2017 እ.ኤ.አ መጋቢት ወር ተሰብስበው ያጸደቁት የጋራ ስምምነት ነው። ስምምነቱ ያተኮረውም በሶማሊያና አጠቃላይ በቀጣናው የስደተኞችንና የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ የቀጣናው አገራትና አጋዥ አካላት በትብብር የተቀናጀ መርሀ ግብር ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 8/ 2012
ዘላለም ግዛው