ከአንድ ሳምንት በፊት የፍትህ ሰቆቃ በሚል ዕርስ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም በርከት ባሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይህን ዘጋቢ ፊልም የተከታተሉ ብዙ ኢትዮጵያውን በሀዘን ተኮራምተዋል፡፡ በወገኖቻችን ላይ እንዴት እንዲህ ይደረጋል ሲሉም ተቆጥተዋል፡፡ ወንድሞቻቸው በበቀሉባት ሀገር ይህን ሁሉ የግፍ ፅዋ በመጎንጨታቸው ተቆጭተዋል፡፡
በዚህ ዘጋቢ ፊልም ባለታሪክ ሆነው ከቀረቡት ሰዎች አንዱ አብደታ ታደሰ ይባላል፡፡ አብደታ ስለተፈፀመበት ግፍ ሲናገር፤ ሰው እንደዛ ያደርጋል ተብሎ አይገመትም ይላል፡፡ የግፍ ሰሪዎቹን ማንነት ሲገልፅ ደግሞ ‹‹በኦሮምኛ ቋንቋ ቡልጉ የሚባል ነገር አለ፤ ጭራቅ ማለት ነው፡፡ ሰውን ከእነህይወቱ የሚበላ አራት አይን ያለው ትልቅ ፍጡር ተደርጎ የተሳለ ነው፡፡ በልጅነታችን ዘመን ቡልጉ ማስፈራሪያ ነበር፡፡ ነገር ግን እዚህ (ማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ) ቡልጉን በዓይኔ አይቼዋለሁ›› ይላል፡፡ እኔም አብደታ በማዕከላዊ እስር ቤት ስለተመለከተው ቡልጉ ጥቂት ማለት ፈልጌ ይህችን ጽሑፍ ሞነጫጭሬ እነሆ አልኳችሁ፡፡
ቡልጉ ሉአላዊ የሆነ መንግሥት ባላት ሀገር ውስጥ በዜጎች ላይ ያሻውን እየፈፀመ የኖረ ሌላ መንግሥት ነው፡፡ ሉአላዊው መንግሥት ፍልውሃ ጀርባ እና አራት ኪሎ ሁለት ቤተ መንግሥቶች ሲኖሩት ቡልጉ ግን ለቁጥር የሚታክቱ ቤተ መንግሥቶች ባለቤት ነው፡፡ ማዕከላዊ እስር ቤት፣ አዲስ አበባ ውስጥ የተገኙት ሰባት ድብቅ እስር ቤቶች እና በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች አሉ ተብለው የሚታመኑ ተጨማሪ ድብቅ እስር ቤቶች የቡልጉ ቤተ መንግሥቶች ናቸው፡፡ ቡልጉ ብልግና አዋቂ ነው፡፡ እንደውም የብልግና ወላጅ አባት ቢባል ያንስበት ይሆናል እንጂ አይበዛበትም፡፡ ቡልጉ የሰዎችን ደም በስትሮ እየመጠጠ የሚወዛ፤ ሥጋቸውን ተልትሎ እየበላ የሚያገሳ፤ ጥርሳቸውን አራግፎ ከትከት ብሎ የሚስቅ የሰይጣን ቋጥኝ ነው፡፡
መስቀል አደባባይ የሚገኘውን የቀይ ሽብር ሰማዕታት መተሰቢያ ሙዚየም እንደ ቡልጉ ተመላልሶ የጎበኘ ጎብኚ ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በመታሰቢያ ሐውልቱ ላይ በሰፈረ ደማቅ ጽሑፍ ‹‹መቼም የትም እንዳይደገም›› የተባለውን ሁሉ አሻሽሎ ደግሞታል፡፡ የነበረውን በማሻሻል ሳይወሰን ታይተው እና ተሰምተው የማይታወቁ አዳዲስ ሰዎችን የማሰቃያ ዘዴዎች ለዓለም አስተዋውቋል፡፡ እንደውም ለዚህ ፈር ቀዳጅነቱ የፈጠራ ባለቤትነት የምስክር ወረቀት ሳይቀበል አይቀርም፡፡
የሕግ ዋነኛ ተቀዳሚ ተግባር ፍትህን ማስፈን ነው፡፡ ለቡልጉ ግን ሕግ የመግዣ መሣሪያ ነው፡፡ ጥያቄው አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሟል ወይስ አልፈፀመም ሳይሆን በአገዛዙ ላይ እንቅፋት ሆኗል ወይስ አልሆነም ነው፡፡ ለአገዛዙ እንቅፋት ሆነህ ከተገኘህ በዕድሜ ዘመንህ አልፈህ የማትጨርሰው የእንቅፋት አይነት ከፊትህ ይደነቀርልሃል፡፡ በነፃ የመዘዋወርና የመንቀሳቀስ፣ የአካል ደህንነት እና በህይወት የመቆየት መብቶችህ እንደ ትራፊክ መብራት በሴኮንዶች ይጣሳሉ፡፡ በአርባ ስምንት ሰዓት ቀርቶ በአርባ ስምንት ወራትም ፍርድ ቤት ላትቀርብ ትችላለህ፡፡
አጋጣሚ ቡልጉዎች እጅ ከጣለህ፣ ሴት ቡልጉ አትግጠምህ፡፡ መፈጠርህን እንድትጠላ ታደርግሃለች፡፡ በርግጥ ልቧ ይራራል፡፡ ፊትህ በቀዝቃዛ ውሃ እንዳይጎዳ ሰስታ ሙቅ ውሃ ታንቆረቁርልሃለች፡፡
ቡልጉ ማታ በፒንሳ ጤና ሲነሳህ እና በሽቦ ሲሸበሽብህ አድሮ ጠዋት ዳኛ ሆኖ ፍርድ ያከናንብሐል፡፡ ይህን ሁሉ የቡልጉዎች ጭካኔ ሳስብ በህይወት ተርፈው ምስክር ለመሆን የበቁት ሰዎች ጥንካሬ ይደንቀኛል፡፡ ተከታዩን ግጥም የፃፍኩት ለዚህ ነው፡፡
ልብስህ አድፎ ገላህ ሸቶ
የዘር ፍሬህ ተኮላሽቶ
በኤሌክትሪክ ተንዘፍዝፈህ
ጫካ አድረህ ዛፍ ታቅፈህ
ግርፊያ አዝሎህ ተዝለፍልፈህ
በድቅድቁ አይንህ ታስሮ
መቃብርህ ተቆፍሮ
ከቡልጉ ጥርስ የተረፍከው
ይህን ሁሉ እንዴት ቻልከው ?
አጥንት ሰባሪው ቡልጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ባቀረቡ ቁጥር መልስ ለመስጠት ሲሮጥ ብዙ ሪከርዶችን ሰባብሯል፡፡ ለሪፖርቶቹ የሚሰጠው ምላሽ ተመሳሳይ ነው፡፡ የጠላት ወሬ እና የኒኦሊብራል የሴራ ዘመቻዎች ናቸው ይላል፡፡ አያይዞም ዜጎች በሀገራቸው ተከብረው እና ታፍረው ሰብዓዊ እና ዴሞካራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው እየኖሩ ነው ብሎ መግረፊያውን እንደያዘ ይከራከራል፡፡ እንዲህ ያለውን የቡልጉ ዓይን ያወጣ ቅጥፈት ለዓይነ እና እዝነ ህሊና ይበልጥ ቅርብ ለማድረግ በፍትህ ሰቆቃ ከተጠቀሰው ‹‹በጫካ ውስጥ ከዛፍ ጋር ታስሮ ማደር›› ጋር የተያያዘ ተረት እነሆ፡፡
ሌሊት ሌሊት ግንድ ታቅፎ የሚጠፈር እስረኛ እየበዛ፣ ዛፎቹ እያነሱ ስለመጡ ከክረምት ወራት በአንዱ ቡልጉዎች ሰብሰብ ብለው ችግኝ ለመትከል እንጦጦ ወጡ፡፡ ችግኝ ተከላው እንደተጀመረ ከመካከላቸው አንዱ ችግኟን ተቆፍሮ በተዘጋጀው ጉድጓድ ውስጥ በአፍጢሟ ደፍቶ አፈር መመለስ ይጀምራል፡፡ በዚህ ጊዜ ትዕይንቱን በፎቶ ለማስ ቀረት የሄደ ፎቶ ግራፍ አንሺ ‹‹እረ ጌቶች እንዲህ ተተክሎ እንዴት ይፀድቃል?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ አፈር እየመለሰ ያለው ቡልጉ ቀና ብሎ ወፈር ባለ ግልምጫ አጮለውና ‹‹በሪፖርት ይፀድቃል›› ብሎ መለ ሰለት፡፡ ሥጋት የገባ ው ሥጋ ለባሽም ከችግኟ ጋር አብሮ እንዳይቀበር ሸሽቶ ሄዶ የሠላም ኑሮውን ቀጠለ፡፡ ተረቴን መልሱ በደልን በፍትህ አብሱ፡፡
እንግዲህ ቡልጉ በዚህ መልኩ ስንቱን በአፍጢሙ ደፍቶ ከአፈር እየደባለቀ የሀሰት ሪፖርት እንዳረቀቀ አንድዬ ይወቀው፡፡ እውነቱን ያዩ እና የተመለከቱ፣ በአፍጢም የተደፉ ሰዎች ዕጣ እንዳይገጥማቸው በመሥጋት የሀሰት ሪፖርቱን አጨብጭበው ያፀድቃሉ አሊያም ሸሽተው ይሄዳሉ (ስደት)፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ‹‹የተከሰሱ ሰዎች በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር›› መብት እንደላቸው ይደነግጋል፡፡ በተከሰሱበት ወንጀል በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ብይን እስካልተሰጠ ድረስ ተጠርጣሪዎችን ወንጀለኛ ማለት ሌላ ወንጀል ነው፡፡ ይህ ግን የቡልጉዎችን ህልውና አይመለከትም፡፡ ቡልጉዎች ህልው (ህላዊ) ናቸው፡፡ ሥጋ ነስተው ነፍስ ዘርተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ፍርድ ቤት የሚያረጋግጠው በሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ቡልጉ መሆን አለመሆናቸውን ነው፡፡
ሕዝብ ቡልጉዎችን አሳምሮ ያውቃቸዋል፡፡ ውስጡ እያረረ የሚስቅባቸው ቀልዶቹ ይህን ያረጋግጣሉ፡፡ ለአብነት በምርጫ ዘጠና ሰባት ሰሞን አዲስ አበባ ውስጥ ትኩስ የነበረ አንድ ቀልድ ልጥቀስ፡፡ ቀልዱ የአሜሪካው ኤፍ ቢ አይ እና ቡልጉ ለውድድር ቀረቡ ይላል፡፡ ከዚያም ሁለቱም በአምስት ደቂቃ ውስጥ በግ አምጡ ተባሉ፡፡ ኤፍ ቢ አይ በተሰጠው ሰዓት በግ ይዞ መጣ፡፡ ቡልጉ ግን ደም በደም የሆነ ውሻ እየጎተተ መጣ፡፡ ትዕዛዝ አስተላላፊዎቹ ‹‹በግ አይደለ እንዴ አምጣ ያልንህ?›› ሲሉት ቡልጉ ‹‹ተደብድቦ አምኗል›› ብሎ እርፍ አለ፡፡
አንድ ያጣላልና እንድንፋቀር ሁለት ልበል፡፡ አንድ ወጣት የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዶ ሦስት ኤፍ በማምጣቱ ለጊዜው ትምህርቱን መቀጠል ሳይችል ይቀራል፡፡ በዚህ ጊዜ ሥራ ወደማፈላለጉ ይገባል፡፡ ሆኖም ለወራት ሲንከራተት ቢቆይም ሥራ ያጣል፡፡ ተስፋ ስለቆረጠ ምርጫ በማጣት በቡልጉነት ለመቀጠር ያመለክታል፡፡ የቡልጉዎች አለቃም ሦስት ኤፍ እንዳለው ከተመለከተ በኋላ ሊቀጥሩት እንደማይችሉ ያበስረዋል፡፡ ወጣቱ ይህን ሥራ አጣዋለሁ ብሎ ስላላሰበ በግርምት ‹‹በምን ምክንያት ነው የማትቀጥሩኝ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ የቡልጉዎቹ አለቃም ‹‹እኛ ሰባት ኤፍ ያለው ነው የምንፈልገው›› ብሎ ቁጭ አለ፡፡
እነዚህ ቀልዶች በሕዝብ ስነ ቃል ውስጥ ቡልጉ ምን አይነት ቦታ እንዳለው ለማሳየት አስረጅ እንዲሆኑ ያህል ተጠቀሱ እነጂ ስለ ቡልጉ ብዙ ተብሏል፡፡ እስቲ እናንተም ቆም በሉና ስለቡልጉ የሰማችሁትን ፣ የሳቃችሁበትን እና የተጋራችሁትን ቀልድ አስታውሱ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2011
የትናየት ፈሩ