1953 ዓ.ም ከአዲስ አበባ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አቃቂ ከተማ ጋርዱባ 06 አካባቢ ነበር የተወለደው፤ በልጅነቱ ፈጣንና አስተዋይ እንደነበር ይነገራል። የታዳጊው ሁኔታ በቤተሰቦቹም ሆነ በአካባቢው ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚደርስ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጎታል። የታዳጊው ብሩህ አዕምሮ በቀለም ትምህርት ቢታገዝ ደግሞ እኛንም አገሩንም ያኮራል ብለው አስበዋል።
ተሻጋሪ ተስፋ ማድረግ ብቻም ሳይሆን በአካባቢው በሚገኘውና ፊት አውራሪ በሚባለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስመዘገቡት። በአስኳላ ውሎው በጥሩ ተማሪነትና በፈጣን ሯጭነቱም ጭምር ለመታወቅ የቻለው የትናንቱ ታዳጊ የቀድሞ አትሌት ሸምሱ ሀሰን ነው። የትምህርት ቤት ቆይታውን እየወደደው ቢመጣም፤ የቤተሰቦቹ ሁኔታ ግን ሊያራምደው አልቻለም።
የቤተሰቡን ችግር ለማቃለል እርሱ ቢያንስ ራሱን ማስተዳደር ቢችል ትልቅ ብርታት እንደሚሆናቸው ሃሳቡ ነበር። በቀለም ትምህርቱ ብዙ ርቀት መጓዝ ቢያልምም አልቻለም። ከቤተሰብ ጥገኝነት ለመላቀቅ ከስድስተኛ ክፍል አቋርጦ ወደ ውትድርና ለማቅናት ወሰነ። አደረገውም፤
ሸምሱ፤ በብሄራዊ ውትድርና ውስጥ ለስልጠና የተመደበለትን ጊዜ አጠናቀቀ። አዲስ አበባ ማዕከላዊ ዕዝ ተመድቦ የህይወቱን ሌላኛውን ምዕራፍ ማጣጣሙን ያዘ። ሸምሱ የልጅነት ህልሙ በዚህ መልኩ እንዲሆን ፍላጎት ባይኖረውም፤ የሆነውን ግን ተቀብሎ ቀጠለ። በትምህርት ቤት ውስጥ ፈጣንና ተስፈኛ እግሮቹ በጦሩ ቤት ያለውን ቆይታ ወደ ስፖርት እንዲገባ አስችለውታል። በማዕከላዊ ዕዝ ውስጥ የሚያደርገው የስፖርት እንቅስቃሴ በጦሩ ውስጥ ለእጩነት አበቃው።
የእርሱን የዕጣ ጎዳና በአትሌቲክሱ ያደረገው አጋጣሚም በዚህ መልክ ተወለደ። የስፖርት አጀማመሩ በ1500 ሜትርና በ800 ሜትር ነበር። በእነዚህ ርቀቶች በተለያዩ ውድድሮች በመሳተፍ ሁለት ጊዜ ሦስተኛ ደረጃ ይዟል። አትሌቱ እግሮቹን ያሟሸው በእነዚህ ርቀቶች ይሁን እንጂ፤ እስከመጨረሻ የዘለቀው ግን በእርምጃ ውድድር ነበር። አጋጣሚው እንዲህ ነበር። አንድ ቀን በማዕከላዊ ዕዝ ስፖርት ውስጥ ብዙም ባልተለመደው የእርምጃ ሩጫ እንዲሳተፍ ይጠየቃል። ጥያቄው ለተሳትፎ ያህል የነበረ ቢሆንም፤ በውድድሩ ባለድል መሆን ቻለ። በ1974 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ ውድድር ተሳትፎ አሸናፊ ሆነ። አትሌቱ በእርምጃ ውድድሩ አሸናፊነቱ በአሰልጣኞቹ የመመረጥ እድል አገኘ። አገሩን ለማስጠራት በብዙዎች ዘንድ ተስፋ እንዲጣልበት ያደረገም ነበር።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ስማቸው ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ የሸምሱን ተስፈኝነት ከመሰከሩ ታላላቅ የስፖርት ሰዎች መካከል ተጠቃሽ ነበሩ። የእርሱ የእርምጃ ሩጫ የተለየ ክህሎት በመገንዘብና አርቀው በማስተዋል በደንብ እንዲሰራ ይመክሩት ነበር። ይህም በስፖርቱ ጉዞውን የጀመረበትን ርቀት በመተው ወደ እርምጃ ሩጫው ብቻ እንዲያዘነብልም ጭምር ሀሳብ እስከ መለገስ ደርሰዋል። እርሱም በእርምጃ ስፖርት ውድድር መጽናቱን ነው የሚናገረው፤ አገራችን በእርምጃ ውድድር ግን በማትታወቅበት ሁኔታ ገፍቶ ለመሄዱ የዋሚ ቢራቱ ምክር ለእርሱም ብቻም ሳይሆን በወቅቱ ለነበሩት ወንዴ ጦሬ፣ ተከስተ ዮሃንስ፣ ጥላሁን ሸገና በጽናት እንዲቆዩ ያደረገ ጭምር እንደነበር ሸምሱ ያስታውሳል።
እርሱ እንደሚለው፤ «በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች እይታ ውስጥ ለመግባት የቻልኩበትን አጋጣሚ መፍጠር ቻልኩ። ይህ ሁኔታ ደግሞ የተሳትፎዬን ደረጃ ተሻጋሪ የሚያደርግልኝን አጋጣሚ ይዞ ብቅ አለ። በአገር ውስጥ የእርምጃ ውድድር ብቃቴ ተለክቶ በዓለም አቀፍ መድረክ ታጨሁ። በ1975 ዓ.ም በኬኒያ ናይሮቢ ላይ በተካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ውድድር ላይ በእርምጃ ሩጫ ለአገሬ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣት ቻልኩኝ። በዚህ ድል ለራሴም ሆነ ለእናት አገሬ አኩሪ ድል ያመጣሁበት ትልቅ የህይወት አጋጣሚዬ ነበር። ይህም አሸናፊነት ገና ጅምር እንጂ የሚያበቃ እንዳልሆነም ለራሴው ቃል የገባሁበት አጋጣሚም ነው»።
የልጅነት ህልሙ መስመሩ በስፖርት ውስጥ ይሆናል የሚል ቅንጣት ያህል ፍላጎት ያልነበረው ወጣቱ ከስኬት ወደ ስኬት መሸጋገር ጀመረ። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ግብጽ ውስጥ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመሳተፍና በአንደኝነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ እንዳሸነፈ ይናገራል። ከዚህ በኋላም፤ በተለይ በኬኒያ እና በግብጽ በተዘጋጁ ውድድሮች ላይ በተደጋጋሚ የመሳተፍ እድል እንደነበረው ያስታውሳል። «በኬኒያም ሆነ በግብጽ በተካሄዱ ውድድሮች አሸናፊ መሆን ችያለሁ። ኬኒያ ውስጥ በተካሄዱ ውድድሮች አራት ጊዜ ተሳትፌያለሁ። በሁሉም አንደኛ ሆኜ ነው ያሸነፍኩት፤ በግብጽ በተመሳሳይ የመሳተፍ አጋጣሚዎች ነበሩኝ። ከነበሩት አራት ውድድሮች በአንዱ ብቻ ሁለተኛ ስወጣ የተቀሩትን በአሸናፊነት ነበር ያጠናቀኩት» ይላል ሸምሱ።
የወጣቱ የድል ጉዞ ከፍ በማለት በአራት ዓመት አንዴ በሚዘጋጀው ኦል አፍሪካ ጌምስ ላይ ሦስት ጊዜያት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቅቷል። ፈጣኑና ትንታጉ አትሌት የድል አድማሱን ከፍታ ከአህጉር አፍሪካ ተሻግሮ ለኦሎምፒክ ውድድር ወደባርሴሎና መጓዙን የሚያስታውሰው ሸምሱ በውድደሩ አምስተኛ ደረጃ በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው፤ ሩሲያ በመጓዝ ደግሞ ስምንተኛ ወጥቶ ማጠናቀቁን ያስታውሳል። «በጊዜው እኔ ትኩረት የማደርገው ሰዓቴን ማሻሻሌን ነው» ይበል እንጂ፤ አገራችን ብዙም ባልታወቀችበት የእርምጃ ውድድር በድሉ ከአገር ውስጥ እስከ አህጉር፤ ከዚያም እስከ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የተሻገረ ስኬት ያስመዘገበ የአገር ባለውለታ ነው። ሸምሱ በአትሌቲክሱ እያደገ የመጣው ውጤቱ በማዕረግ የታጀበም ሲሆን፤ ከአስር አለቅነት እስከ ሻለቃነት የደረሰ ነበር።
የሸምሱ የስፖርት ጉዞው ብቻም ሳይሆን የህይወት ኡደቱ ከ1974 እስከ 1992 ወርቃማ ዓመታት ናቸው ለማለት ያስደፍራል። አትሌቱ በእነዚህ 18 ዓመታት በስፖርቱ እራሱንም ሆነ አገሩን አስጠርቷል። ቤተሰብ በማፍራትም ህይወቱን በደስታ አጣጥሟል። የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤት የሆነውና የቀድሞው የእርምጃ ውድድር ባለድሉ ጎልማሳ የአዕምሮው ሁኔታ በመታወኩ ምክንያት እጅና እግሩን አጣጥፎ ከቤት ለመዋል ተገደደ። ከእርሱ በኋላም በመስኩ አሸናፊ ሆኖ የወጣ አትሌት አለመኖሩን ባገላበጥናቸው የተለያዩ መረጃዎች ለመገንዘብ ችለናል። በአሁኑ ወቅት ግን ለአገሩ የሰራው ገድል ተረስቶ፤ እርሱም አስታዋሽ አጥቶ በአዕምሮ ህመም እየተሰቃየ ይገኛል። ከኬኒያ እስከ ሩሲያ በእርምጃ ብቻ ሜዳሊያዎችን ያስገኙ እግሮች፤ የሚመራቸው ጤናማ አዕምሮ አጥተው ተሳስረው ቁጭ ለማለት ተገድደዋል። በከባድ ህመም ውስጥ ከመሰቃየት በቀር አማራጭ ያጣው ሸምሱ፤ በተለያዩ ውድድሮች አሸናፊ ቢሆንም ዘመኑ ስፖርተኞች እንዲህ እንደዛሬው የማይሸለሙበት ነበርና በስፖርቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለ ይናገራል። «በአሁን ሰዓት አላውቅም እንጂ እኔ በነበርኩበት ጊዜ የገንዘብ ሽልማት ሳይሆን የአበባ ጉንጉን ነበረ ወደ አገራችን ስንመለስ የሚበረከትልን፤ መንግሥት በእርምጃ ውድድር አሸንፌ ስመጣ ይሰጠኝ የነበረው ከብር 1500 ያልበለጠ ገንዘብ ነበር» በማለት በጊዜው ከስፖርቱ ተጠቃሚ እንዳልነበር ያስታውሳል። የአገር ባለውለታ የሆነው የቀድሞው አትሌት ሸምሱ ሀሰን በስፖርቱ ያገኘው ጥቅም ያለመኖሩ ብቻም ሳይሆን ጤናው መታወኩ ደግሞ ቤተሰብ ይዞ በችግር ለመቆራመት እንደዳረገው ይናገራል።
አትሌቱ ሲጀመር ስምንት መቶ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ 1400 ብር በሚያገኛት የጡረታ ገንዘብ በችግር መኖር እጣው ሆኖበታል። የተገኘውን ሥራ ለመስራት እንዳይችል ህመሙ ጋሬጣ ሆኖበት የሚያገኛትን የጡረታ ገንዘብ አጠገቡ ከሚገኙት ባለቤቱና ሁለቱ ልጆቹ ጋር በመቋደስ የችግር ህይወት ለመግፋት ግድ እንደሆነበት ይገልጻል። የሥራ ፍላጎት ቢኖረውም የህመሙ ሁኔታ ሰርቼ እንኳን ለመብላት እንዳልችል አድርጎኛል ሲል ይናገራል። በአንድ ባንክ ውስጥ በጥበቃ ስራ ተቀጥሮ መስራት ቢጀምርም የጤናው ሁኔታ የሚያሰራ አይደለምና መቀጠል አልቻለም። የመንፈስ ከፍታው በዚህ ደረጃ የሆነው ሸምሱ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ጥሯል። የእርሱ ሁኔታ አላላውስ ያላት ባለቤቱም የህይወት አጋሯን በቤት ውስጥ ሆና ከማስታመም በስተቀር ወጥታና ሰርታ ተጨማሪ ገቢ ለማምጣት እንዳትችል ሳንካ እንደፈጠረባት ሲቃ እየተናነቀው ይናገራል።
ሸምሱ፤ የጤናው መቃወስ ይሄንን ጠንካራ የመንፈስ ከፍታውን የናደበት ሲሆን፤ «አሁን ካለሁበት የችግር አረንቋ እንድወጣ እጃችሁን ዘርጉልኝ» ሲል ጥሪውን ለአገሩ ህዝብ ለማቅረብ ተገድዷል። ለርዳታ ጥያቄ የተዘረጋውን እጁን ተከትሎ የሁለት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹን ምላሽ እንዳገኘ አጫውቶናል።
«እስካሁን የሁለት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼን መጎብኘት አስገኝቶልኛል። አንዷ ሁለት ሺ ብር አንደኛዋ ደግሞ አንድ ሺ ብር ሰጥተውኛል። ይሁን እንጂ፤ የእነዚህ ወገኖች ድጋፍ አሁን የደረሰበትን የጤና ችግርና ባዶውን ማጀት ለመሙላት አይችልም። አሁንም ጥያቄ የሆነብኝ ነገር አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ስለምን በእኔ ላይ ጨከነ? ምን በድየው ይሆን!? ሊያስታውሰኝ እንዴት አቅም አጣ? ምን ላይ ወደክ እንኳን አላለኝም። እንዴት ነህ መባሉ የተሰበረን መንፈስ ያክማል። የገንዘብ ድጋፍ ይቅርና እስካሁን የት ወደክ አላለኝም። ይህ ሁሌም ጥያቄ የሚያጭርብኝና የዘወትር ብስጭቴ ነው» ሲል ሃሳቡን ይቋጫል።
አገራችን ብዙም ስሟ በማይነሳበት በእርምጃ ውድድር በግሉ ጥረት ከፍ ብሎ የነበረውን የቀድሞ አትሌት ሸምሱ ሀሰን በአሁን ወቅት ካጋጠመው የጤና ቀውስና ከገባበት የችግር አረንቋ እንዲወጣ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል። በአሁን ወቅት በአዕምሮ ህመም መሰቃየት ብቻም ሳይሆን በጡረታ በሚያገኛት አንድ ሺህ አራት መቶ ብር ስድስት ቤተሰብ እያስተዳደሪ እንደሚገኝ ተናግሯል። ሸምሱ እንዲህ እንደዛሬው ህይወት ፊቷን ሳታዞርበት የጤናው ሁኔታም ባልተቃወሰበት ወቅት በአትሌቲክሱ በተወዳዳሪነት ብቻ ሳይሆን በአሰልጣኝነት አገልግሏል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆንም ለአገሩ ለመድማትና ለመሞት እራሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ሸምሱ አነሰም በዛም እናት አገሩን ለማገልገል የተቻለውን ያህል ርቀት እንደመሄዱ፤ ከዛሬው ሰቆቃው እንዲወጣ ሁሉም የበኩሉን ሊያግዘው ይገባል። በተለይ፤ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቀድሞውን አትሌት ማስታወስ ይጠበቅበታል። የአገር ባለውለታ የሆነውና የተረሳው የቀድሞው አትሌት የዚህ ባለታሪክ ሆኖ ይቅረብ እንጂ፤ አስታዋሽ የማጣት ቁጭት፤ የጤና መቃወስ፣ የወገን አይዞህ ባይነት ማጣት እንደ ሸምሱ ሁሉ በበርካታ የአገር ባለውለታዎች ላይ የደረሰ በደል ነው። በጉብዝናቸው ወቅት ለአገራቸው ታሪክ የሰሩትን በቁም እያሉ ለመርዳትና ለማዳን ርብርብ አለማድረግ ሲያልፉ ቁጭትን ሲያጭር በተደጋጋሚ ይስተዋላል። በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የነበሩ የአገር ባለውለታዎችን ተረባርቦ በህይወት ለማቆም ሳይሆን ከሞቱ በኋላ ኃውልት ለማቆም መሯሯጥ መገለጫችን ይመስለኛል።
የአገር ባለውለታዎችን ማሰብ ጥቅሙ ለአገር ነው። በተለያዩ ዘርፎች ለአገር የአቅማቸውን የሚበረክቱ ጀግኖችን ማፍራት ብቻ ሳይሆን፤ ከከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጀግኖችን የመርሳት አባዜም ባለቤት ነን። በተጨማሪም በቁም ሳለ ከችግሩ፣ ከበሽታው ለማዳን ርብርብ ከማድረግ ይልቅ ለመቅበር የሚደረገው ርብርብ «አጃኢብ»ያሰኛል። ለዚህም ትልቁ ማሳያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቲክሱ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረጉ ጀግኖችን ማስታወስና መዘከር የማይሆንለት እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ታዝበነዋል። በተለያዩ አለም ዓቀፍ ውድድሮች ላይ በእርምጃ ውድድር ሜዳሊያዎችን ያገኘው የቀድሞው አትሌት ሸምሱ፤«አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ስለምን በእኔ ላይ ጨከነ? ምን በድየው ይሆን? ሊያስታውሰኝ እንዴት አቅም አጣ?» ሲል ቁጭቱን ሲገልጽ ታዝበናል።
በኦሊምፒኮችና በዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ ኢትዮጵያን ወርቅ በወርቅ ያደረጉ ጀግኖች አትሌቶች ዋና አሠልጣኝ የነበሩት ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬን፣ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርን በህይወት ሳሉ በመርሳት፤ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ኃውልት ለማቆም ሲታትር ነበር። ይህም ፌዴሬሽኑ አንጋፋዎቹ የአገር ባለውለታዎች ህይወታቸው ሳይቃወስ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ፤ ሲሞቱ ለሙሾና ለሀውልት ከመሮጥ አባዜው ዛሬም እንዳልተላቀቀ ከተለያዩ ወገኖች የተሰነዘረ ትችት ነው።
ፌዴሬሽኑ ትናንት ከሰራው ስህተት ከመማር ይልቅ፤ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ለመፈጸም እደማይመለስም አብሮ የተነሳ ሃሳብ ነበር። በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል የአገር ባለውለታዎችን እጀ ሰባራ የማድረጉ ስንኩሉ ልምድ በስፖርቱ ብቻም ሳይሆን፤ በተለያዩ የሙያ መስኮች የዜግነት ግዴታቸውን የተወጡ የአገር ባለውለታዎች የመደገፍ ልምዱ ኢምንት ነው። የአገር ባለውለታዎቹ ምናልባትም የሚታወሱት ወይ ታመው አልጋ ሲይዙ፣ ወይም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ነው፡፡ አንጋፋዎች ሲዘነጉ ተከታዩ ትውልድ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ለባለውለታዎች ዕውቅና ለመስጠት በሕግ ማዕቀፍ የሚመራ የሜዳሊያና የኒሻን፣ በአገልግሎት ዘመን መጠን የሚበረከት ሽልማትና የምሥጋና ሥነ ሥርዓት ሊኖር ይገባል፡፡ አገርን በፍቅር ማገልግል የውዴታ ግዴታ ቢሆንም፣ አስመስጋኝ ተግባር ላከናወኑ አኩሪ ዜጎች ዕውቅና መስጠት የአገር ባህል መሆን ይገባል ባይ ነን፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
ዳንኤል ዘነበ