እ.ኤ.አ በ2016 ወረሃ ግንቦት በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት አስደሳቹ ዜና ተሰማ። ዩናይትድ የዓለማችን ቁጥር አንድ አሰልጣኝ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ፖርቹጋላዊው ጆሴ ሞሪንሆ እንዳስፈረመ አስታወቀ። ከቼልሲ ክለብ የተሰናበቱት ጆዜ ሞሪኒሆ ማንችስተር ዩናይትድን ለማሰልጠን መስማማታቸው ነበር። ክለቡ በዓመት እስከ10 ሚሊዮን ፓውንድ ለ3 ዓመት ሊከፈላቸው ስምምነት መድረሱን ነበር ያስታወቀው፡፡
የጆዜ ወደ ዩናይትድ የመምጣታቸው ጉዳይ በስፋት ያነጋገረ ቢሆንም፤ በብዙ ደጋፊዎች ዘንድ አዎንታዊ መልክ የያዘ ነበር። ሰውዬው ኃያሉን ክለብ በአሰልጣኝነት ለመምራት ትክክለኛው ሰው መሆናቸውን የክልቡ ደጋፊዎች በአንድ ድምጽ መሰከሩላቸው። በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጡረታ ከወጡ በኋላ የተዋጣለት አሰልጣኝ ለማግኘት ተቸግረው ነበር። የዩናይትድን ሀያልነት አስጠብቆ ለማስጓዝ የሚችል ከወዴት ይገኛል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነም በማመንም ጭምር ነበር፤ «ዘ ስፔሻል ዋን» በሚለው ቅጽል ስም የሚታወቁት ጆዜ ሞሪኒሆ ዶሳንቶስ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ወደ ዩናይትድ ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ አምስት አንጋፋ ክለቦችን አሰልጥነዋል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ሦስት ጊዜ አንስቷል። በዓለም የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ቻምፒየንስ ሊግ ለሶስት ጊዜ ማንሳት ችለዋል። የእነዚህ ሁሉ ስኬቶች ባለቤት መሆናቸው በዩናይትድ ቤትም ስኬታማ ይሆናሉ የሚል ተስፋ እንዲጣልባቸው ያደረገ ነበር። አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ከክለቡ ጋር ግንቦት እኤአ 2016 የተፈራረሙና ለሁለት ዓመት ተኩል ከማንችስተር ጋር ቆይታ ያደረጉ ቢሆንም የክለቡን ኃያልነት ለመመለስ ተስኗቸዋል። እኤአ በ2016 የውድድር ዓመት ፕሪሚየር ሊጉን ማንሳት ባይችሉም የኮሚኒቲ ሺልድ፣ የአውሮፓ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች አሸንፈዋል። በ2017 ደግሞ ማንቸስተር ሲቲን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው።
በቻምፒዮንስ ሊግም ሆነ በአውሮፓ ሊግ ስኬታማነት ለመሆን ያለመቻሉ በውድድር ዘመኑ ጥሩ ያለመሆኑ ነበር። ክለቡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ውጤት የራቀው ሲሆን በ17 ጨዋታዎችን 26 ነጥብ ብቻ በመያዝ በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የክለቡ አቋም የቻምፒዮናነት ጉዳይን የማይታሰብ እያደረገ መምጣቱን ተከትሎ ጆዜ ከክለቡ ጋር ያላቸውን ቆይታም ጥያቄ ውስጥ አስገብቶት ቆይቷል። በክለቡ አመራሮችም ሆኑ በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ጉርምርምታና ተቃውሞ እየተባባሰ ነበር የመጣባቸው።
ጆዜ ክለቡን ወደቀደመው ክብሩ የመመለስ አደራቸውን ሳያሳኩ ትናንት በክብር ተሰናብተዋል። የማንቸስተር ዩናይትድ የእግር ኳስ ክለብ ባወጣው መግለጫ፥ አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት በቆዩበት ወቅት ለሰሩት ስራ አመስግኗል። በቀጣይም ስኬት ተመኝቶላቸዋል። የታላቁ ክለብ ቀጣይ አሰልጣኝ ማን ሊሆን ይችላል? ዘ ስፔሻል ዋን በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የጆዜ ሞሪኒሆ መንገድ ወዴትኛው ክለብ ይሆን? የሚሉት ጉዳዮች የስፖርት ቤተሰቡን ልብ ያንጠለጠለ ጉዳይ ሆኗል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
ዳንኤል ዘነበ