የራሷ የዘመን አቆጣጠር ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ በማህበረሰቡ አማካኝነት የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን ያካሄዳሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ክረምት አልፎ አዲስ ዘመን በተለወጠ ቁጥር የአዲሱን ዓመት መዳረሻና መባቻ የሚያመላክቱ የተለያዩ ባህላዊ አከባበሮች በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ የ13 ወር ፀጋ ባለቤትነቷን የምትታወቅበት የጳጉሜን ቀናት በአማራ ክልል በጎጃም እና በሌሎችም አካባቢዎች “እንግጫ ነቀላ”፣ በኦሮሚያ ደግሞ “ሽኖዬ” ወይም ከእንግጫ ነቀላ ጋር በቀጥታ የሚገናኘው “ቁኒ ቡቂ ፈና” እየተባለ የሚጠራው በዋናነት ይነሳል። በዚህ በ13ኛው ወር ላይ አሮጌው ዓመት ተሰናብቶ አዲሱ መምጣቱ ይነገርበታል። ለመሆኑ እንዴት ከተባለ መነሻው ነሐሴ ወር ቢሆንም፤ እስከ ወርሃ መስከረም ድረስ በወጣት ልጃገረዶች እና ወንዶች የሚዘወተሩት በአደይ አበባ፣ በእንግጫ፣ በከሴና በለምለም ሣር የሚታጀቡት በዓላት ሰፊውን ቦታ ይይዛሉ።
በዓላቱ በባህላዊ ሥርዓቶች የሚደምቁ ሲሆን፤ ሁሉም አዲስ ዓመት መምጣቱን የሚያበስሩ ናቸው። እናም ለዛሬ ወደ አማራ ክልል ጎጃም ወደ ኦሮሚያው የተለያዩ ቦታዎች እንጓዝና የተለያ መረጃ ምንጮችን አብነት አድርገንና በዘርፉ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን የሠሩ ሰዎችን ሐሳብ በማካተት እናቀርባለን።
በመጀመሪያ ከምስራቅ ጎጃሙ እንነሳ፤ ጳጉሜን ይዞ እስከ መስከረም መጀመሪያ ድረስ የሚዘልቅ ነው። በዓሉ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በልጃገረዶች አመካኝነት የሚከበርም ነው። ስያሜውም የእንግጫ ነቀላ ይባላል። በባህሉ አክባሪዎች ዘንድ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ብቻ ሳይሆን የመተጫጫ በዓልም ጭምር እንደሆነ ይታመናል።
እንግጫ ማለት የሣር አይነት ሲሆን፤ ልጃገረዶች ወንዝ ዳር ወርደው በለምለሙ ሜዳ ላይ ሄደው የሚያገኙት ነው። አገልግሎቱ ለስፌት የሚጠቅም ሲሆን፤ በበዓሉ ጊዜ ግን ሌላ ግልጋሎት ይሰጣል ይላሉ በምስራቅ ጎጃም የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ውዳለም አለማው። እርሳቸው እንደገለፁልን፤ ልጃገረዶች እንግጫ ነቀላውን የሚካሄዱት ዘመን ሲለወጥ ሲሆን፤ ባህላዊ አከዋወንም ይታይበታል። በአዲስ ዓመት ዋዜማ ማለትም በጳጉሜን 5 ወይም 6 ልጃገረዶች በጠዋት ተነስተው ወንዝ ወርደው የሚያደርጉት ክዋኔም ነው። ከዚያ በዚያው ቀን ማምሻ ላይ የነቀሉትን እንግጫ ይጎነጉኑታል። ይመድቡታል።
ሲነጋ ልጃገረዶቹ ከያሉበት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰው ቤት እየዞሩ የተጎነጎነውን እንግጫ የቤቱ ምሰሶ ላይ በማሰር አዲሱን ዓመት መምጣቱን ያበስራሉ። ይህ ባህላዊ ክዋኔ በዜማና በጭፈራ የታጀበ ነው∷ የልጃገረዶች በዓል በሰሜን ሸዋ፣ በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥቶት ይከበራልም ብለውናል።
ለዓመታት ግን እየደበዘዘና በከተሞች አካባቢም እየጠፋ በመሄድ ላይ እንዳለ የሚገልፁት ሃላፊዋ፤ ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ የሚመደበው ይህ የልጃገረዶች ጨዋታ፤ አሁን አሁን እንደገና እየደመቀ መምጣቱን የሚያሳዩ መልክቶች አሉ። በተለይም ዘንድሮ በክልሉ በደመቀ ሁኔታ ሲከበር ነበር። ማህበረሰቡ እንዲያውቀውና እንዲተገብረው ከማድረክ አኳያም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጥናት ሳይቀር አስጠንቶ ችግሮቹ እንዲለዩና መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ በድምቀት አክብሮታል ይላሉ።
በዓሉ እንደ ፈረንጆቹ የጎዳና ላይ ፌሽታ በሚሉት መልኩ በአደባባይ ይከብሯል። ይህ ደግሞ ባህሉን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ መነቃቃትን ይፈጥራል የሚሉት ወይዘሮ ውዳለም፤ ይህ በዓል በምስራቅ ጎጃምና በአዊ ዞኖች የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ በሚል ይከበራል። ከሌሎች የአደባባይ በዓላትም የሚለየው የሚጠቀመው ቁሳቁስና ክዋኔው የሚደረግበት ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ።
በዓሉ ብዙ ጊዜ በሀገሬው አጠራር «ደቦት» ወይም ችቦ ለማዘጋጀት የሚያገለግል ኮሸሽላ የተባለ እንጨት በመሰበሰብ የሚጀመር ነው። ጠመናይና ቀበርቾ የተባሉ ቤት ውስጥ የሚጨሱ ሥራ ሥሮችን ጨምሮ ነሐሴ 16 ቀን የሚጎዘጎዝ «ከሴ» የተባለ ጥሩ መዓዛ ያለው ተክል ከአደይ አበባ ጋር ተደባልቆ ይታጨድና አዲሱ ዘመን በጥሩ ስሜት የሚያልፍበት እንደዚህ ጥሩ ሽታ የሚመጣበት ይሁን ሲሉም ልጃገረዶች የሚያበስሩበት መሆኑንም ያስረዳሉ።
በዓሉ በዚህ ሁኔታ ይቀጥልና የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ የእንግጫ ነቀላ በዓል ይከናወናል። በእንግጫ ነቀላ ወቅት ልጃገረዶች የተለያ ዜማዎችን የሚያዜሙ ሲሆን፤ ለአብነትም ጥቂት ስንኞችን እናንሳ።
የቅዱስ ዮሐንስ ያልዘፈነች ቆንጆ
ቆማ ትቀራለች እንደ ሰፈር ጎጆ። ይህንን የሰሙ የአካባቢው ጎረምሶች ደግሞ ወደ ልጃገረዶቹ ይመጣሉ። ይህን ይላሉ።
እንግጫችን ደነፋ
ጋሻውን ደፋ
እንግጫዬ ነሽ ወይ
እሰይ እሰይ። ሲሉ ለመታጨት ምትፈልግ ሴት ደግሞ እንዲህ የሚለውን ስንኝ ታወርዳለች።
አበባው ያብባል በየሁሉ ደጅ
ምነው እኔ የለኝ የከንፈር ወዳጅ
አንት የከንፈር ወዳጅ በጊዜ ሳመኝ
ጤፍ አበጥራለሁ የሰው ግዙ ነኝ
የሰው ግዙ ሆኖ የሰው ግዙ መውደድ
እሳት በገለባ እፍ ብሎ ማንደድ ።
ለቅዱስ ዮሐንስ የላክልኝ ድሪ ሰላላ መላላ
መልሰህ ውሰደው ጉዳይም አይሞላ። እያሉ ያፌዙበታል። ከዚያ ከወደዳት ወደ እርሷ ይጠጋና ማተብ ያስርላታል።
ይህ በዓል በዋናነት የልጃገረዶች በዓል ቢሆንም አመሻሽ ላይ በልጆችና በልጃገረዶች የተነቀለው እንግጫ እየተጎነጎነ ጣራ ላይ ያድርና ጠዋት ላይ በዘመን መለወጫ ዕለት ለበረከትና ለረድዔት በሚል ራስ ላይ፣ የሊጥ ዕቃ ላይና ሌማት ላይ ይታሰራል። የተጎነጎነው እንግጫም እስከ መስቀል በዓል ድረስ ይቆይና ከደመራ ጋር ይቃጠላል። አመዱንም ከህፃን እስከ አዋቂ ይቀባዋል። ይህ ደግሞ በባህሉ ዘንድ ጤንነት ይሰጣል ተብሎ ይታመንበታል።
ስለ እንደነዚህ አይነት በዓላት ሲነሱ ሳይጠቀስ የማያልፈው በዓሉ ግርማ ባሳተመው ‹‹ደራሲው›› በተሰኘው ልቦለዱ ላይ የጠቀሰው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የመስከረምን ድባብ በሚገባ ያሳየናልና ነው። እናም ምን አለ ካላችሁ ይኽው ሐሳቡ፤ ‹‹መስከረም ጠባ። የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች። ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመሩ። አደስ ተቀቡ። እንሶስላ ሞቁ። ወንዝ ወረዱ።
ቄጤማ ለቀሙ። ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ አሽንክታባቸውን አጥልቀው፣ ‹አበባዬ ሆይ – ለምለም› በማለት ተሰብስበው ብቅ አሉ – እንደ ጮራይቱ። የወርሐ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ። ጠፍ እያለ መጣ ምድሩ። ወንዙም እየጠራ። ኩል መሰለ ሰማዩ። ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ። ደመራ ተደመረ። ተቀጣጠለ ችቦ። ‹ኢዮሃ አበባዬ – መስከረም ጠባዬ› ተባለ።›› ነው።
ይህ ታዲያ ምን ያሳየናል፤ ከእንግጫስ ጋር ምን አገናኘው ከተባለ መልሱ እንዲህ ነው። ልጃገረዶች ይህንን አብነት አድርገው ነው በዚህ ወቅት እንዲህ የሚሆኑት። በዚያው ልክ እንግጫ የዕንቁጣጣሽ ብሥራት ነጋሪ ነው። ስለዚህም ልጃገረዶች ሳዱላቸውን ያሳምራሉ፤ አደስ ተቀብተውም አልባብ አልባብ ይሸታሉ። እንሶስላ ሞቀውም የእግራቸውን ተረከዝ ማማር ለአጫቸው ጎረምሳ ያሳያሉ። የት ከተባለ ወንዝ በመውረድ ነው።
ይህ ወር ማለትም አሥራ ሦስተኛዋ ወር በጎጃም ብቻ አይደለም እንደ ኖኅ እርግብ ንፁህ የሆኑ ልጃገረዶች የሚያብረቀርቁበት። በኦሮሚያው በተለይም በሸዋ ኦሮሞ ዘንድ በስፋት የሚከበር ሲሆን፤ ሽኖዬም ወይም ቁኒ ቡቂ ፈና እያሉ ልጃገረዶች የደስታ ቀናቸው አድርገው ያከብሩታል። ምክንያቱም ለምለሟ የኦሮሚያ ምድርም ከመችውም ይልቅ አረንጓዴ ትለብሳለች። አፈሯም ሆነ ወንዞቿ እርጥብነታቸውን የሚገልፁበት ጊዜ ነው። እናም ማንኛዋም ልጃገረድ ነፃ ሆና እንደ ጥጃ በለምለሙ መስክ ላይ እየቦረቀች የአዲስ ዓመት ብስራትን ትናገራለች።
ሽኖዬ ወይም እንግጫ ወይም ቁኒ ቡቂ ፈና ለኦሮሚያ ልጃገረዶች ደስታቸውን ከተፈጥሮ ሁኔታው ጋር እያጣጣሙ የሚያሳልፉበት፤ ልዩ ዕለትና ቀን እንደሆነ የሚናገሩት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ከበደ ለሊሳ ናቸው∷ በሁሉም ወር ሁሉም የኢትዮጵያን ምድር መጓዝ ብዙ ያሳያል። ምክንያቱም ጳጉሜን ሌላ ድባብ ያለው ለብቻው አንድ ወር በልዩ ሁኔታ የሚከሰትበት ምድር በልጃገረዶች ኩነት ይደምቃል። እንደ ጥር ሁሉ ጳጉሜን የልጃገረዶቹ ድምጽ ዜማ የሚወጣበት፣ ፊታቸው ሐሴት የሚቀዳጅበት ቀን ነው። ስለዚህም ልጃገረዶችም ይህን ጊዜ ማለትም ጳጉሜን በእሴታቸው አድምቀው ይውላሉ።
እንደ አቶ ከበደ ገለፃ፤ ይህ ጊዜ ልጃገረዶች የአዲስ ዓመት ብስራትን ብቻ የሚናገሩበት አይደለም። ይልቁንም ነፃነታቸውን በአደባባይ የሚያሳዩበት፤ ወዳጅነትን የሚመሰርቱበት፤ ራሳቸውን አስውበው የሚያሳዩበት ነው። በዚህም ከርቀት የሚመለከታቸው ጎረምሳ ለእጮኝነት የሚመርጥበት ስለሚሆንም ይህንን ጊዜ በሰፊ መድረክ ለመጠቀም ይተጋሉ። በእርግጥ ይላሉ አቶ ከበደ በእርግጥ በኦሮሞ ባህል በዚህ ወቅት ወንድና ሴት አብሮ መጫወት አይፈቀድለትም።
ይህ በዓል የሴቶች ብቻ ነው። ስለዚህም ከአማራ ክልሉ ለየት የሚያደርገው በአንድነት ወንድና ሴት አለመጫወታቸው፤ ለመተጫጨትም ተብሎ የሚከወን አለመሆኑ ነው። በተመሳሳይ አለባበሱም ይለያል። ግን ከርቀት ሆኖ መመልከት አይከለከልምና መምረጥ የሚችልበትን አጋጣሚ ሊፈጥርለት ይችላል ።
ይህ ጊዜ ለልጃገረዶች አንድነትና ጥንካሬም ጭምር የሚያሳዩበት ነው። እናም ሰርዶና አደይ አበባ ነቅለው ለምለሙ ጊዜ መጥቷል፤ ጭለማው ተገፏል ሲሉ በየቤቱ እየሄዱ ይዘፍናሉም ይጨፍራሉም። ይህ ደግሞ በሌሎች ክልሎች ከሚከወነው የልጃገረዶች በዓል ጋር የሚያመሳስለው እንደሆነ ይናገራሉ። ጳጉሜን ማጠሯ የሚቆጨውም ጎጃም ገብቶ እንግጫ ነቀላውን በተመሳሳይ ኦሮሚያ ሄዶ ቁኒ ቡቂ ፈናውን ወይም ሽኖዬውን የተመለከተ ነው። ምክንያቱም በዚያ የሚያያቸው ብዙ ክዋኔዎች አሉ። በእርግጥ ለብዙ ዓመታት ይህን በዓል ብዙዎች አያውቁትም ነበር። በተለይ ኦሮሚያ ላይ የሚከበሩት ተደብቀው ቆይተዋል። እናም አሁን አዲሱ ትውልድ በርትቷልና ለማክበር በዝግጅት ላይ ናቸው ሲሉ አጫውተውኛል።
የእናቶቻቸውን ወግ የተከተሉ ጎበዝ ሴቶች ተአምር እያሳዩን ናቸው የሚሉት አቶ ከበደ፤ ንፁህ ሴቶች፣ ደናግላኖች ኖኅ የላካት ቁራ ስትቀርበት ለምስራች እንደላካት እርግብ ሆነው የአዲሱን ዓመት መምጣት የዋህ በሆነው ልባቸው ይነግሩን ጀምረዋል። ስለዚህም ይህንን የማስቀጠሉ ሁኔታ መጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል።
እኛም እንደ እርግቧ የምስራች መግለጫ የሆነውን እንግጫን ወይም ቁኒ ቡቂ ፈና በመያዝ ሰላምን የሚያበስሩልንን ልጃገረዶች ተከትለን ዘመኑ የልምላሜና የበረከት ምልክት ይሁንልን∷ የልጃገረዶቹ እንግጫ በእርግጥም ለጎረቤቶቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን አዲስ ዘመን መጥባቱን የሚያበስር ያድርግልንም። በዜማቸው ውበት፣ በአደይ ምስጋናቸው ቅኔ ምድራችን ትረስርስ ብለንም መረቅን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው