በቅርቡ ነው አሉ።በመሀል አራት ኪሎ። አንዲት ሴት ከመስሪያ ቤት ወደ ቤቷ ለመሄድ በመንገድ ላይ ነች። በዚህ ሰዓት መንገዱ ይጨናነቃል። መኪኖችና እግረኞች ከወዲያ ወዲህ ይተራመሳሉ። አንዳንዴ ወጪ ወራጁ ሲበረክት እርስበራስ መገጫጨት ይኖራል።ልክ እንደ ሩቅ ምስራቆቹ እንደ ቻይኖቹ ጎዳና።
ወደቀደመው ጉዳይ ልመለስ።ወደ ሴቲቱ መንገደኛ።ሴትዬዋ ከትከሻዋ ቦርሳዋን ጣል አድርጋ እየተራመደች ነው።የቀን ውሎዋ ያደከማት ይመስላል። ባሻገር ደግሞ ስለቤቷ ታስባለች። ምናልባትም ሰለልጆችዋ፣ገብታ ስለምትከውነው የጓዳ ጣጣዋ።ከበስተኋላዋ ሰዎች ይከተሏታል። እሷም ከፊት ለፊቷ የሌሎችን ጀርባ ተከትላ ትራመዳለች።
መኪኖች ያልፋሉ፣እግረኞች ይሄዳሉ።አንዱ ሌላውን ያስተውላል።እሱም ያለፈ የሄደውን ይቃኛል።ይህ ደግሞ ሁሌም እንዲህ ነው። መተዛዘብ፣መተያየቱ ተለምዷል።እይታው ግልምጫን ከአድናቆት የሚያካትት ነው።አንዳንዱ በደመነፍስ ይጓዛል።አንዳንዱ ነገሬ ብሎ ዓይኑን ከሰው ይጥላል።
ከበስተኋላ የሚሰማ የሞተር ሳይክል ድምጽ እየቀረበ ነው።መንገደኛዋ መራመዷን ቀጥላለች። ሞተሩ ሁለት ሰዎችን ይዟል።አንዱ ሾፌር ነው። ሌላው ደግሞ ከኋላ ተፈናጣጭ።ድንገት እንደ ንፋስ ሽው የሚለው ሞተር ሴትዬዋ አጠገብ ሲደርስ እንደመቀዝቀዝ አለ ።ከኋላ ያለው ተፈናጣጭ አይኖቹ እንደ ንስር ይቃብዛሉ፣እጆቹ እንደ አሞራ ክንፍ ተዘርግተዋል።ሽውታው በሰማይ እንዳለ በራሪ ይመሰላል።
አሁን ሴትዬዋን በቅጡ ተጠግቷታል።በድምጽ አደናብሮ ማስደንገጥ ሳይፈልግ አልቀረም።ይህን ደግሞ ብዙዎች ያደርጉታል።የሰውን ቀልብ መግፈፍ ያስደስታቸዋል።ሌላው ሲደነግጥ ደስታቸው ይበረታል። ልክ እንደ ህንድ አክተር የሆኑ ይመስላቸዋል።ምንአልባትም ለእነሱ በርካቶች ተደንቀው የሚያጨበጭቡላቸው ያህል ይኮፈሳሉ። እናም በጨኸት አካባቢን እያወኩ ይሮጣሉ፣ ይፈጥናሉ። ብን…ሽው… ሌላው ብሽቅ… እርርርርርር…
ሴትዬዋና ሞተር ሳይክሉ አሁንም ጎን ለጎን ናቸው።ተፈናጣጩ ይበልጥ ነቅቷል።አፈናጣጩ ስልተኛ ሆኗል።እሷ እንደ ቀደመው ነች።በድካም ስሜት መጓዟን አልተወችም።በድንገት ትከሻዋ ላይ ከባድ እጅ ወደቀ። አፍታም ሳይቆይ ተፈናጣጩ ቦርሳዋን አንጠልጥሎ ሲከንፍ ታዬ። ይኽኔ ሴትዬዋ በድንጋጤ ራደች።በፍርሀት ተንቀጠቀጠች።ለመጮህ ያደረገችው ሙከራ በሞተር ሳይክሉ የደመቀ ጨኸት ታፈነ። ሞተረኞቹ የያዙትን ይዘው በፍጥነት ብን…ሽው… አሉ።
ይህን ያየ አንድ ታክሲ ከኋላ ሊከተላቸው ሞከረ።እንደው ልፋ ቢለው እንጂ ጭራቸው የሚያዝ አልነበረም። በእነሱ ቤት በፊልም ያዩትን እየደገሙት ነው።በድል አድራጊነት፣ በአሸናፊነት፣ ወደፊት ብን…ሽው…
እንደተለመደው ሰዎች ተሰባሰቡ። አንዳንዶቹ ባንክ ገብታ ስትወጣ ተከትለዋት እንደሆነ በእርግጠኝነት ተናገሩ።ገሚሶቹ ደግሞ የድርጊቱ አስከፊነት አሳስቧቸው የያዙትን አጠበቁ።እርስበርስ መነጋገሩ ሲበረክት ፍርሀትና አለመተማመን ነገሰ ።ድንገት ሽው የሚልና ድምጹ የሚልቅ ሞተር ሳይክል ብቅ ሲል በክፉ የሚያዩት ዓይኖች ይቀባበሉት ያዙ።
እነሱ ልክ እንደ አሞራ እንደ ሰማዩ ጭልፊት ግዳይ ጥለዋል።አሞራና ጭልፊትም እኮ እንዲሁ ናቸው።ወደምድር ሲያንዣብቡ ቆይተው ክው በሚያደርግ ቀልብ ገፋፊ ጥፊያቸው ጆሮ ግንድን ያልሳሉ። ድርጊታቸው ደግሞ በዚህ ብቻ አያበቃም።በጠንካራ ጥፍራቸው ታግዘው አይተው የጎመጁትን ጉዳይ አንጠልጥለው ከፍ… ከፍ.. ከፍ ብለው ይበራሉ። ወደ ሰማይ ወደ ዳመናው።
ወዳጆቼ! እነዚህ የምድር ላይ ጭልፊቶች ዓላማና ግባቸው አንድና አንድ ነው።ያዩትን የጎመጁበትን ቦርሳ መንትፎ መብረር ብቻ።ከዚህ በዘለለ የምትነጠቀው ሴት በእነሱ ጉተታ ተሰበረች፣ ተላላጠች፣ ሞተች ደንታቸው አይደለም።ለነገሩ ሌባ ብሎ የዋህና ደግ የታለና! ሁሌም ቢሆን ለራሱ ብቻ የሚያመቸውን ያደርጋል።ያሰበውን ለማግኘት መግደል ፣መደብደብ አካል ማጉደል ካለበት ያለጥርጥር ያደርገዋል።
የዛን ዕለት ስለሴትዬዋ መውደቅና መሰበር አልጠየቅሁምና የሰማሁት የለም።የደረሰባት ድንጋጤ ከባድ እንደሚሆን ግን መገመት ይቻላል።እንዲህ አይነቶቹ መንታፊዎች ድርጊቱን ለመፈጸም ሞተሩን በኪራይና በውሰት ስለሚጠቀሙ ማንንታቸውን ለማወቅ ይቸግራል።
አሁን ላይ ደግሞ ከመኪናው ቁጥር ያልተናነሰ የሞተር ሳይክል እንደ አሸን እየፈላ ነው።ይህ መሆኑም ወንጀል ፈጻሚዎቹን በቀላሉ ተከታትሎ ለመያዝ የሚቸግር ይሆናል።አብዛኞቹ ድርጊቱን ለመፈጸም ሲያስቡ ታርጋ አልባ ሞተሮችን ይጠቀማሉ።ሲያሻቸውም በለመደው እጃቸው የሌላውን ቁጥር ፈተው ከእነሱ ላይ በመግጠም ይንቀሳቀሳሉ።
ብዙዎች ሞተር ሳይክልን ለመለማመድ ጊዜና ገንዘባቸውን ይከፍላሉ።አንዳንዶች ይህን ማድረጋቸው ንብረት ይዘው የገቢ ምንጭ ለማፍራት ነው።ጥቂቶች ደግሞ እጃቸንን ፈተናል ብለው ባሰቡ ጊዜ ችሎታቸውን የሚያሳዩት እንዲህ አይነቱን ግዳይ በመጀመር ይሆናል።ሁሌም ሁለት ሆነው በረራ የሚያካሂዱት አሞራዎች መንገዳቸው ሁሉ ጥንድነት አይለየውም። አየሩን ቀዝፈው ባህር እንደሚያሻግሩት የአይሮፕላን ካፒቴኖች ሁሉ ይህም ተግባር በዋናው አብራሪና በረዳቱ አጋዥነት የሚከወን ነው።
ሁሌም ቢሆን የሞተር አብራሪው ተግባር መሪውን በመጨበጥና አካባቢውን በመቃኘት ይጀምራል። ሁለቱም ይህን ለማድረግ ባይቦዝኑም የረዳቱ ተግባር ደግሞ ከዋናው አብራሪ ይበልጥ ሀላፊነት የወደቀበት ይሆናል።ለእሱ ስልት መጠቀምና ፈጣን መሆን ዋንኛው ሚዛን ነው።አሞሮቹ ነጥቆ ለመሮጥ በመረጡትና በተስማሙበት ሰው አቅራቢያ ሲደርሱ ረዳቱ ስራውን ለመጀመር ከበስተኋላ ሆኖ ማኮብኮቡን ይቀጥላል።
ብዙ ግዜ ዘራፊዎቹ አሳቻ ሰዓት ስለሚጠ ቀሙና የተዘናጋውን ለይተው ስለሚያውቁ ሙከራቸው ከሽፎ አያውቅም።ውለው አድረውም ድርጊቱን በተመሳሳይ ቦታ ለመፈጸም የሚያግዳቸው አይኖርም።አሁን ይህ ስጋት የተሞላበት ጉዞ ለበርካቶቻችን ሰቀቀን መሆኑን ቀጥሏል። ለእነሱ ደግሞ ያልታሰበ ሲሳይ ማፈሻ እየሆነላቸው ነው።
ወዳጆቼ! አሁን ላይ በመንገዳችን የሚያሳስቡን ጉዳዮች ተበራክተዋል።ለትራፊክ አደጋው ስናስብ ዘረፋው፣እሱን አለፍን ስንል መጭበርበርና ሌላውም ጉድ ይከተለናል።እንደ ቀድሞው ለሴት ልጅ ክብር መጨነቅና ማሰቡ እየቀረ ነው።ይባስ ብሎ በአደባባይ ሰብዕናን የሚጎዳና ህሊናን የሚያስጨንቅ ድርጊት ነውር መሆኑ ተረስቷል ።
ጎበዝ!እኔ ግን እንዲህ እላለሁ ።ይህን ድርጊት የማናውቅና መደረጉን ያልሰማን እንደምንኖር ሁሉ በየጊዜው አስገራሚ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እያየን የምንታዘብ ደግሞ በርካቶች ነን።አሁን ማመን መታመን ይሉት መልካምነት «ነበር» መባል ጀምሯል።ከሁሉም የሚያዋጣው ከአሞሮቹ ሙጭለፋ ተጠንቅቆ ራስን መጠበቅ ብቻ ነው።እኔ የሞተር ሳይክል ድምጽ ስሰማ መጠንቀቅ ጀምሪያለሁ። እናንተስ?
መልካምሥራ አፈወርቅ